MAP

ሩሲያ ዩክሬንን ወርራ ባለችበት በአሁኑ ወቅት በዩክሬን ትምህርት መጀመሩ ተነግሯል ሩሲያ ዩክሬንን ወርራ ባለችበት በአሁኑ ወቅት በዩክሬን ትምህርት መጀመሩ ተነግሯል   (ANSA)

እ.አ.አ. በ 2026 ስድስት ሚሊዮን ህፃናት ከትምህርት ገበታቸው ውጪ እንደሚሆኑ ተገለጸ

የተባበሩት መንግስታት የህፃናት ኤጀንሲ ለትምህርት የሚሰጠው የገንዘብ ድጋፍ እ.አ.አ. በ 2023 ዓ.ም. ከነበረው በ 24 በመቶ በመቀነሱ ምክንያት በሚቀጥለው ዓመት ከትምህርት ውጭ የሚሆኑትን ህፃናት ቁጥር ወደ 278 ሚሊዮን ከፍ ያደርጋል የተባለ ሲሆን፥ ይህም በንፅፅር ሲታይ በጀርመን እና በጣሊያን ውስጥ ያሉትን ሁሉንም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ባዶ እንደማድረግ ይቆጠራል ተብሏል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በዸም አቀፍ ደረጃ ለትምህርት ይሰጥ የነበረው የገንዘብ ድጋፍ በመቋረጡ ምክንያት እ.አ.አ. በ 2026 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ወደ 6 ሚሊዮን የሚጠጉ ተጨማሪ ህጻናት ከትምህርት ገበታ ውጭ ሊሆኑ እንደሚችሉ የተባበሩት መንግስታት የህፃናት አድን ድርጅት (ዩኒሴፍ) ይፋ ያደረገ ሲሆን፥ ከእነዚህም ውስጥ አንድ ሶስተኛ የሚሆኑት በሰብአዊ ድጋፍ ሥር በሚገኙ አከባቢዎች እንደሆነም ጭምር ገልጿል።

ዸም አቀፉ ‘ይፋዊ የልማት ድጋፍ’ (ODA) ድርጅት ለትምህርት ይሰጥ ከነበረው አጠቃላይ ድጋፍ 3.2 ቢሊዮን ዶላር ይቀንሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ የገለጸ ሲሆን፥ ይህም እ.አ.አ. ከ 2023 ዓ.ም. ጋር ሲነፃፀር በ 24 በመቶ ዝቅ እንደሚል እና በእነዚህ የገንዘብ ድጋፍ ቅነሳዎች ምክንያት በዸም ዙሪያ ከትምህርት ገበታ ውጭ የሚገኙ ህፃናት ቁጥር ከ 272 ሚሊዮን ወደ 278 ሚሊዮን ወይም በሌላ አገላለጽ በጀርመን እና በጣሊያን ውስጥ ያሉትን አጠቃላይ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከመት ጋር እኩል ይነፃጸራል ተብሏል።

ኦዲኤ ወይም ይፋዊ የልማት ድጋፍ በኢኮኖሚ ትብብርና ልማት ድርጅት ሥር የሚገኘው የልማት ድጋፍ ኮሚቴ (DAC) የውጭ እርዳታን ለመለካት የሚጠቀምበት ሥርዓት ሲሆን፣ ዋና ዓላማው የታዳጊ ሀገራትን የኢኮኖሚ እድገትና ደህንነት ማሳደግ እንደሆነ ይገለፃል።

የኦዲኤ የገንዘብ ድጋፍ መቋረጥ በተለይም ደካማ በሆኑ እና በጦርነት በተጠቁ ግዛቶች ውስጥ እንደ ትምህርት፣ ጤና እና መሰረታዊ ማህበራዊ ፍላጎቶች ባሉ ወሳኝ ዘርፎች ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል ተብሏል።

የዩኒሴፍ ዋና ዳይሬክተር ካትሪን ራስል ይሄንን ጉዳይ አስመልክተው እንደተናገሩት ከትምህርት የሚቀነሰው እያንዳንዱ ዶላር የበጀት ውሳኔ ብቻ ሳይሆን የህፃናቱን የወደፊት ህይወት አደጋ ላይ የሚጥል ውሳኔ መሆኑን በአፅንዖት ገልጸው፥ ትምህርት በተለይም በሰብዓዊ ድጋፍ ሥር በሚገኙ አከባቢዎች ውስጥ ላሉ ህፃናት ወሳኝ የህይወት መስመር ሊሆን እንደሚችል እና ትምህርት ቤቶች ህፃናቱን የጤና እንክብካቤ፣ የጥበቃ እና የምግብ ከመሳሰሉ አገልግሎቶች ጋር እንደሚያገናኛቸው ጠቁመው፥ ከዚህም በተጨማሪ “ህፃናት ከድህነት እንዲላቀቁ እና የተሻለ ህይወት እንዲገነቡ ምርጥ እድል ይሰጣል” በማለት አስረድተዋል።

ለአደጋ የተጋለጡ ሃገራት
እንደ ዩኒሴፍ ትንታኔ መሰረት ምዕራብ እና መካከለኛው አፍሪካ በገንዘብ ቅነሳው ምክንያት በከፍተኛ ሁኔታ ከሚጎዱት ሃገራት ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፥ በዚህም መሰረት በእነዚህ አከባቢዎች ወደ 2 ሚሊዮን የሚጠጉ ህፃናት የትምህርት እድልን የማጣት ስጋት እንደሚያጋጥማቸው ተገልጿል።

ከዚህም በተጨማሪ በመካከለኛው ምስራቅ እና የሰሜን አፍሪካ ሃገራት ውስጥ ከትምህርት ገበታ ውጭ የነበሩ የ 1.4 ሚሊዮን ህፃናት ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ሊጨምር እንደሚችል የተገለጸ ሲሆን፥ 28 ሃገራት በቅድመ መደበኛ፣ በመጀመሪያ ደረጃ እና በሁለተኛ ደረጃ ሲደረግላቸው ከነበረው የትምህርት ድጋፍ ቢያንስ አንድ አራተኛውን ያጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ፥ ብሎም በኮትዲቯር እና ማሊን በመሳሰሉ ሃገራት የትምህርት ቤት ምዝገባ በ 4 በመቶ ቀንሶ በመታየታቸው ምክንያት አደጋ ከተጋረጠባቸው ሀገራት መካከል ይመደባሉ ተብሏል።

የትምህርት ድጋፍ ቅነሳው በዸም ላይ በከፍተኛ ደረኛ ተጽእኖ ከሚያሳድርባቸው ዘርፎች ውስጥ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት አንዱ እንደሆነ የተነገረ ሲሆን፥ ይህም አሁን ያለውን የትምህርት ችግር እንደሚያባብስ እና የተጎዱ ህጻናትን በ164 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የህይወት ዘመን ገቢን ሊያሳጣ እንደሚችል ተነግሯል።

ችግሩ ከትምህርትም በላይ ነው
በዸም ዙሪያ ሰብአዊ ቀውሶች በተጋረጡባቸው ሀገራት ትምህርት ማለት ከመማር ማስተማር ሂደት ያለፈ ነገር እንደሆነ የገለጸው ተቋሙ፥ በዚህ ሂደት ውስጥ ህፃናት ‘የህይወት አድን ድጋፍ፣ መረጋጋት እና የአእምሮ ጉዳት የደረሰባቸው ህፃናት ደግሞ የማገገም ስሜትን’ እንደሚሰጣቸው የተገለጸ ሲሆን፥ በእነዚህ ቦታዎች ወደ 10 በመቶ የሚሆኑ የድጋፍ ቅነሳዎች ሊኖሩ እንደሚችልም ተገምቷል።

ዩኒሴፍ በሮሂንጊያ ለሚገኘው የስደት ቀውስ በሚያደርገው ድጋፍ 350,000 ህጻናት በቋሚነት የመሠረታዊ ትምህርት ዕድል የማጣት አደጋ ላይ መሆናቸው የተነገረ ሲሆን፥ የተባበሩት መንግስታት የህጻናት ኤጀንሲ አስቸኳይ የገንዘብ ድጋፍ ካልተደረገ የትምህርት ማዕከላት ሊዘጉ እንደሚችሉ እና ህጻናትን ለጉልበት ብዝበዛ እና ለህገወጥ የሰዎች ዝውውር ተጋላጭ እንደሚያደርግ ይፋ አድርጓል።

የምግብ ፕሮግራሞችን የመሳሰሉ የትምህርት ቤት አገልግሎቶች ከ 50 በመቶ በላይ የገንዘብ ቅነሳ ሊያጋጥማቸው እንደሚችል፣ ከዚህም ባለፈ ለሴቶች ይደረግ የነበረው የትምህርት በጀት በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚቀንስ የተባበሩት መንግስታት የህፃናት አድን ዘገባ ያመላክታል።

ከዚህም ባለፈ እነዚህ ቅነሳዎች የተለያዩ አሉታዊ ውጤቶች እንዳሉት የተገለጸ ሲሆን፥ ከነዚህም መካከል መንግስታት በመረጃ ላይ ተመስርተው ትምህርታዊ ዕቅዶችን የመፍጠር አቅማቸውን እንደሚያዳክም፣ ለመምህራን እድገት ድጋፍ መስጠት እንዳይችሉ እና የትምህርት ውጤቶችን መከታተል እንዳይችሉ እንደሚያደርግ፥ ይህም ማለት ተመዝግበው መቆየት የሚችሉት ህጻናት እንኳን ሳይቀር የተጠናከረ ትምህርት የማግኘት ችግር ሊያጋጥማቸው እንደሚችል፥ ብሎም በዸም አቀፍ ደረጃ ቢያንስ 290 ሚሊዮን ተማሪዎች የትምህርት ጥራት ማነስ እንደሚያጋጥማቸው ተገልጿል።

ልጆቻችንን ይርዱ፣ ለመጪው ጊዜ ጥበቃ ያድርጉ 
የተባበሩት መንግስታት የህፃናት አድን ድርጅት ዩኒሴፍ ለጋሽ ሀገራት እና አጋሮች የትምህርት ዕርዳታውን ማመጣጠን እና የሰብአዊ ትምህርት የገንዘብ ድጋፍን ጨምሮ ተከታታይ እርምጃዎችን በመውሰድ የትምህርት ሥርዓቱን ለመጠበቅ አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስዱ ያሳሰበ ሲሆን፥ የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ካተሪን እንዳሉት በህፃናት ትምህርት ላይ ኢንቨስት ማድረግ ለወደፊቱ ልናደርጋቸው ከምንችላቸው ምርጥ ኢንቨስትመንቶች ውስጥ አንዱ መሆኑን ጠቁመዋል።

05 Sep 2025, 14:09