MAP

አንድ አረጋዊ ፍልስጤማዊ ከጋዛ ከተማ በስተ ምዕራብ የእርዳታ ምግብ ከሚሰጥበት ቦታ የተወሰነ ሩዝ ለማግኘት እየጠበቁ አንድ አረጋዊ ፍልስጤማዊ ከጋዛ ከተማ በስተ ምዕራብ የእርዳታ ምግብ ከሚሰጥበት ቦታ የተወሰነ ሩዝ ለማግኘት እየጠበቁ   (AFP or licensors)

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በጋዛ ያለው ረሃብ እየተባባሰ እንደሚሄድ አስጠነቀቀ

በጋዛ የተከሰተው ሰው ሰራሽ ረሃብ በመስከረም ወር መገባደጃ ላይ የበለጠ ሊስፋፋ እንደሚችል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ እርዳታ ኤጀንሲ ከፍተኛ ባለስልጣን አስታወቁ።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በጋዛ ከተማ እና በአካባቢው የተከሰተው ረሃብ “የሰብዓዊነት ውድቀት ማሳያ ነው” ሲሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ የገለጹ ሲሆን፥ በጋዛ ያለውን ረሃብ “እንቆቅልሽ ሳይሆን ፤ ሰው ሰራሽ ጥፋት፣ የሞራል መላሸቅ እንዲሁም የሰብዓዊነት ውድቀት ነው" ሲሉ ገልጸውታል።

የተቀናጀ የምግብ ዋስትና ደረጃ ምደባ (አይፒሲ) በመላው ጋዛ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ፍልስጤማውያን “በረሃብ፣ በቸነፈር እና በሞት” አሰቃቂ ሁኔታዎችን እያሳለፉ እንደሆነ የገለጸ ሲሆን፥ ይሄንን ተከትሎ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ኤጀንሲ ዋና ጸሃፊ ቶም ፍሌቸርን በመወከል ረዳታቸው የሆኑት ጆይስ ምሱያ የተቀናጀ የምግብ ዋስትና ደረጃ ምደባ የረሃብ ግምገማ ኮሚቴ ጋዛን አስመልክቶ ይፋ ያደረገውን መረጃ በመጥቀስ በአከባቢው ከሚቀጥለው መስከረም ወር ጀምሮ የከፋ ረሃብ ሊከሰት እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

ወይዘሮ ጆይስ በአሁኑ ወቅት በጋዛ ግዛት ውስጥ ረሃብ እየተከሰተ መሆኑን እና በሳምንታት ጊዜ ውስጥ ወደ ዴይር አል-ባላህ እና ካን ዩኒስ ሊስፋፋ እንደሚችል ያላቸውን ግምት ገልጸዋል።

በተባበሩት መንግስታት ግምት መሰረት በአሁኑ ጊዜ ከ 500,000 በላይ ሰዎች ለረሃብ እና ለድህነት የተጋለጡ ሲሆን፥ ይህ አሃዝ በሚቀጥለው ወር መጨረሻ ወደ 640,000 ከፍ ሊል እንደሚችል ገልጾ፥ ተጨማሪ 1 ሚሊዮን ሰዎች ‘በድንገተኛ አደጋ ደረጃ - 4’ ሥር እንደተመደቡ እና ከ390,000 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ‘በአስጊ ሁኔታ ደረጃ - 3’ ውስጥ እንደተካተቱ ተገልጿል።

“በእርግጥ በጋዛ ውስጥ ማንም ሰው በረሃብ ያልተነካ የለም” ያሉት ወይዘሮ ጆይስ፥ መግለጫው ከዚህ ቀደም ረሃብ እንደ አስከፊ ሁኔታ ተደርጎ ለምክር ቤቱ ከተሰጡ ማስጠንቀቂያዎች አንፃር የአሁኑ ከፍተኛ መባባስ ማሳየቱን የጠቆሙ ሲሆን፥ ከዚህም በተጨማሪ የተባበሩት መንግስታት ባለስልጣናት አሁን ላይ ሲተነበይ የነበረው ሁኔታ መድረሱን ተናግረዋል።

በተለይ በህፃናት ላይ ያለው ተጽእኖ በጣም ከባድ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፥ እ.አ.አ. በ 2026 ዓ.ም. አጋማሽ ላይ ከ132,000 ያላነሱ እድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት በከፍተኛ የተመጣጠነ ምግብ እጦት እንደሚሰቃዩ ይጠበቃል ተብሏል።

ከእነዚህም ውስጥ ከ43,000 በላይ የሚሆኑት በአሁኑ ወቅት ለሞት አደጋ እንደተጋለጡ እና ይህ አሃዝ ከቅርብ ወራት ወዲህ በሦስት እጥፍ ማደጉ የተገለጸ ሲሆን፥ ለነፍሰ ጡር እና ለሚያጠቡ ሴቶች የጉዳቱ መጠን ከ17,000 እስከ 55,000 ከፍ ሊል እንደሚችል ተገምቷል።

29 Aug 2025, 14:20