MAP

76 የሚሆኑ የቡኒያ ሀገረ ስብከት ካህናት “ተጠናክሮ የቀጠለው ሁከት ክልላችንን አደጋ ላይ እየጣለ ነው” በማለት መግለጫ አወጡ 76 የሚሆኑ የቡኒያ ሀገረ ስብከት ካህናት “ተጠናክሮ የቀጠለው ሁከት ክልላችንን አደጋ ላይ እየጣለ ነው” በማለት መግለጫ አወጡ  (AFP or licensors)

በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የሚገኙ ከ70 በላይ ካህናት ስለሰላም ጥሪ በማቅረብ መልእክት አስተላለፉ

በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ያለው ሰላም እያሽቆለቆለ ባለበት በአሁኑ ወቅት የቡኒያ ሀገረ ስብከት ካህናት ተጠናክሮ የቀጠለው ብጥብጥ ክልላቸውን አደጋ ላይ እየጣለ መሆኑን በመጥቀስ መግለጫ አውጥተዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና በሩዋንዳ መካከል ያለው የሰላም ሁኔታ በቅርቡ መሻሻሎችን አሳይቶ የነበረ ቢሆንም አሁንም ድረስ በአንዳንድ አከባቢዎች ውጥረቱ ከፍተኛ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፥ ይሄንን በማስመልከት 76 የሚሆኑ የቡኒያ ሀገረ ስብከት ካህናት ነሐሴ 14 ቀን 2017 ዓ.ም. በአከባቢው ተጠናክሮ የቀጠለው ሁከት ክልሉን አደጋ ላይ እየጣለ መሆኑን በመጥቀስ መግለጫ ማውጣታቸው ተገልጿል።

የቫቲካን የዜና ወኪል የሆነው ፊደስ ኒውስ እንደዘገበው ቡኒያ በኮንጎ ምሥራቃዊ ክፍል የምትገኘው የኢቱሪ ዋና ከተማ ስትሆን፥ በተለያዩ ታጣቂ ቡድኖች መካከል በተፈጠረው ግጭት ከፍተኛ የጸጥታ ስጋት ውስጥ መግባቷ እና እ.አ.አ. ከግንቦት 2021 ዓ.ም. ጀምሮ በከበባ ውስጥ እንደምትገኝ ገልጿል።

ብጥብጥ ክልሉን ያወድማል
በአካባቢው በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈጸመው የኃይል እርምጃ እና ግድያ በመቀጠል በካቶሊክ ማህበረሰቦች ላይ ተጽእኖ ማሳደሩ የተነገረ ሲሆን፥ በቅርብ ጊዜ ከተከሰቱት ክስተቶች ውስጥ እንኳን ነሃሴ 13 እና 14 ምሽት ላይ ታጣቂ ወታደሮች ወደ ቅዱስ ኪዚቶ ጸሎት ቤት ውስጥ መግባታቸው እንደሚታወስ እንዲሁም ታጣቂዎቹ ቤተ መቅደሱን ከፍተው በመግባት ቅዱስ ቁርባኑን መሬት ላይ እንደጣሉ እና የጸሎት ቤቱን መስኮቶችን በመስበር ካህናቱን ሲያስፈራሩ እንደነበር ተገልጿል።

እንደ ካህናቱ ገለጻ በአካባቢው የሕግ አስከባሪ መኮንኖች ቢኖሩም እንኳን፣ ይህ ጥቃት በአከባቢው ከተከሰቱት በርካታ ጥቃቶች መካከል አንዱ መሆኑን አመላክተዋል።

ካህናቱ በማከልም ከበርካታ ክስተቶች ውስጥ ሐምሌ 11 በሎፔ መንደር ውስጥ በሚገኘው አንድ ደብር ላይ በተከሰተው እና ሐምሌ 19 ኮማንዳ አውራጃ ውስጥ በሚገኝ ሌላ ደብር ምሽት ላይ በተከሰተ ጥቃት ወደ 50 የሚጠጉ ሰዎች መገደላቸው እና ቢያንስ 40 የሚሆኑ ወጣቶች ታግተው መወሰዳቸውን መግለጫው ይፋ አድርጓል።

ኢፍትሃዊ ድርጊቶች
የሀገረ ስብከቱ ካህናት በመግለጫቸው ቀውሱ ወደሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች እየተስፋፋ መሄዱን እና በዚህም ሳቢያ በርካታ ሰዎች መጠለያ ፍለጋ ከቤታቸው እየተሰደዱ መሆናቸውን ያመላከቱ ሲሆን፥ የጸጥታ ሃይሉ ውጤታማነት ላይ ስጋቶች መኖሩን በመጥቀስ፥ ብዙውን ጊዜ የጸጥታ አካላቱ አቅመ ቢስነታቸውን እና ተባባሪነታቸውን ለመደበቅ ብሎም የአካባቢ ወጣቶችን የጸጥታ መደፍረስ መንስኤ አድርጎ በማቅረብ ሁኔታውን የትንኮሳ እና የበቀል እርምጃዎች ናቸው በሚሉ ቃላት ጥቃቶቹን የማሳነስ እና የማቃለል ሁኔታዎች እንዳሉ ገልጸዋል።

የሀገረ ስብከቱ ካህናት መግለጫ መሰረት ከሁሉ የከፋው ነገር የሕግ አስከባሪ አካላት ከሚሊሻዎች ጋር በመተባበር ለነፍስ ግድያ፣ በሕገወጥ መንገድ የመት ተግባር፣ አካለ መጠን ያልደረሱ ሕፃናትን ሳይቀር በዘፈቀደ በማሰር እና የንጹሐን ዜጎችን ንብረት በመዝረፍ ተጠያቂ መሆናቸውን አስረድተዋል።

የተሳሳቱ ውንጀላዎች
መግለጫው በመቀጠል ቡኒያ ከተማ የሚገኙ ካህናት የኢቱሪ ወታደራዊ ባለስልጣናት በቤተክርስቲያኗ ላይ የፈጸሙትን “የስም ማጥፋት እና የቃላት ዛቻ” ማውገዛቸውን በማስታወስ፥ የአከባቢው ባለስልጣናት ቤተክርስቲያን ከሚሊሻ አባላቱ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ግለሰቦች 'ትደብቃለች' ብለው እንደሚያስቡ በመግለጫቸው ገልጸዋል።

ካህናቱ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በትንቢታዊ ተልእኮዋ ምክንያት ከብዙዎቹ ተቋማት መካከል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያወጀው እና ከኮዴኮ ጋር በወንጀል ተባባሪነት እየሰራ ከሚገኘው ወታደራዊ አካል የተቀነባበረ ጥቃት ኢላማ ሆና እንደነበር ግልጽ መሆኑን በማስታወስ እነዚህን የሃሰት ውንጀላዎች ውድቅ አድርገዋል።

ሚሊሻዎቹ ከመደበኛው ታጣቂ ወታደሮች ጋር በመሆን በሎፓ በሚገኝ ደብር ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ያስታወሰው መግለጫው፥ ከበባው ቀዳሚ እና አስፈላጊው ተግባሩ የነበረውን “የሚታይ እና ተጨባጭ የሆነ ሰላምን ማስፈን እንዳልቻለ” በመግለጽ፥ በተቃራኒው ታጣቂ ቡድኖች መስፋፋታቸው ብቻ ሳይሆን በቁጥርም በጦርም ጭምር መጠናከራቸውን ካህናቱ በመግለጫቸው አመላክተዋል።

25 Aug 2025, 16:31