በሄይቲ ከታገቱት ሰዎች መካከል አንድ አየርላንዳዊ ሚስዮናዊ እንደምትገኝበት ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
በሄይቲ ዋና ከተማ ፖርት ኦው ፕሪንስ አቅራቢያ የሚገኘውን የቅድስት ሄለን ህጻናት ማሳደጊያን የምታስተዳድረው ጌና ሄራቲ እሁድ ዕለት ከሶስት ዓመት ህፃን እና ከሰባት የሥራ ባልደረቦቿ ጋር ታፍና መወሰዷ ከአከባቢው የወጡ ምንጮች አረጋግጠዋል።
የህጻናት ማሳደጊያው ከ200 በላይ ህጻናትን የሚንከባከብ በደግነት፣ በፍቅር እና ትጋት በተሞላበት ሥራው በህብረተሰቡ ዘንድ የሚታወቅ ተቋም ሲሆን፥ የአከባቢው ባለሥልጣናት ጉዳዩን አስመልክተው እንደተናገሩት አጋቾቹ የውጪውን የአጥር ግንብ ሰብረው ወደ ግቢው ዋና ሕንፃ በማምራት በጥንቃቄ የተቀናጀ እገታ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
ጌና ሄራቲ እ.አ.አ. ከ 1993 ዓ.ም. ጀምሮ በሄይቲ በሚስዮናዊነት አገልግሎት ላይ የምትገኝ ወጣት ስትሆን፥ ብዙ ጊዜ ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ ህጻናትን በመርዳት በአከባቢው ዘንድ ትታወቃለች።
በአከባቢው ያለው የሰላም ሁኔታ ለዓመታት እያሽቆለቆለ መምጣቱን፣ ቀውሱንና ሊያስከትል የሚችሉትን አደጋዎች ብትገነዘብም በአከባቢው በጀግንነት በመቆየት ተልዕኮዋን ስትወጣ የነበረ ሲሆን፥ ከመታገቷ በፊት በድፍረት በሥፍራው የመቆየት ውሳኔዋን ስትገልጽ “እዚህ የመቆየቴ ምክንያት ህፃናቱ ናቸው፥ ምንም አይነት የመልቀቅ ሀሳብ ዬለኝም” በማለት ቁርጠኝነቷን ገልፃ እንደነበር ተነግሯል።
በምዕራቡ ንፍቀ ክበብ እጅግ በጣም ደሃ የሆኑ ህዝቦች የሚኖሩባት ሄይቲ ሕገ-ወጥነት እና የቡድን ጥቃት ከተንሰራፋባት ዓመታት የተቆጠሩ ሲሆን፥ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከሰማንያ በመቶ በላይ የሚሆነው የዋና ከተማዋ ፖርት አው ፕሪንስ አከባቢዎች በጎዳና ወንበዴዎች እና በተደራጁ ወንጀለኞች ቁጥጥር ሥር መሆኑን ይፋ አድርጓል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ባሳለፍነው ጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ ባደረጉት ንግግር ዸም አቀፉ ማህበረሰቡ ለሄይቲ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ የሚያደርገውን ድጋፍ ማጠናከር ካልቻለ በቅርቡ የሀገሪቱ ዋና ከተማ ሙሉ ለሙሉ በወሮበሎች የምትተዳደር ይሆናል ሲሉ ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል።
አብዛኛውን ጊዜ ለጠመንጃ እና ሌሎች መሳሪያዎች መግዣ የሚሆን ገንዘብ ለማግኘት ታልሞ የሚፈጸመው የጠለፋ ወንጀል በሄይቲ የዕለት ተዕለት የተለመደ ተግባር ሲሆን፥ የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት የሄይቲ ባለስልጣናት የሀገሪቱን በርካታ ግዛቶች ከተቆጣጠሩት የወንጀለኛ ቡድኖች ጋር የሚያደርጉትን ውጊያ ለመደገፍ ከተለያዩ ሀገራት የተውጣጡ የፖሊስ አባላት እንዲሰማሩ ፈቃድ መስጠቱን ተከትሎ የተለያዩ ሃገራት፣ በተለይም የካሪቢያን ሃገራት ደካማ የጸጥታ ሃይሏን ለማጠናከር ጸጥታ አስከባሪ ፖሊሶችን ወደ ሄይቲ የላኩ ቢሆንም፥ ነገር ግን ከትላልቅ ሃገራት ውስጥ አንድም ሀገር የሰላም ማስከበር ዘመቻ ለመመስረት የሰራዊት ማጠናከሪያ እንዳላቀረበ እየተነገረ ይገኛል።
ሄይቲ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ለማካሄድ አቅዳ የነበረ ቢሆንም፥ ሆኖም ግን በሃገሪቷ ውስጥ በሚታየው ከፍተኛ አለመረጋጋት ምክንያት አሁን ላይ የሚቻል ነገር እንዳልሆነ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ።