አየርላንዳዊው ደራሲ ኮለም ማካን 'በሁለት ሰዎች መካከል ያለው ርቀት ሁሌም ታሪክ ብቻ ነው' ማለታቸው ተገለጸ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
“አንድ ታሪክ ከየት እንደሚጀምር ባላውቅም፥ ነገር ግን ለመጀመር አንድ ሰው ዝግጁ መሆን እንዳለበት እና ለተቃርኖዎች ክፍት መሆን እንዳለበት አውቃለሁ” ያሉት ትውልደ አየርላንዳዊው ኮለም ማካን፥ የምንኖረው እርግጠኝነት በጎደለው ዸም ውስጥ እንደሆነ እና ሁሉም ሰው ሁል ጊዜ እንደሚያውቅ፣ ሁሉንም ነገር እንደሚረዳ እርግጠኛ በሆነበት ዸም ውስጥ እንደምንኖር ገልጸው፥ “እኔ ግን በሁለት ሰዎች መካከል ያለው ርቀት ሁልጊዜ ታሪክ ብቻ ነው ብዬ አስባለሁ” ብለዋል።
የአየርላንድ ተወላጅ የሆኑት አሜሪካዊ ደራሲ ኮሎም ማካን አንድ ታሪክ የት እና እንዴት እንደሚጀመር ተጠይቀው፥ የአንድ ታሪክ ዋና ፍሬ ነገር በጣም አስፈላጊ የሆነውን የሌላን ሰው ህልውና የምናውቅበት እና እሱም የእኛን መኖር የሚያውቅበት አንድ የሆነ እውነት ማግኘት እንደሆነ የገለጹት ደራሲው፥ ‘የግድ እርስ በርስ መዋደድ ባይኖርብንም፥ ነገር ግን እርስ በርሳችን መግባባት ካልቻልን ያኔ ተፈርዶብናል’ በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።
ደራሲው ይሄን የተናገሩት ነሃሴ 18 በሪሚኒ ከተማ በተካሄደው ስብሰባ አራተኛው ቀን ላይ ሃይለኛ እና አነቃቂ ክስተቶች በነበሩበት ወቅት ሲሆን፥ ከአቶ ማካን በተጨማሪ ስፔናዊው ጸሃፊ ጃቪየር ሰርካስ እና የቅድስት መንበር የመገናኛ ጽ/ቤት ሃላፊ ዶክተር ፓውሎ ሩፊኒ የተገኙበት ሲሆን፥ በጣሊያናዊቷ ጋዜጠኛ ሊንዳ ስትሮፓ አወያይነት የተመራው የውይይት መድረክ ኅብረትን ሊገነባ የሚችል የግንኙነት መስመሮችን ለመፈለግ ታልሞ እንደተካሄደ ተነግሯል።
በግጭቶች እና በጽንፈኝነት፣ በፕሮፓጋንዳ እና በውሸት በተሞላው ዸም ውስጥ የደራሲያኑ ሥራ ቀላል እንዳልነበረ የተገለጸ ሲሆን፥ አሁንም በተስፋ ውስጥ ሆነን መግባባት እንችል እንደሆነ የተጠየቁት ዶክተር ሩፊኒ በበኩላቸው ‘ማድረግ እንችላለን ብቻ ሳይሆን ማድረግ አለብን’ ካሉ በኋላ፥ ነገር ግን ምንም እንኳን አብዛኛውን ጊዜ በክፋት ስለታወርን ቀላል ባይሆንም በመጀመሪያ ደረጃ ተስፋን መገንባት እንደሚገባ ገልጸው፥ በጋዜጦች፣ በቴሌቪዥን እና በማህበራዊ ድህረ ገፆች ላይ መጥፎ የሆኑ ነገሮች ስለሚበዙ እና ስለ መልካም ነገር የሚናገሩት ታሪኮች የተቀበሩ ቢመስሉም የእኛ ተግባር መልካም ነገር መፈለግ፣ መናገር እና ምንም ሊሠራ ወይም ተስፋ ሊደረግ የማይችል በሚመስልበት ጊዜ እንኳን ታሪኮችን ማካፈል ነው ብለዋል።
“ይህ ሁሉ በእርግጠኝነት ለካቶሊኮች በተለይም ለመላው ዸም ይጠቅማል” ያሉት ዶክተር ሩፊኒ፥ ካቶሊክ መሆን ማለት በድንበር ውስጥ ታጥሮ መኖር እንዳልሆነ አስረድተዋል።
ስፔናዊው ደራሲ አቶ ሰርካስ በበኩላቸው ወደ ዋናው ነገር ተመልሶ እውነትን መናገር እንደሚገባ እና ይህንንም ማድረግ ያለብን በወንጌል አስተምህሮ ምክንያት እንደሆነ ጠቁመው፥ እውነት ነጻ እንደሚያወጣ፣ በአንፃሩ ውሸት ባሪያ እንደሚያደርግ፥ ዛሬ ባለንበት ዘመን ውሸት በፖለቲካ፣ በህዝብ ህይወት ውስጥ እና በሁሉም ቦታ በከፍተኛ ደረጃ የመሰራጨት ሃይል እንዳለው አመላክተዋል።
አቶ ሰርካስ ፕላቶን ጨምሮ ሁሉም ሰው እንደሚስማማበት የሰው ልጅ የመፃፊያ ማሽን ሲፈጥር ያሰብነውን ሁሉ ያስረሳናል ተብሎ እንደነበር፤ አስታውሰው፥ የማተሚያ ማሽን ፈጠራ ላይም እንደዛው እንደነበር፤ ከዚያም ቴሌቪዥን ሲፈጠር ሰዎች ባህል ይጠፋል ብለው እንደነበር በማስታወስ ዋናው ችግር ቴክኖሎጂ እንዳልሆነ አስረድተው፥ ከነዚህ ሁሉ ስጋቶች ውስጥ አንዳቸውም እንዳልተከሰቱ፥ ምክንያቱም ሁሉም ነገር ቴክኖሎጂን የምንጠቀምበት መንገድ ላይ የተመሰረተ እንደሆነ፥ በተለይም ዛሬ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ወይም ሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘመን ይህ ነገር ወሳኝ እንደሆነ ገልጸዋል።
አቶ ማካን በበኩላቸው ሁልጊዜ የምንኖረው በአስቸጋሪ ጊዜያት ውስጥ እንደሆነ፥ ነገር ግን ይህ በተለይ ውስብስብ እንደሚመስል ምክንያቱም ደግሞ አንዳንድ ችግሮችን የመፍታት ሂደት በጣም አስቸጋሪ በመሆኑ እንደሆነ አምነው፥ በዚህም ምክንያት መረጋጋትን መማር፣ እንዲሁም በጥሞና እና በፈውስ ላይ ማተኮር እንዳለብን መክረዋል።
ይህም ሊሆን የሚችለው በጋራ ዕውቀት ብቻ እንደሆነ፥ ሌላውን ማዳመጥ ቀላል ባይሆንም ነገር ግን መልካም እንደሆነ፥ ይህንንም ከእኛ በሃሳብ ከሚለዩት ጋር ማድረግ እንዳለብን፣ ከሁሉም በላይ ግን በራሳችን ማህበረሰብ፣ ቤተሰብ፣ ትምህርት ቤቶች እና በዩኒቨርሲቲዎች መለማመድ እንዳለብን አሳስበዋል።
በዚህ ወቅት ቤተክርስቲያን አካባቢያዊ እና ዸም አቀፋዊ ስለሆነች ሚናዋ ወሳኝ እንደሆነ የጠቆሙት አየርላንዳዊው ደራሲ፥ ነፍስኄር ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ይህንን የግንኙነት፣ የተግባቦት እና የማዳመጥ መልዕክት አስተላልፈውልን እንደነበር አስታውሰዋል።
አቶ ሰርካስ በማከልም ቤተክርስትያን በአሁኑ ወቅት የሥነ ቋንቋ ውስንነት ስላለባት ቋንቋዋን መቀየር እንዳለባት ገልጸው፥ ክርስትና በዸም ውስጥ ያለውን አኗኗር ስለለወጠ አብዮታዊ ናት ማለት እንችላለን ካሉ በኋላ፥ በተቃራኒው ግን ቤተክርስቲያን የክርስቶስን ማህበራዊ አብዮት ማስተዋወቅ እንዳቃታት፣ የቤተክርስቲያኑ ቋንቋ ማርጀቱን እና ማራኪ አለመሆኑን ገልጸዋል።
ዶክተር ሩፊኒ በዚህ ጉዳይ ሙሉ በሙሉ እንደማይስማሙ ገልጸው፥ ምንም እንኳን የቋንቋ ችግር መኖሩ ባይካድም ነገር ግን ቋንቋ ከነገሮች በኋላ እንደሚመጣ፥ ቤተ ክርስቲያን በኅብረት የተገነባች እንደሆነ፣ ይህ ኅብረት ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን ብቻ እንደማይመለከት አብራርተው፥ እኛ ሁላችንም የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ማመንን እንደሚመለከት እና በዚህ መንገድ ከኖርን ቃላቶቻችን ትርጉም ያለው እንደሚሆን ገልጸዋል።
ሁለት ሰዎች እርስ በርሳቸው እንደሚዋደዱ ቢናገሩ እና ነገር ግን በተግባር ካላሳዩ እነዚህ ቃላት ትርጉም አልባ እንደሆኑ ገልጸው፥ ቤተክርስቲያን የኅብረትን ውበት እንደገና ማግኘት ያለባት ዋና ነጥቡ ይህ ነው ብለዋል።
አቶ ሰርካስ አስቸጋሪው ነገር ካቶሊኮች እንኳን ቢሆኑ ቤተ ክርስትያን ምን ማለት እንደሆነ ብዙ ጊዜ እንደማይረዱ ጠቁመው፥ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ መሠረታዊ ቃላቶች አንዱ የሆነውን ‘ሲኖዶሳዊነት’ ብዙ ሰው በተሳሳተ መንገድ እንደሚረዳ አንዱ ተጨባጭ ምሳሌ ነው ካሉ በኋላ፥ ‘ቤተክርስቲያንም ይህ ምን ማለት እንደሆነ ለማስረዳት እንዳልቻለች’ እና ይህም በመሆኑ ከብጹእነታቸው መማር ያለብን በጣም ጠቃሚ ነገር ጎሎናል በማለት ሃሳባቸውን አካፍለዋል።
ስፔናዊው ጸሐፊ ምንም እንኳን እሳቸው ‘ኢ-አማኝ’ ቢሆኑም ቤተ ክርስቲያኒቱ የርኅራኄ ተግባር በማሳየት በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ የሲኖዶሳዊነት ጉዞ እንዲካፈሉ እና ስለ ጉዳዩ መጽሐፍ እንዲጽፉ እንደጋበዘቻቸው ገልጸው፥ በዸም ዙሪያ ያሉ በተለይም እንደ ጣሊያን፣ ስፔን እና አየርላንድ ባሉ የካቶሊክ አገሮች ውስጥ እንዲህ ዓይነቱን መጽሐፍ ለመጻፍ በትክክል ምን እየተፈጠረ እንዳለ፣ እነዚህ ሰዎች እነማን እንደሆኑ፣ ቤተክርስቲያን ዛሬ ላይ ምን እየሰራች እንደሆነ ማወቅ እንደሚያስፈልጋቸው እና ትልቅ ሥራ ከእርሳቸው እንደሚጠበቅ ተናግረው፥ ይህ ለቤተክርስቲያን አደጋ ቢሆንም ለእኔ ግን ትልቅ ስራ ነበር ብለዋል።
በጣም ብዙ ሰዎች፣ በመላው ዸም በቤተክርስቲያኒቱ እና በቫቲካን ላይ ጭፍን ጥላቻ እንዳላቸው ገልጸው፥ ‘መጀመሪያ ይሄን መጽሃፍ ለማዘጋጀት እኔም ጭፍን ጥላቻዬን ማስወገድ ነበረብኝ’ ካሉ በኋላ፥ “እኛ ጸሐፊዎች የምናደርገው ይህንን ነው፥ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዳየነው እውነታውን እናስወግዳለን፥ ስለዚህም ሁሉም ነገር አስገራሚ ይሆናል” ያሉት ጸሃፊው፥ ይህም በመሆኑ ሁሉም ነገር በትክክል እንዲከናወን “እኛ ጸሃፊዎች ትህትና ሊኖረን ይገባል” በማለት ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል።
“የደራሲዎች ወይም ገጣሚዎች ሚና ልዩ መብት ሊሰጠው አይገባም” ያሉት አቶ ማካን፥ ጋዜጠኞች ትልቅ ሚና፣ ዕድል እና ኃላፊነት እንዳላቸው፥ “ነገር ግን ጥንቃቄ መደረግ ያለበት ነገር እውነታዎች ቅጥረኞች ስለሆኑ በቀላሉ ይሸጣሉ” ካሉ በኋላ፥ በመጨረሻም አንድ መገንዘብ ያለብን በእውነታዎች ላይ ያልተመሠረቱ ነገሮች እንዳሉ ብሎም ፍቅር፣ ኩራት፣ መስዋዕትነት እና ዓመፅ መኖራቸውን ማስተዋል እንዳለብን ገልጸው፥ ይሄንንም ለማድረግ ጋዜጠኛ፣ ደራሲ እና ጸሃፊ በራሱ ተዘግቶ ወይም ከሌሎች ተነጥሎ መኖር ዬለበትም ብለዋል።
ከዚህ ይልቅ ወደ ጎዳና መውጣት፣ ሰዎችን ማግኘት፣ ትክክለኛ ታሪኮችን ሊነግራቸው በማይፈልግበት ጊዜም እንኳን ቢሆን መናገር እንዳለበት ጠቁመው፥ ቀላል የሆኑ ነገር ግን የሰው ልጅ መልካምነት የሚገልጹ ታሪኮችን እንኳን ለመንገር ጥረት ማድረግ ይገባል በማለት አጠቃለዋል።