የኮሎምቢያ ብፁአን ጳጳሳት በሴናተር ሚጌል ኡሪቤ ሞት የተሰማቸውን ሃዘን ገለጹ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ግንቦት ወር መጨረሻ ላይ በኮሎምቢያ መዲና ቦጎታ በተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ ላይ በተተኮሰባቸው ጥይት ቆስለው የነበሩት የኮሎምቢያው ሴናተር እና ዕጩ ፕሬዝዳንት ሚጌል ኡሪቤ ሆስፒታል ውስጥ ህክምና ሲደረግላቸው ቆይተው ሰኞ ዕለት በ 39 ዓመታቸው ህይወታቸው ማለፉን ቤተሰቦቻቸው አስታውቀዋል።
ሟቹ ሴናተር ኡሪቤ ግንቦት 30 ቀን 2017 ዓ.ም. በሚቀጥለው ዓመት ለሚካሄደው ፕረዚዳንታዊ ምርጫ የዴሞክራቲክ ሴንተር ፓርቲን ወክለው የምርጫ ዘመቻ ሲያካሂዱ በነበረበት ወቅት በአስራ አምስት ዓመቱ ታዳጊ ታጣቂ ሁለት ጊዜ ጭንቅላታቸው ላይ፣ አንድ ጊዜ ደግሞ እግራቸው ላይ በጥይት የተመቱ ሲሆን፥ ተጠርጣሪው በጥይት ተመትቶ አምልጦ የነበረ ቢሆንም ከጊዜ በኋላ በቁጥጥር ስር መዋሉ ተነግሯል።
ኮሎምቢያዊው ሴናተር እና ፕሬዝዳንታዊ እጩ ሚጌል ኡሪቤ ቱርባይ ሆስፒታል በነበሩበት ወቅት ለበርካታ ጊዜ ቀዶ ጥገናዎች ተደርጎላቸው በአስጊ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ ሲሆን፥ ባለቤታቸው ማሪያ ክላውዲያ ከሁለት ወራት በፊት በከባድ ሁኔታ የቆሰሉትን የፖለቲከኛውን ሞት ካሳወቀች በኋላ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ “ያለአንተ እንዴት መኖር እንደምችል መንገድ እንዲያሳየኝ እግዚአብሔርን እጠይቃለሁ” በማለት ጽፋለች።
በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለሴናተሩ በትጋት ሲጸልዩ እንደነበር የተገለጸ ሲሆን፥ ህልፈታቸውን ተከትሎ የኮሎምቢያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ብፁአን ጳጳሳት ጉባኤ የሐዘን መግለጫ አውጥቷል።
“ከመላው ቤተሰባቸው ጋር ያለንን አጋርነት ለመግለጽ እንፈልጋለን” ያለው የብፁአን ጳጳሳቱ መግለጫ፥ በክርስቲያናዊ ተስፋ አምላክ መጽናናቱን እንዲሰጣቸው ያላቸውን ምኞት ገልጸው፥ የኮሎምቢያ ባለስልጣናት የግድያውን ምርመራ እንዲከታተሉ አሳስበዋል።
'ተስፋችን ከእኛ እንዲሰረቅ መፍቀድ ዬለብንም' በማለት ለሃገሪቱ ህዝብ መልዕክቱን ያስተላለፈው መግለጫው፥ ህዝቡ በሰላማዊ መንገድ ምላሽ እንዲሰጥ እና እንደ ሀገር አንድ የሚያደርጉትን መርሆችን እና እሴቶችን መጠበቅ እንደሚገባ መክረዋል።
ብፁአን ጳጳሳቱ በመግለጫቸው ነፃነት እና መከባበር የሁሉም ኮሎምቢያውያን ሁለንተናዊ የሰው ልጅ እድገት ዋስትና ይሆን ዘንድ ሀገሪቱ “ነፃነት እና ስርዓት” የሚለውን መሪ ቃል እንድታከብር አሳስበዋል።
ከተገደሉት ሴናተር ጋር ምንም ዝምድና የሌላቸው የቀድሞው የኮሎምቢያ ፕሬዝዳንት አልቫሮ ኡሪቤ “ሃገሪቷ የነበራትን ተስፋ ገድለዋል፣ የሚጌል ትግል የኮሎምቢያን መንገድ የሚያበራ መብራት ይሆናል” በማለት ሃዘናቸውን ገልጸዋል።
ከዓመታት በፊት ጋዜጠኛዋ የሚጌል እናት ዲያና ቱርባይ፣ ፓብሎ ኤስኮባር በተባለ ታጣቂ ታግተው የሃገሪቱ ፖሊስ ባደረገው ያልተሳካ የማዳን ሙከራ ወቅት ህይወታቸው ማለፉ ይታወሳል።
ሟቹ ሚጌል በህይወት እያሉ እናታቸው የነበራቸውን ድፍረት ለመጪው የኮሎምቢያ እድገት ተግተው ለመስራት እንዳነሳሳቸው ብዙ ጊዜ ደጋግመው ሲናገሩ እንደነበር ተገልጿል።
ምንም እንኳን ተጠርጣሪው እና በርካታ ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው ቢሆንም፣ አሁንም ድረስ እጩ ፕረዚዳንቱ የተገደሉበት ምክንያት ግልፅ እንዳልሆነ ተነግሯል።