በጋዛ ሆስፒታል ላይ በተደረገ የአየር ጥቃት ሰባት ሰዎች መሞታቸው ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የእስራኤል አየር ሃይል እሁድ እለት በጋዛ ከተማ በሚገኘው አል- አህሊ ሆስፒታል ላይ ባደረሰው ጥቃት ቢያንስ ሰባት ሰዎች መሞታቸውን የአካባቢው የጤና ባለስልጣናት ያስታወቁ ሲሆን፥ ጥቃቱ የደረሰው የእስራኤል ጦር በጋዛ ከተማ የሚኖሩ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ፍልስጤማውያንን በግዳጅ አፈናቅሎ በደቡባዊ ጋዛ በሚዘጋጅ ካምፕ ለማስገባት ዕቅድ በያዘበት ወቅት እንደሆነ እና እየተባባሰ ያለው የሰብአዊ ሁኔታዎች በዸም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ስጋትን መፍጠሩ ተገልጿል።
ጦሩ የጋዛ ከተማን የሚወርበት የጊዜ ሰሌዳ ባያስቀምጥም፥ በራፋህ ከተማ ፍርስራሽ ላይ ይቋቋማል የተባለው ይህ ካምፕ በመጀመሪያ 600 ሺህ ፍልስጤማውያን በመቀጠልም አጠቃላይ የጋዛን ሕዝብ፣ 2.1 ሚሊዮን የሚያኖር እንደሆነ እና ፍልስጤማውያኑ አንዴ ወደ ካምፑ ከገቡ መውጣት እንደማይፈቀድላቸው ተገልጿል።
የእስራኤል ወታደራዊ ሃይል በበኩሉ ፍልስጤማዊያኑን የማዛወር ጥረቱ ተጠናክሮ በቀጠለው የውጊያ ዘመቻ ሲቪሎችን ለመጠበቅ አስፈላጊ እርምጃ መሆኑን ገልጿል።
ነገር ግን የረድኤት ድርጅቶች እና የመብት ተሟጋች ድርጅቶች እንዲሁም በአብዛኛው ታዛቢዎች “ማጎሪያ ቦታዎች” እየተባሉ የሚጠሩት ደቡባዊ ዞኖች የተጨናነቁ፣ መሰረተ ልማት የሌላቸው እና ለቦምብ ጥቃት የተጋለጡ መሆናቸውን ያስጠነቅቃሉ።
እስራኤል ነሃሴ 11 ሆስፒታሉ ላይ ያደረችው ጥቃት በሲቪል ዜጎች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት እንደጨመረው እና የህክምና መሰረተ ልማቶች ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንዳስገባ የተገለጸ ሲሆን፥ የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች በፍርስራሹ ውስጥ የተረፉ ሰዎችን እየፈለጉ በነበረበት ወቅት ሁከት መፈጠሩን የዓይን እማኞች ገልጸዋል።
ከእሁዱ ጥቃት ቀደም ብሎ እስራኤል ዘይቱን በተባለችው የጋዛ ከተማ ላይ እየፈጸመ ባለው ለቀናት በቀጠለ ከፍተኛ ጥቃት ‘አሰቃቂ ሁኔታ መፍጠሩን’ እና በሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን መፈናቀላቸውን በሐማስ የሚመራው የከተማዋ ማዘጋጃ ቤት የገለጸ ሲሆን፥ የእስራኤል ጦር ቅዳሜ ዕለት ብቻ ባደረሰው ጥቃት ቢያንስ 40 ፍልስጤማውያን መገደላቸውን የጋዛ ሲቪል መከላከያ ኤጀንሲ አስታውቋል።
ይህ በእንዲህ እያለ እሁድ ዕለት የጋዛ ጦርነት እንዲቆም እና በሐማስ የተያዙ ታጋቾች እንዲለቀቁ ስምምነት ላይ እንዲደረስ ለመጠየቅ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ እስራኤላውያን በቴልአቪቭ 'ሆስቴጅ' በተሰኘው አደባባይ የወጡ ሲሆን፥ የአደባባይ ተቃውሞው አዘጋጆች የእስራኤል መንግሥት ጋዛን ለመውረር የያዘው ዕቅድ በሐማስ ተይዘው ያሉ 20 የሚሆኑ ታጋቾችን አደጋ ላይ ይጥላል ብለዋል።
ይህ አገራዊ የስራ ማቆም አድማን ያሰናዱት የታጋቾች ቤተሰቦች እና የጦርነቱን መስፋፋት የሚቃወሙ አካላት እንደሆኑ የተገለጸ ሲሆን፥ ኢናቭ ዛንጋውከር የተሰኙ ልጃቸው የታገተባቸው እናት "ሁሉን አቀፍ እና ተጨባጭ የሆነ ስምምነት እንዲደረግ እንዲሁም ጦርነቱ እንዲቆም" እየጠየቁ እንደሆነ ገልጸዋል።
የእስራኤል ጦር ድንኳኖች በእርዳታ ኤጀንሲዎች አማካኝነት ወደ ጋዛ እንዲገቡ መፍቀድ እንደሚጀምር ያስታወቀ ሲሆን፥ “ህዝቡን ከጦርነት ቀጣና አውጥቶ ወደ ደቡባዊ ጋዛ ሰርጥ ለማስፈር በሚደረገው ዝግጀት የድንኳን እና መጠለያዎች አቅርቦት እንደገና ይቀጥላል” ሲል የእሰራኤል ወታደራዊ አካል ኮጋት ገልጿል።
የእስራኤል መንግስት ጋዛ ከተማን ለመቆጣጠር ያቀደውን እቅድ በመቃወም የአንድ ቀን አጠቃላይ የሥራ ማቆም አድማ የተካሄደው የእስራኤል የጦር ካቢኔ የጋዛን ከተማ ለመውረር እንዲሁም ፍልስጤማውያኑን የማፈናቀል ውሳኔን ካፀደቀ በኋላ እንደሆነ እና ይህ የእስራኤል እርምጃ የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታ ምክር ቤት ጨምሮ በበርካታ አገራት ውግዘት እንደደረሰበት ተነግሯል።
የዚህ የአደባባይ ተቃውሞ አካል በሆነው ብሄራዊ የስራ ማቆም አድማ መንገዶች፣ ቢሮዎች እንዲሁም በአንዳንድ አካባቢ የሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች የተዘጉ ሲሆን፥ ከዚህ የአደባባይ ተቃውሞ ጋር ተያይዞ ወደ 40 የሚጠጉ ሰዎች መታሰራቸውን ከአከባቢው የሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ይሄንን የአደባባይ ተቃውሞ "የሃማስን አቋም የሚያጠናክር" እንዲሁም የታጋቾችን መለቀቅ የሚያጓትት” ሲሉ ተችተዋል።
በዚህ አውዳሚ ጦርነት ከ2.1 ሚሊዮን ከሚሆነው የጋዛ ሕዝብ መካከል 90 በመቶ ወይም 2.1 ሚሊዮን ሕዝብ የተፈናቀለ ሲሆን፥ አንዳንዶች በተደጋጋሚ እንደተናፈናቀሉ እና በርካታዎቹ በተጨናነቀ እና በአስከፊ ሁኔታ ውስጥ ነው እንደሚኖሩ መረጃዎች ያሳያሉ።
የጦርነቱ መስፋፋት በሀማስ ቁጥጥር ስር የሚገኙትን የእስራኤላውያንን ህይወት የበለጠ አደጋ ላይ ይጥላል የሚሉ የታጋቾች ቤተሰቦች እና በርካታ ተቋማት እስራኤል ያቀደችውን ወረራ በአስቸኳይ እንድታቆም ጠይቀዋል።