MAP

ሰብአዊ እርዳታን የጫነ የጭነት መኪና በግብፅ እና በጋዛ ሰርጥ መካከል ባለው ራፋህ ድንበር አቅራቢያ - ነሃሴ 5 ቀን 2017 ዓ.ም. ሰብአዊ እርዳታን የጫነ የጭነት መኪና በግብፅ እና በጋዛ ሰርጥ መካከል ባለው ራፋህ ድንበር አቅራቢያ - ነሃሴ 5 ቀን 2017 ዓ.ም.  

በጋዛ ረሃብ እየተባባሰ በመምጣቱ እስራኤል እገዳዎችን እንድታነሳ የእርዳታ ቡድኖች አሳሰቡ

ኦክስፋም እና ድንበር የለሽ የህክምና ባለሙያዎችን ጨምሮ ከ100 በላይ የሚሆኑ የሰብአዊ እርዳታ ድርጅቶች እስራኤል በጋዛ ላይ የምትፈጽመውን “እርዳታ ክልከላን እንደ መሳሪያ” መጠቀም ብለው የገለጹትን ተግባር በአስቸኳይ እንድታቆም በጋራ ሆነው በፈረሙበት ደብዳቤ ጠይቀዋል።

አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

እስራኤል በጋዛ እያካሄደች ያለችው በጅምላ የማስራብ ዘመቻ ኦክስፋም እና ድንበር የለሽ የህክምና ባለሙያዎችን ጨምሮ ከ100 በላይ ዸም አቀፍ የሰብአዊ እርዳታ ድርጅቶች ያወገዙ ሲሆን፥ ድርጅቶቹ መንግስታት አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስዱም ጥሪ አቅርበዋል።

በመላው ግዛቱ ረሃብ እየተባባሰ መምጣቱን ያስጠነቀቁት ቡድኖቹ፥ ከእስራኤል መንግስት በተደጋጋሚ መጋቢት ወር ላይ የገቡትን አዲሱን የእስራኤል ደንቦች እስካላከበሩ ድረስ የሰብአዊ እርዳታ ለማቅረብ ፍቃድ የሌላቸው መሆኑን እንደተነገራቸው አብራርተዋል።

እስራኤል በጋዛ ያሉ የሰብዓዊ እርዳታዎች እንዳይገቡ በማገድ፣በመቆጣጠርና፣ እርዳታ የሚከፋፈልባቸው ስፍራዎች ላይ ጥቃት በመፈፀም በርካታ ፍልስጤማውያን ለከፋ ረሀብና ሞት የተዳረጉ ሲሆን፥ ህፃናት በምግብ እጥረት መቀንጨር ሲዳረጉ፣ በእድሜ ከፍ ያሉት ደግሞ በረሀብ በየመንገዱ ሞተው ማግኘት እየተለመደ መጥቷል። እንደ ጋዛ የጤና ሚኒስቴር መረጃ መሰረት ባለፉት 24 ሰዓታት እንኳ ከ10 በላይ ፍልስጤማውያን በረሀብ ሞተዋል።

በደብዳቤው መሰረት የእስራኤል ባለስልጣናት በሀምሌ ወር ብቻ ከ60 በላይ የእርዳታ አቅርቦት ጥያቄዎችን ውድቅ በማድረጉ ምክንያት የምግብ፣ የመድሀኒት እና የመጠለያ እቃዎችን ለተቸገሩት ማድረስ እንዳልቻሉ ገልጸዋል።

ሆስፒታሎች በከፍተኛ ሁኔታ የመሠረታዊ አቅርቦቶች እጥረት ስላጋጠማቸው ህጻናትን፣ አዛውንቶችን እና አካል ጉዳተኞችን ጨምሮ ተጋላጭ የሆኑ ህዝቦች በረሃብ እና መከላከል በሚቻሉ በሽታዎች እየሞቱ እንደሆነ ቡድኖቹ አሳስበዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ድርጅቶቹ እገዳው የሰብአዊ ሥራን ፖለቲካዊ እንዳደረገው እና ዸም አቀፍ ህግን የሚጻረር ነው ሲሉ ይከራከራሉ።

የእስራኤል ባለስልጣናት በበኩላቸው ዕርዳታ ወደ ሃማስ እንዳይዘዋወር ለመከላከል ተብሎ የተደረገ መሆኑን በማንሳት እርምጃዎቹ ትክክል እንደሆነ ይናገራሉ።

ሁለት ዓመት ሊሞላ ጥቂት ወራት በቀሩት እና እስራኤል በጋዛ እያካሄደችው ካለው ጦርነት ጋር በተያያዘ ኔታኒያሁ ጋዛን ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር ዕቅድ አውጥተው ለተግባራዊነቱ እየሠሩ መሆኑን ባለፈው ሳምንት ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።

15 Aug 2025, 15:01