የደቡብ ሱዳን ጳጳስ ህዝባቸው በዕለት ተዕለት ኑሮአቸው ውስጥ ሰላምን መሻት እንዳለባቸው አሳሰቡ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ከሱዳን የረጅም ጊዜ እርስ በርስ ጦርነት በኋላ ደቡብ ሱዳን በአውሮፓውያኑ በ2003 ዓ.ም. ሐምሌ ወር ላይ ነጻነቷን ያወጀችበት ዕለት ሲሆን፥ በዚህም መሰረት ሃገሪቷ ከሱዳን ነፃ የወጣችበትን 14ኛ ዓመት የነፃነት መታሰቢያን ባከበረችበት ወቅት በደቡብ ሱዳን የቤንቲዩ ጳጳስ የሆኑት ብጹእ አቡነ ክርስቲያን ካርላሳሬ ምእመናን ተጨባጭ ካልሆኑ ሐሳቦች ወጥተው ሰላምን እንደ ግላዊና የጋራ ኃላፊነት መቀበል እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የቤንቲዩ ጳጳስ ሐምሌ 2 ከሚከበረው የደቡብ ሱዳን የነፃነት ቀን አንድ ቀን ቀደም ብለው በሰጡት መግለጫ ሰላም በተጨባጭ እርምጃዎች እና በሥነ ምግባራዊ ታማኝነት መታየት እንዳለበት አሳስበዋል።
“ሁሉም ሰው በተሰማራበት የሥራ መስክ ሁሉ ታማኝ መሆን አለበት” ያሉት ጳጳሱ፣ ዜጎችን ለማገልገል በሥነ ምግባር የታነፅ አመራርን መለማመድ እንደሚገባ አስታውሰው፥ ከአንድ ቡድን ይልቅ የሀገሪቱን አጠቃላይ ጥቅም መፈለግ እንደሚጋባ ካሳሰቡ በኋላ፥ ‘ብዙውን ጊዜ በአፋችን ስለ ሰላም ደጋግመን ብንናገርም፥ ነገር ግን በተለያየ ሁኔታ ጦርነት እንፈጥራለን፣ ሰላም ረቂቅ የሆነ ጽንሰ-ሀሳብ ብቻ ሆኖ ተወስኖ መቆየት ያለበት ሳይሆን ነገር ግን በየቀኑ የምንኖረው እና አብረን የምንገነባው ነገር ነው” በማለት አብራርተዋል።
ደቡብ ሱዳን ነጻነቷን ባገኘች በሁለት ዓመታት ውስጥ ተመልሳ ወደ እርስ በርስ ጦርነት የገባች ሲሆን፥ የግጭቱ ምክንያት ደግሞ በፕሬዚዳንት ሳልቫኪር እና በምክትላቸው ሪክ ማቻር መካከል የተፈጠረ አለመግባባት እንደሆነ ይነገራል።
ይህ የእርስ በርስ ጦርነት ደቡብ ሱዳንን ወደ ኢኮኖሚ ድቀት የከተታት ሲሆን በተፈጥሮ ሀብቷ የተትረፈረፈችው አገር እርዳታ ፈላጊ ሆናለች።
በዚህ ጦርነት ምክንያት ከ400 ሺህ በላይ ዜጎች የተገደሉ ሲሆን፥ ከ1 ነጥብ 9 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ደግሞ ወደ ጎረቤት አገራት መሰደዳቸውን የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሽን ሪፖርት ያስረዳል።
12 ሚሊዮን ህዝብ ብዛት ያላት ደቡብ ሱዳን በፈረንጆቹ 2018 ዓ.ም. የግጭቱ ዋነኛ ተሳታፊዎች የሰላም ስምምነት ቢመሰረቱም የሚጠበቀውን ያህል ውጤት አለማምጣቱን መረጃዎች ያሳያሉ።
ለቁርጠኝነት የተደረገ ጥሪ
ብጹእ አቡነ ካርላሳሬ የሰጡት መግለጫ ደቡብ ሱዳን በአካባቢያዊ ብጥብጥ እና ፖለቲካዊ ክፍፍልን ጨምሮ በጸጥታ እጦት ከባድ ፈተና ውስጥ ባለችበት ወቅት ሲሆን፥ ሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት በደቡብ ሱዳን ህዝቦች ነፃ አውጪ ንቅናቄ የተቃዋሚዎች ቡድን (SPLM-IO) እና በደቡብ ሱዳን ህዝብ መከላከያ ሃይል (SSPDF) መካከል በተቀሰቀሰ ግጭት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለሞት፣ ለመቁሰል እና ለመፈናቀል መዳረጋቸው እየተገለጸ ይገኛል።
ብጹእ አቡነ ካርላሳሬ ደቡብ ሱዳናውያን ክርስቲያኖች ጨዋነት የተሞላበት ንግግር እንዲያደርጉ፣ ከጎረቤቶቻቸው ጋር የጋራ በሆነ መተማመን እንዲኖሩ፣ ኃላፊነት የተሞላበት አመራር እንዲያሳዩ እና ቁርጠኛ የሆነ አገልግሎት እንዲሰጡ ያበረታቱ ሲሆን፥ በማከልም ‘ሙስና የነፃነት መሰረትን ስለሚያናጋ ይሄንን ለመከላከል ተቋማት መጠናከር እንዳለባቸው’ አሳስበዋል።
በሰላም ላይ የተመሰረተ መጪ ጊዜ
ደቡብ ሱዳን በአውሮፓዊያኑ በ 2026 ዓ.ም. የምታደርገውን ሃገራዊ ምርጫ በመጠባበቅ ላይ ያለች ሲሆን፥ ብጹእ አቡነ ካርላሳሬ ይሄንን አስመልክተው እንደተናገሩት የደቡብ ሱዳን ህዝብ ሰላማዊ አብሮ የመኖር ባህል እና የዜግነት ኃላፊነትን በማጠናከር ለምርጫው እንዲዘጋጅ ጥሪ በማቅረብ፥ ምርጫው የሀገሪቱን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ለመቅረጽ ወሳኝ አጋጣሚ ስለሆነ ‘ፍትሃዊ፣ ተአማኒ እና ሰላማዊ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።