ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና የኤም 23 አማፂያን ከፊል የሰላም ስምምነት በኳታር ተፈራረሙ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
‘የመርሆዎች መግለጫ’ የሚል ስያሜ የተሰጠው ሃምሌ 12 ቀን 2017 ዓ.ም. የተፈራረሙት ይህ ስምምነት ሁለቱም ወገኖች ከጥቃት፣ ከ"ጥላቻ ፕሮፓጋንዳ" እና "በመሬት ላይ ያሉ አዳዲስ ቦታዎችን በኃይል ለመያዝ ከሚደረጉ ሙከራዎች" መቆጠብ እንዳለባቸው የሚገልጽ ሲሆን፥ ይህ ስምምነት በችግር ውስጥ ለነበረችው ሀገር መጪው ጊዜ ሰላማዊ እንደሚሆን ተስፋ እንደተጣለበት ተገልጿል።
ቅዳሜ ዕለት በኳታር ዶሃ የኪንሻሳ መንግስት ተወካዮች እና የኤም 23 አማፂ ቡድን የተፈራረሙት የመርህ መግለጫ፥ ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነትን እንዳካተተ እና በምሥራቅ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የመንግሥት ስልጣንን ወደነበረበት ለመመለስ የሚያስችል ፍኖተ ካርታ እንደያዘ የጣሊያን የዜና ወኪል ኤጂአይ (AGI) ዘግቧል።
መግለጫው ወደ ቋሚ ስምምነት ያደርሳል ተብሎ የታሰበ ፍኖተ ካርታ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፥ ሁለቱ ወገኖች የስምምነቱን ውሎች እስከ ሐምሌ 22 ተግባራዊ ለማድረግ በመስማማት፥ የመጨረሻው የሰላም ስምምነት በነሐሴ 12 እንደሚጠናቀቅ እና ባለፈው ወር በአሜሪካ አደራዳሪነት በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ኤም 23ን ትደግፋለች የሚለውን ውንጀላ ውድቅ ካደረገችው ሩዋንዳ መካከል ከነበረው ስምምነት ጋር መጣጣም አለበት ተብሏል።
ከዚህም በተጨማሪ የሃገሪቱ ባለስልጣናት እንደገለጹት ስምምነቱ ኤም 23 ከያዛቸው አካባቢዎች "ያለ ድርድር እንዲወጣ" ማድረግን ጨምሮ የመንግሥትን "ቀይ መስመር" ግምት ውስጥ ያስገባ ነው ብለዋል።
በአሁኑ ግጭት ዋነኛ ተዋናዮች ከሆኑት መካከል አንዱ የሆነው የኤም 23 አማፂያን የተመሰረቱት ከ16 ዓመታት በፊት ከከሸፈው የሰላም ስምምነት በኋላ እንደሆነ የሚታወቅ ሲሆን፥ መግለጫው “ሁሉን አቀፍ የሰላም ስምምነት” ን በማሰብ በተቻለ ፍጥነት መደበኛ ድርድር ለመጀመር ቃል እንደተገባበትም ጭምር ተገልጿል።
ግጭት የተንሰራፋበት ክልል
ኤ.ጂ.አይ እንደዘገበው ከየካቲት ወር ጀምሮ በክልሉ ውስጥ የነበሩ የተለያዩ ግጭቶች መሻሻል አሳይተው የነበረ ሲሆን፥ ነገር ግን በኤም 23 እና በኪንሻሳ መንግስት ደጋፊ ሚሊሻዎች መካከል የሽምቅ ውጊያዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን ገልጿል።
በማዕድን የበለፀገው የምስራቅ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ግዛት ከ30 ዓመታት በላይ በግጭት ሲታመስ የቆየ ሲሆን ከዚህ ቀደም የተደረሱ የሰላም ስምምነቶች እና የተኩስ አቁም ጉዳዮች ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተደጋጋሚ መጣሳቸው ይገለፃል።
በቅርብ ወራት ውስጥ ኤም 23 እና የሩዋንዳ ወታደሮች በኮንጎ ጦር ላይ የከፈቱትን መብረቃዊ ጥቃትን ተከትሎ በሩዋንዳ አዋሳኝ አካባቢዎች ዳግመኛ ሁከት መቀስቀሱ ተነግሯል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና በኮንጎ መንግስት መረጃ መሰረት በዚህ ግጭት ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለሞት መዳረጋቸው እና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩት ደግሞ መፈናቀላቸውን ብሎም ከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ መከሰቱን ጠቁመዋል።
በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ የኤም 23 አማፂያን በማዕድን የበለፀገውን ምሥራቃዊ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ዋና ከተማ ጎማን፣ የቡካቩ ከተማን እና ሁለቱን አየር ማረፊያዎችን የተቆጣጠሩ ሲሆን፥ በዚህም የተነሳ ለአስር ዓመታት የዘለቀው ግጭት ተባብሶ መቀጠሉ ይነገራል።
ሰላም ጥረትን፣ መደጋገፍንና መስማማትን ይጠይቃል
የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ዣክሜይን ሻባኒ ከተግባቦት እና የመገናኛ ብዙሃን ሚኒስትር ፓትሪክ ሙያያ ጋር በመሆን በጋራ በሰጡት መግለጫ መንግስታቸው በሩዋንዳ ከሚደገፈው ኤም 23 ታጣቂ ቡድን ጋር የተፈራረመውን የተኩስ አቁም ስምምነት በማስመልከት እንደተናገሩት ይህ ስምምነት ሰላምን ለማስፈን የተወሰደ አንድ እርምጃ መሆኑን ገልጸዋል።
የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ አክለውም ከሶስት አስርት ዓመታት ብጥብጥ በኋላ “ሰላም የመጀመሪያው ምርጫ” መሆኑን ጠቁመው፥ ሃገሪቷ ወደ ሰላም እየተቃረበች መሆኗን ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ እንደሆኑ እና ይሄንን የሰላም ሂደት የመገንባት ሃላፊነት እንዳለባቸው ጭምር አብራርተው፥ ሆኖም ግን ይህ ተግባር ከፍተኛ ሥራ የሚጠይቅ መሆኑን በማስታወስ "ህዝቡ ለዚህ ዓላማ እንዲተባበር እና ‘ፍቃደኝነቱን’ እንዲያሳይ ማዘጋጀት አለብን" ብለዋል።
የተረጋጋ ሰላምን ለማምጣት መስራት
የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ፓትሪክ ሙያያ በበኩላቸው “የተረጋገጠ እና ዘላቂ ሰላም እንፈልጋለን” ሲሉ ሃሳባቸውን ያጋሩ ሲሆን፥ በሁለቱም ወገኖች የተፈረመው የሰላም ስምምነት ሰነዱ በምስራቅ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ውስጥ የነበረውን የመንግስት ሥልጣን ወደነበረበት መመለስን የሚገልጽ በመሆኑ፣ በኤም 23 ቁጥጥር ስር ባሉ ግዛቶች ውስጥ ‘የመንግስት አስተዳደርን እና ህዝባዊ ኃይልን እንደገና ማሰማራት” እንደሚያስፈልግ ገልፀው፥ ይህ “በሰላም ስምምነቱ ውስጥ በዝርዝር የሚገለጽ” የሂደቱ ዋና ርዕሰ ጉዳይ እንደሚሆን አረጋግጠዋል።