MAP

የፍልስጤም እና የእስራኤል ጦርነት የፍልስጤም እና የእስራኤል ጦርነት  (AFP or licensors)

ጋዛ ውስጥ የጅምላ ረሃብ መኖሩን መንግሥታዊ ያልሆኑ የዕርዳታ ድርጅቶች አስታወቁ

ጋዛ ውስጥ የሚሠሩ ወደ አንድ መቶ የሚጠጉ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በአካባቢው የተስፋፋውን ጅምላ ረሃብ አውግዘው ይህም ሠራተኞቻቸውን እየጎዳ መሆኑን ገልጸዋል። በአካባቢው የሚገኙ ሆስፒታሎች መረጃ መሠረት፥ በምግብ እጥረት ምክንያት በጥቂት ቀናት ውስጥ 21 ሕፃናት መሞታቸው ታውቋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በጋዛ ሰርጥ እስራኤል በምትሰነዝራቸው ጥቃቶች ሰዎች እየሞቱ እንደሆነ እና የምግብ ዕርዳታን በመፈለግ ላይ ከሚገኙት መካከል አንድ ሺህ ያህል ሰዎች እንደተገደሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ገምቷል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

 

“አሁን በጋዛ ሰርጥ ዋነኛው ጠላት ረሃብ ሆኗል” ያሉት በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፥ ካለፈው እሁድ ጀምሮ አንድ ጨቅላ ሕጻንን ጨምሮ 21 ሕፃናት በረሃብ መሞታቸውን አስታውቀዋል። “ምግብ ለማግኘት በሚሞከርበት ጊዜ ሞት ይከተላል” ያሉት የዕርዳታ ድርጅቶቹ፥ ካለፈው ግንቦት ወር ጀምሮ በእስራኤል እና በአሜሪካ በሚደገፈው አወዛጋቢው የጋዛ ሰብዓዊ ፋውንዴሽን የዕርዳታ ስርጭቱን ከጀመረ ወዲህ ወደ አንድ ሺህ የሚጠጉ የተራቡ ሰዎች ወረፋቸውን ሲጠብቁ ሳለ መገደላቸውን በተባበሩት መንግሥታት የፍልስጤም ስደተኞች ኤጀንሲ አስታውቋል።

ዸም አቀፍ ውግዘት

እስራኤል ደህንነቱ የተጠበቀ ፈጣን የሰብዓዊ ዕርዳታ ስርጭትን እንድታመቻች ግፊት በማድረግ ላይ የሚገኙት የአውሮፓ ኮሚሽኑ ፕሬዝዳንት ወ/ሮ ኡርሱላ ፎን ደር ሌየን፥ “ሲቪሎች ዒላማ ሊደረጉ አይገባም” ብለው፥ ከጋዛ የሚወጡ ምስሎች ሊቋቋሟቸው የማይችሏቸው መሆናቸውን ተናግረዋል።

ይህን በመጋራት የተናገሩት በአውሮፓ ኅብረት የውጭ ጉዳይ ከፍተኛ ተወካይ ካጃ ካላስ፥ ምግብ ፍለጋ ላይ የሚገኙ ሰዎችን መግደል ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ሲገልሱ፥ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አቶ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በበኩላቸው፥ “ጋዛ በቅርብ ጊዜ ታሪክ ውስጥ አይታው የማታውቀው አስፈሪ አደጋ አጋጥሟታል” ሲሉ ተናግረዋል።

መሬት ላይ ያለው ሃቅ

ጋዛ ሰርጥ እስራኤል በምትሰነዝራው ጥቃቶች ሰዎች እየሞቱ እንደሆነ ሲነገር፥ ባለፉት ጥቂት ሰዓታት ውስጥ ቢያንስ 43 ሰዎች ሲገደሉ ከእነዚህ መካከል 18ቱ ጋዛ ውስጥ በአል ሻቲ የተፈናቃዮች ካምፕ ውስጥ የሚኖሩ ሲሆኑ ሰባቱ ዕርዳታን በመጠባበቅ ላይ እያሉ እንደ ነበር ታውቋል።  

ይህ በእንዲህ እንዳለ እስራኤል የጦርነት ግቦቿ ስኬታማነት እንደተቃረብ ያስታወቀች ሲሆን፥ የዩናይትድ ስቴትስ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ በተኩስ አቁም እና ታጋቾቹን ለማስለቀቅ የሚደረገውን ድርድር ለመቀጠል በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ውስጥ ወደ አካባቢው እንደሚደርሱ ይጠበቃል።

 

23 Jul 2025, 17:16