ሌላ ዙር የዩክሬን-ሩሲያ የሰላም ድርድር ሊኖር እንደሚችል ተገለጸ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ሩሲያ ዩክሬንን ሙሉ በሙሉ ከወረረች 1,243 ቀናት የተቆጠሩ ሲሆን፥ በእነዚህ ጊዜያት በተደረጉት ጦርነቶች 170,000 የሚገመቱ ንጹሃን ዜጎች መገደላቸውን መረጃዎች የሚያሳዩ ሲሆን፥ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (OCHA) እንዳስታወቀው ወደ 13 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በአሁኑ ወቅት የሰብአዊ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ገልጿል።
በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል ያለው ሁኔታ በጣም አስቸጋሪ መሆኑ የሚነገር ሲሆን፥ የዩክሬን ባለስልጣናት በዚህ ሳምንት አዲስ ዙር የሰላም ድርድር እንዲደረግ ሀሳብ ያቀረቡ ቢሆንም ሩሲያ እስካሁን ሃሳቡን መቀበሏን ይፋ አላደረገችም።
በሞስኮ እና በኪዬቭ መካከል በኢስታንቡል የተካሄደው ሁለት ዙር ውይይት አገራቱ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ማድረግ ባይችልም፥ ነገር ግን በጦርነቱ የተገደሉትን ወታደሮች አስከሬን ለመመለስ እንዲሁም በርካታ ቁጥር ያላቸውን ምርኮኞችን ለመለዋወጥ ተስማምተዋል።
በሰኔ ወር መጀመሪያ ላይ ከተጠናቀቀው የመጨረሻው ዙር ንግግር በኋላ የዩክሬን ተደራዳሪዎች ሩሲያ ዳግም "ያለ ቅድመ ሁኔታ የተኩስ አቁም" እንዲደረግ የሚለውን ሃሳብ ውድቅ ማድረጓን ተናግረዋል።
ለሰላም ሌላ ዕድል ይኖር ይሆን?
ባለፈው ወር መጀመሪያ ላይ በሁለቱ ሀገራት መካከል ሲደረግ የነበረው ድርድር ከተቋረጠ በኋላ የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ሰሞኑን “የድርድር ሂደቱ መጠናከር አለበት” ማለታቸው የተነገረ ሲሆን፥ ዘለንስኪ ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ለመገናኘት ፈቃደኛነታቸውን ደጋግመው ሲናገሩ “ሰላምን ብሎም ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ በአመራር ደረጃ ተገናኝቶ መወያየት ያስፈልጋል” ብለዋል።
የሩሲያ መገናኛ ብዙሀን እንደዘገቡት ይህ የታሰበው አዲስ የውይይት ዙር ትክክለኛ ቀን እስካሁን እንዳልታወቀ፥ ነገር ግን ኢስታንቡል አስተናጋጅ ከተማ ሆና ልትቀጥል እንደምትችል ገልጸዋል።
ዜሌንስኪ ሰሞኑን ባደረጉት ንግግር በዚህ ድርድር የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ ሁሉም ነገር መደረግ እንዳለበት ገልጸው፥ ከሩሲያው ፕረዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ፊት ለፊት ለመገናኘት ያላቸውን ዝግጁነትም በድጋሚ ያረጋገጡ ሲሆን፥ "በመሪዎች ደረጃ የሚደረግ ስብሰባ ሰላምን በትክክል ለማረጋገጥ አስፈላጊ ነው" ብለዋል።
ኪየቭ እና የአውሮፓ አጋሮቿ እንዲሁም አሜሪካ የሚፈልጉት ያለምንም የቅድመ ሁኔታ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ሲሆን፥ ሩሲያ በበኩሏ ዩክሬን ተጨማሪ ግዛት እንድትሰጣት እና ሁሉንም የምዕራባውያን ወታደራዊ ድጋፍን መቀበል እንድታቆም ጠይቃለች።
ግጭቱ እንደቀጠለ ነው
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ሩሲያ ሃምሌ 14 ቀን 2017 ዓ.ም. ጥዋት ላይ ከቅርብ ወራት ወዲህ በዩክሬን ላይ ስታደርግ ከነበሩት ጥቃቶች ከፍተኛ የተባለውን የአየር ጥቃት ማድረጓ የተነገረ ሲሆን፥ በዚህ ጥቃት የ 12 ዓመት ታዳጊን ጨምሮ ሁለት ሰዎች ሲሞቱ፣ 15 ሰዎች መቁሰላቸው ተነግሯል።
የከተማዋ ባለስልጣናት በጥቃቱ የምድር ውስጥ ባቡር ጣቢያ፣ ሱቆች፣ መኖሪያ ቤቶች እና አንድ ሙዋለ-ህፃናት ላይ ጉዳት መድረሱን ገልጸዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው ሰኔ ወር ላይ በዩክሬን ላይ የተፈጸመው ጥቃት ጦርነቱ የካቲት 2014 ዓ.ም. ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ከተፈጸሙት ጥቃቶች በሰላማዊ ሰዎች ላይ ከፍተኛ የሞት ቁጥር የተመዘገበበት ወር መሆኑን ይፋ ያደረገ ሲሆን፥ በዚህ ወር ብቻ 232 ሰዎች ሲሞቱ፣ 1,343 መቁሰላቸውን ገልጿል። በአገር አቀፍ ደረጃ የሚሳኤል፣ የድሮን እና የመድፍ ጥቃቶች እየተባባሱ በመምጣቱ ከግንባር መስመር ርቀው የሚገኙ ከተሞችን ሳይቀር ጥቃት እንደደረሰባቸው መረጃዎች ያሳያሉ።
የዩክሬን የተሃድሶ ጉባኤ
በሮም ከተማ ከሃምሌ 3 እስከ 4 ቀን 2017 ዓ.ም. ድረስ የዩክሬን የተሃድሶ ጉባኤ የተካሄደ ሲሆን፥ በዚህ ጉባኤ ላይ የካሪታስ ዩክሬን ፕሬዝዳንት ቴቲያና ስታውኒቺ እና የካሪታስ-ስፔስ ዩክሬን ዋና ዳይሬክተር ቭያቼስላቭ ግሪኔ-ቪች ተገኝተዋል።
ጉባኤውን ተከትሎ ሁለቱ ሃላፊዎች ከካሪታስ ኢንተርናሽናሊስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ከሦስት ዩክሬናውያን አንዱ ሰብዓዊ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው አሳስበው፥ ተቋማቸው በሀገሪቱ ውስጥ ከሚሰራቸው ዘርፈ ብዙ ሥራዎች ውስጥ ‘ሰዎች ከደረሰባቸው ጉዳት እንዲያገግሙ እና ወደ መረጋጋት እንዲመለሱ መርዳት’ አንዱ እንደሆነ ገልጸዋል።