ጦርነት ወይስ ሰላም? ምርጫው ሁሌም የኛ ነው
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የሁለቱ የሰላም አምባሳደሮች መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል፦
"እኛ በጦርነቱ ምክንያት የቤተሰብ አባሎቻችንን የቀበርን ፍልስጤማዊ እና እስራኤላዊ ሰላም ፈጣሪዎች ነን፥ ጦርነት ምን ዓይነት ዋጋ እንደሚያስከፍል እናውቃለን። መቋቋም የማይቻል ክብደቱን እናውቃለን። የሃዘንን ስሜት እናውቃለን፣ የምንወደውን ሰው ማጣት ያለውን ስቃይ እና ግጭት የሚያደርሰውን ውድመት እናውቃለን። ዛሬ ድምጻችንን የምናሰማበት ምክንያት ለዚህ ነው፤ ሰላም እንዲመጣ የምንማፀነው እና እነዚህ ጦርነቶች ማብቃት አለባቸው ብለን በማያሻማ መልኩ የምንናገረው ለዚህ ነው።
በኢራን እና በእስራኤል መካከል እየተባባሰ ያለው ጦርነት፣ በጋዛ እየደረሰ ካለው ሞት እና ውድመት ጋር ተደምሮ የክልላችንን ህዝቦች ብቻ ሳይሆን የመላው ዸምን የሞራል ህሊና ሥጋት ውስጥ የጣለ ነው። እጅግ በርካታ ንጹሃን ሰዎች እና ቤተሰቦች መርጠው ባልገቡበት ማዕበል ውስጥ ገብተዋል። ሆኖም ስልጣን ያላቸው ሰዎች ጦርነትን መምረጣቸውን ቀጥለዋል።
ዓመፅ የጥንካሬ ምልክት አይደለም። የሃሳብ እና የሥነ ምግባር አመራር ውድቀት ነው። ጦርነት ጥበብ እና ርህራሄ ያለቀባቸው ሰዎች ውሳኔ ነው። ብቃት ማነስ እና የሞራል ውድቀትን ያሳያል። ቦምቦች ደህንነትን ያመጣሉ ወይም የሰላም የበላይነት ይፈጥራል ብለው የሚያምኑ መሪዎች የወደፊት ሕይወታችንን እንዲቀርጹ ሊታመኑ አይገባም።
ስለዚህም እኛ እንዲህ እንላለን፥ አማራጭ እንዳለ እናውቃለን። እኛ ለዚህ ሕያው ማስረጃዎች ነን። ወደፊት ህይወታችን የተጠላለፈ እና ለዘለዸም ጠላቶች እንድንሆን እንዳልተመረጥን እናውቃለን። የተለየ መንገድ የሚቻል ብቻ ሳይሆን ብቸኛው የሞራል መንገድ ነው።
ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል ውስጥ፣ የሰላም ሥራችንን የተቀላቀሉ ብዙ ኢራናውያንን አግኝተናል። እንደ እኛ ሁከት እንዲቆም የሚናፍቁ ተራ ሰዎች ናቸው። ከቅርብ ቀናት ወዲህ ጦርነቱ እየበረታ በሄደ ቁጥር ከአውሮፓ፣ ከአሜሪካ እና በራሷ ኢራን ውስጥ ካሉ ኢራናውያን ሳይቀር በርካታ መልእክት ደርሶናል። የጥፋት ዑደቱ እንዲቆም ተማጽነዋል። ድምፃቸው ግልጽ ነው፥ ይህን ጦርነት አይፈልጉም።
ከመልዕክቶቹ ውስጥ አንዱ እንዲህ ይነበባል፡-
“እኔ የምጽፍላችሁ የጦርነትን ስቃይ ከሚያውቅ፣ ነገር ግን አሁንም የሰላም ህልም ካለው የኢራን ህዝብ ውስጥ ሆኜ ነው፥ ዝም ማለት ቀላል በሆነበት ዸም የተስፋ ድምጽ ስለሆናችሁ ከልቤ አመሰግናችኋለው፥ ዸም የተበታተነች በሚመስልበት ጊዜ በሰብዓዊነት ስላመናችሁ ላመሰግናችሁ እፈልጋለሁ” ይላል።
እኛ ብቻችንን አይደለንም። እኛ ትንሽ አይደለንም። እነዚህ የሰላም ድምጾች ከድንበር ተሻግረው ይገኛሉ፣ እናም እነሱ መጠናከር አለባቸው። የእስራኤል፣ የፍልስጤም እና የኢራን ህዝብ በአመጽ እንደማይገለጽ ጠንቅቀን እናውቃለን። ማህበረሰቦቻችን በታሪክ፣ በጥንካሬ እና በፈጠራ የበለፀጉ ናቸው። ዛሬ ግን ያ ፈጠራ በግጭት እየተበላ ነው። ጉልበታችንን ወደ ሰላም ካዞርን ምን መገንባት እንደምንችል፣ ለዸም ምን አይነት ውበት ልናቀርብ እንደምንችል አስቡት።
ለሰላም ለመነሳት ጊዜው አሁን ነው። በፍትህ፣ በእኩልነት፣ በእርቅ እና በሰብአዊ ክብር የምናምን ሁላችን ፖለቲካዊ ውድቀት ከመጣው ጥፋት ለመውጣት ጊዜው አሁን ነው። አይሁድ፣ ክርስቲያን፣ ሙስሊም ሁሉም በጋራ የእምነት አስተምሮአችን የህይወትን ቅድስና እና የሰላም አስፈላጊነት በሚያስተምሩበት መንፈስ መነሳት አለብን።
ቅዱሳት መጻሕፍት ግልጽ ናቸው፡- “የሚያስታርቁ ብፁዓን ናቸው፣ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና” ይላል ፥ ሁላችንም እንደዚህ አይነት ልጆች እንድንሆን ተጠርተናል። እምነታችን የጦር መሳሪያ አይደለም። ድልድይ ነው። አንድ ሊያደርገን እንጂ ሊከፋፍለን አይገባም።
ከዚህ ጦርነት ርቀው ለሚገኙ፣ በጣሊያን፣ በአውሮፓ፣ በላቲን አሜሪካም ሆነ በሌሎች ቦታዎችም ቢሆን ከጦርነት የራቁ እንደሆኑ ሊሰማቸው ይችላል። ነገር ግን ይህ አደገኛ ቅዠት ነው። ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየር እንደተናገረው፣ “ኢፍትሃዊነት የትም ቦታ ቢሆን ለፍትህ አስጊ ነው” ይላል። ጦርነት በአንድ ቦታ ብቻ ተወስኖ የሚቀር አይደለም። የእሳቱ ነበልባል ድንበር እየተሻገረ ዸምን ወደ ጥፋት እየጎተተ ነው። ዸም ከዚህ በፊት በጦርነት የወደቀችው በዚህ መንገድ ነው።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ከሁለት ሳምንት በፊት በተገናኘንበት ወቅት እንደነገሩን፡- "የሰላም መንገድ ሁሉንም የሚያካትት እና በሁሉም ህይወት ባላቸው ፍጥረታት መካከል ትክክለኛ ግንኙነት እንዲፈጠር ያደርጋል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እንዳመለከቱት፣ ሰላም የማይከፋፈል መልካም ነገር እና የሁሉም የሰው ልጆች ነው” ብለው ነበር።
የማስጠንቀቂያ ምልክቶችን እያየን ነው። ከህንድ እና ፓኪስታን እስከ ሰሜን ኮሪያ፣ ከጋዛ እስከ ሱዳን እና የመን፣ ከዩክሬን እና ከሩሲያ እስከ ኮንጎ ድረስ። እያንዳንዱ አዲስ ግጭት ወደ ጫፉ ያቀርበናል። አንዳንዶች ተጨማሪ ጦርነት አስከፊው ጦርነት እንዳይከሰት ይከላከላል ብለው ያምናሉ። ታሪክ ግን የሚያስተምረን በተቃራኒው ነው። እያንዳንዱ ጦርነት ሰላምን የበለጠ ደካማ ያደርገዋል። እያንዳንዱ ጦርነት ወደ ኒውክሌር ውድመት ያቀርበናል።
ለዚህም ነው ሙሉ በሙሉ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ መኖር ዬለበትም ብለን የምናምነው። ለኢራን ወይም ለእስራኤል ብቻ ሳይሆን ለሁሉም አገሮች ተግባራዊ ሊሆን ይገባል። የትኛውም ሀገር በምድር ላይ ህይወትን ሊያጠፋ የሚችል የጦር መሳሪያ እንዲኖረው ምንም አይነት የሞራል ማረጋገጫ የለም።
በየቀኑ ስቃዩ ሥር እየሰደደ ነው፥ ጋዛ እየወደመች ነው። ዌስት ባንክ ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ጥቃት ገጥሞታል። የእስራኤል እና የኢራን ቤተሰቦች በየጊዜው በሚሳኤል እና በአየር ጥቃት ስጋት ውስጥ ይገኛሉ። ይህ ጦርነት ለሁሉም ይተርፋል፥ ሀዘንን ከሀዘን ሞትን ከሞት ጋር ያገናኛል። ነገር ግን በምትኩ ተስፋን ከተስፋ፣ ሰብአዊነትን ከሰብዓዊነት ጋር ማገናኘት እንደምንችል እናምናለን።
ተናደናል፣ ፈርተናል፣ ቁጣችን እና ህመማችን እንደ ኒውክሌር ሃይል ጥልቅ እና ኃይለኛ ነው፥ እናም ይሄንን ሃይል ለጥፋት መጠቀም ቀላል ነበር። እኛ ግን በምትኩ ወደ ብርሃን ለመለወጥ ወሰንን፥ ቁጣችንን፣ ፍርሃታችንን እና ሀዘናችንን ወደ የተቀደሰ ነገር፣ ወደ ዲፕሎማሲ፣ ወደፈውስ እና ሰላም እናደርሳለን።
ገለልተኛ አይደለንም። እኛ የተነጠልን ሰለባ አይደለንም። እኛ ምስክሮች ነን። እኛ ከአደጋ የተረፍን ነን። አሁን የምንናገረው ጦርነት ምን እንደሚያመጣ በትክክል ስለምናውቅ ነው። ጦርነት መቼም ቢሆን ዘላቂ ሰላም አያመጣም።
ነገር ግን ሌላ ነገር እናውቃለን፡ ሁሌም ቢሆን ይሄንን የሚያስታርቅ ነገር አለን። ቂም በቀልን መፈለግ እንችላለን ወይም እርቅን መቀበል እንችላለን። የጦር መሳሪያን ወይም የዲፕሎማሲውን አመክንዮ መከተል እንችላለን። የታሪክ ምርኮኞች ሆነን ልንቀር እንችላለን ወይም አዲስ የወደፊት ሁኔታን መፍጠር እንችላለን።
ዛሬ የምንናገረው እንደ እምነት ሰዎች ነው። እምነት ከተጠያቂነት ስለሚያድነን ሳይሆን ይሄንን ስለሚፈልግ ነው። እውነተኛ እምነት ተራ ነገር አይደለም። ይሰራል፣ ይገነባል፣ ህይወትን ይጠብቃል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ባለፈው ዓመት በቬሮና በተካሄደው የሰላም መድረክ ላይ እንደነገሩን “ሰላም ካለመተማመን፣ ቅጥር ከመገንባት፣ እርስ በርስ በጦር መሳሪያዎች ከመደጋገን በፍፁም አይገኝም” ቅዱስ ጳውሎስ “የዘራችሁትን ታጭዳላችሁ” ብሏል፥ ስለዚህ ሞትን፣ ጥፋትን ወይም ፍርሃትን ሳይሆን፥ ይልቁኑ ተስፋን እንዝራ! ብለው ነበር።
ለርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ራዕይ ቁርጠኞች ነን፥ እናም ተስፋን ለመዝራት እና በጨለማ ጊዜ ውስጥ እንኳን ስለ ሰላም ለመስራት እንመርጣለን" በማለት አጠቃለዋል።