MAP

በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል በስታንቡል የተደረገው የሰላም ንግግሮች በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል በስታንቡል የተደረገው የሰላም ንግግሮች  (AFP or licensors)

ምንም እንኳን ጥቃቶች ቢኖሩም የዩክሬን-ሩሲያ የሰላም ድርድር እየተካሄደ መሆኑ ተገልጿል

ኪየቭ ሩሲያን በሰው አልባ አውሮፕላኖች ከደበደበች በኋላ ሩሲያ በምላሹ በዩክሬን ላይ ጥቃት እያደረሰች እንደሆነ የሚገልጹ አዳዲስ ዘገባዎች ቢያመላክቱም፥ የሩሲያ እና ዩክሬን ሁለተኛ ዙር የሰላም ንግግር በቱርክ ኢስታንቡል ከተማ እየተካሄደ መሆኑ ተገልጿል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በሁለቱ ሀገራት መካከል የተደረገውን የሰላም ድርድር የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃካን ፊዳን የመሩት ሲሆን፥ የቱርክ፣ ሩሲያ እና ዩክሬን ባለስልጣናት ተሳትፈውበታል።

የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃካን ጦርነቱ ተጠናክሮ ቢቀጥልም በዩክሬን እና በሩሲያ መካከል ሁለተኛው ዙር ቀጥተኛ ውይይት በመጀመሩ ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸው፥ ኢስታንቡል ውስጥ እየተካሄደ ያለው ውይይት በሁለቱም ወገኖች የተኩስ አቁም መስፈርቶች ላይ እንደሚወያይ ጠቁመዋል።

ዩናይትድ ስቴትስ ለሰላም ሂደቱ የበኩሏን አስተዋጽኦ እያበረከተች መሆኑን የገለጹት የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ፥ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ለሞትና ለአካል ጉዳት ያደረሰውን ጦርነት ለማስቆም ውይይቱ ተጨባጭ ውጤት እንደሚያስገኝ እርግጠኛ ነኝ ብለዋል።

በቅርቡ ለኔቶ ወታደራዊ ህብረት ሃላፊ ማርክ ሩት እንደተናገሩት ቱርክ ጦርነቱ እንደሚያበቃ ያላትን ተስፋ ጠቁመው፥ “በእርግጥ በዩክሬን እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ወደ ፍትሃዊ እና ዘላቂ ፍጻሜ ለማምጣት የምናደርገው ጥረት የውይይታችን አስፈላጊ አካል ይሆናል” ሲሉ በአጽንዖት መናገራቸው ይታወሳል።

“ሁላችሁም እንደምታውቁት ቱርክ ይህ ጦርነት እንዲቆም የዲፕሎማሲያዊ መንገድን አስፈላጊነት ሁል ጊዜ ቅድሚያ ትሰጣለች” ያሉት ሃካን፥ አሁን ከሶስት ዓመታት ከባድ ስቃይ በኋላም ቢሆን በመጨረሻም የሠላም ዕድል መኖሩን ጠቁመው፥ “በኢስታንቡል ውስጥ የሚደረጉ ንግግሮች አዲስ ምዕራፍ ሊከፍቱ እንደሚችሉ ተስፋ እናደርጋለን” ሲሉ ሚኒስትሩ አክለዋል።

ሁለቱ ወገኖች ከዚህ ቀደም ግንቦት 8 ቀን 2017 ዓ.ም. እዚሁ ቱርክ ውስጥ ተገናኝተው መነጋገራቸው የሚታወስ ሲሆን፥ ሰኞ ዕለት የጀመረው የሩሲያ እና ዩክሬን ሁለተኛ ዙር የሰላም ንግግር የተጀመረው የሩስያ ጥቃቶች ዩክሬንን መምታታቸውን የሚገልጹ ተጨማሪ ዘገባዎች መውጣት ከጀመሩ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ እንደሆነ ተነግሯል።

የአከባቢው ባለስልጣናት እንዳሉት ሰኞ ማለዳ ላይ ሁለት ባለስቲክ ሚሳኤሎች በሰሜናዊ ምስራቅ ዩክሬን የምትገኘው ካርኪቭ ከተማ ውስጥ የሚገኝ የመኖሪያ ሰፈር መምታታቸውን ገልጸዋል።

የከተማው ከንቲባ ኢጆር ቴሬክሆቭ አንደኛው ሚሳኤል በአንድ የመኖሪያ ህንፃ አጠገብ ሲያርፍ፥ ሁለተኛው ደግሞ ትምህርት ቤት አቅራቢያ የሚገኘው መንገድ ላይ ጉዳት ማድረሱን ጠቁመዋል።

በአሁኑ የሩሲያ ጥቃት በሰው ህይወት ላይ ስለደረሰ ጉዳት እስካሁን የተገለጸ ነገር ባይኖርም፥ ይህ ጥቃት የተፈጸመው ዩክሬን በሰው አልባ አውሮፕላኖች ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በአራት የሩሲያ ወታደራዊ ካምፖች የሚገኙ 40 የጦር አውሮፕላኖች ላይ ተከታታይ ከባድ ጥቃቶችን መፈጸሟን ተከትሎ እንደሆነ መረጃዎች ቢያሳዩም፥ የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ዩክሬን ባካሄደችው ጥቃት ምንም አይነት ጉዳት እንዳልደረሰ ገልጸዋል።

ሆኖም ግን ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ በጥቃቱ 117 ሰው አልባ አውሮፕላኖች ጥቅም ላይ መዋላቸውን ገልፀው "34 በመቶ [የሩሲያ] ስትራቴጂክ ክሩዝ ሚሳዔል ተሸካሚዎችን" መምታታቸውን ገልጸዋል። የዩክሬን ደኅንነት ተቋም እንደገለጸው ይሄንን “ዘመቻ የሸረሪት ድር” የሚል ኮድ የተሰጠውን ጥቃት ለመፈጸም ለአንድ ዓመት ከግማሽ ያህል ሲያቅድ መቆየቱንም ገልጿል።

ባለስልጣናቱ እንዳሉት ቢያንስ 13 አውሮፕላኖች በሩሲያ አየር ማረፊያዎች ላይ በደረሰ ጥቃት መውደማቸውን ጠቁመው፥ በጥቃቱ 7 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ጉዳት ማድረሳቸውን ገልጸዋል።

ከሦስት ዓመታት በላይ የዘለቀው ጦርነት የሚያበቃው መቼ እና እንዴት እንደሆነ ዸም እየተከታተለው በሚገኝበት በዚህ ወቅት ምንም እንኳን ግጭቶች እየተካሄዱ ቢሆንም፥ የሰላም ንግግሮች መጀመራቸው ተስፋ ሰጪ እንደሆነ እየተነገረ ይገኛል።
 

03 Jun 2025, 16:18