በዌስት ባንክ ውስጥ የሚገኙ 12 የፍልስጤማዊያን መንደሮች ስጋት ላይ እንደሆኑ ተገለጸ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
በዌስት ባንክ፣ በማሳፈር ያታ አከባቢ፣ ከኬብሮን በስተደቡብ ባሉት ኮረብቶች ውስጥ የሚገኙትን 12 የፍልስጤማዊያን መንደሮችን እያፈራረሰ ያለውን የእስራኤል ቡልዶዘር ግስጋሴ ለማስቆም የዸም አቀፍ አድናቆት እና የኦስካር ሽልማት እውቅናን እንኳን ያላገኘው ‘ሌላ መሬት ዬለንም’ በሚል ርዕስ የተሰራው ዘጋቢ ፊልም ብቻውን በቂ ነበር የተባለለት ሲሆን፥ ይህ አከባቢ በኦስሎ ስምምነት መሰረት ‘ኤሪያ ሲ’ ተብሎ የተሰየመ በዌስት ባንክ አከባቢ የሚገኝ የፍልስጤማዊያን ግዛቶች ውስጥ አንዱ እንደሆነ ይታወቃል።
በተቃራኒው በአሁኑ ወቅት በእስራኤል እና በኢራን መካከል የተከሰተው ግጭት የዸም አቀፉን ህብረተሰብ ትኩረት ይዞ በመገኘቱ፥ 2,800 የሚሆኑ ፍልስጤማውያን የሚጠለሉበትን ቤቶች የማፍረስ መንገዱን ምቹ ያደረገ ይመስላል ተብሏል።
ረቡዕ፣ ሰኔ 11 ቀን 2017 ዓ.ም. በእስራኤል የዌስት ባንክ ከፍተኛ የእቅድ ምክር ቤት አካባቢውን በሙሉ የእስራኤል ሃይሎች ቀጥታ የተኩስ ልምምድ የሚያደርጉበት ‘የተኩስ ዞን 918’ በሚል ስያሜ ወታደራዊ የተኩስ ቀጠና አድርጎ በመፈረጅ በይፋ የመጨረሻ ውሳኔ የሰጠ ሲሆን፥ በማሳፈር ያታ ዙሪያ ያለው ህጋዊ ክርክር ለብዙ አሥርተ ዓመታት የዘለቀ እና ዘላቂ ጥበቃ ባላገኙ ነዋሪዎች ተደጋጋሚ አቤቱታ ሲቀርብበት እንደነበረ ተነግሯል።
ይህ የመጨረሻው ውሳኔ ከአሁን በኋላ ፍልስጤማዊያኑ የሚያደርጉትን ጥረት የሚያስቆም እንደሆነ የተነገረ ሲሆን፥ የአከባቢው ነዋሪዎች ወታደራዊ ስያሜው ከእውነተኛ የመከላከያ ፍላጎቶች ይልቅ የአይሁድ ሰፈሮችን ለማስፋፋት እንደ ምክንያት ሆኖ ያገለግላል ብለው ሲከራከሩ እንደቆዩ እና በአካባቢው የሚደረጉ ወታደራዊ ልምምዶች እምብዛም ባይሆኑም፥ ብዙ ጊዜ በእስራኤል ወታደሮች ጥበቃ የሚደረግላቸው ቢያንስ 12 አዳዲስ ማዕከሎች መመስረታቸው ተገልጿል።
ውጥረት እና ብጥብጥ እየተባባሰ መሄዱ
ከእነዚህ ሰፈሮች ጋር ተያይዞ ውጥረቱ እና ብጥብጡ ተባብሶ መቀጠሉን ነዋሪዎች እየገለጹ የሚገኙ ሲሆን፥ የዚህን አከባቢ አሁናዊ ሁኔታ በሚያሳየው ዘጋቢ ፊልም ውስጥ የፊልሙ ዋና ተዋናይ እና ተባባሪ ዳይሬክተር ባዝል አድራ የአጎት ልጅ የእስራኤል መከላከያ ሰራዊት በስፍራው እያለ በሰፋሪዎች ቡድን በአሰቃቂ ሁኔታ ሲገደል የሚያሳይ አንድ በጣም አሳዛኝ ትዕይንት እንደተካተተበት ተገልጿል።
በወቅቱ ጠቅላይ ሚንስትር የነበሩት ኤሪያል ሻሮን በአካባቢው የሕዝብ ዝውውር ለመጀመር ፍላጎት እንዳላቸው በገለጹበት ከ 1980ዎቹ ጀምሮ፣ ፍልስጤማዊያኑ የወታደራዊ ቀጠና ምደባው ሰፋ ላለ የግዳጅ መፈናቀል ዓላማ ያገለግላል በማለት ሲከራከሩ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፥ ከዚህም በተጨማሪ በ2016 ዓ.ም. እስራኤላዊው ዳኛ ዴቪድ ሚንትዝ የማህበረሰቡን ይግባኝ ውድቅ በማድረግ ቤተሰቦቻቸው የሚኖሩበትን መሬቶች ለትውልድ እንዲለቁ ትእዛዝ አስተላልፈው እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፥ ዘጋቢ ፊልሙ እንደሚያሳየው ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ማፍረስ ስልታዊ እና በተደጋጋሚ የጥቃት ድርጊቶች የታጀቡ እንደሆኑ ተገልጿል።
የቅርብ ጊዜው ውሳኔ በአካባቢው ከመሬት ምዝገባ ጋር የተያያዙ ሁሉንም ህጋዊ ሂደቶችን ከማስቆሙ በተጨማሪ፥ ግልጽ ያልሆኑ “የደህንነት ስጋቶችን” እንደሚጠቅስ እና በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ለአዲስ የማፍረስ ማዕበል በር የመክፈት አደጋ እንዳለው ተገልጿል።
በክልሉ የተጠናከረ የመፈናቀል አደጋ ባጋጠመበት በአሁኑ ወቅት፥ የማሳፈር ያታ ህዝብ በሰፊው ጂኦፖለቲካዊ ግጭት ሳቢያ በግዳጅ መፈናቀላቸው በቸልታ እንዳይታይ ለዸም አቀፉ ማህበረሰብ እና ሚዲያዎች ጥሪ ማቅረባቸው ተገልጿል።