የ ‘The Chosen’ ተከታታይ ድራማ ተዋኒያን እና ሠራተኞች ትርዕታቸውን በቫቲካን እንደሚያቀርቡ ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ሰኞ ሰኔ 16/2017 ዓ. ም. 'The Chosen' የተሰኘ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ተዋናዮች እና ሠራተኞች በጣሊያን ማቴራ ውስጥ ከሚያካሂዱት የቀረጻ ሥራ ጎን ለጎን በዕረፍት ጊዜያቸው ወደ ሮም መጥተው ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። ተዋናዮቹ ዮናቶን ሩሚ፣ ጆርጅ ዛንቲስ፣ ኤልዛቤት ታቢሽ፣ ቫኔሳ ቤናቬንቴ እና የድራማው አዘጋጅ ዳላስ ጄንኪንስ ስለ አምስተኛው ዙር ትርዒት ትርጉም በማስመልከት ውይይት አድርገዋል።
አዲሶቹ ተከታታይ ትርዒቶች ከዚህ በፊት አሜሪካ ውስጥ የታዩ ሲሆን፥ 'The Chosen' ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ በአሁኑ ወቅት በአማዞን ፕራይም ቪዲዮ ላይ ለተመልካቾች ከሚቀርቡ አሥር ምርጥ ትርዒቶች መካከል አንዱ እንደሆነ ታውቋል። በጣሊያን ውስጥ የሚገኙ ተመልካቾች የአዲሱ ሰሞን ተከታታይ ትርዒቶች እስከሚጀምሩበት የሚቀጥለው ወር ድረስ መጠበቅ ይኖርባቸዋል።
ከተዋኒያኑ እና ሠራተኞች ጋር የተደረጉ ውይይቶች
ተዋናኒያኑ እና የቡድኑ አባላት በመግለጫው እንደገለጹት፥ የአዲሱ ሰሞን ትርዒቶች የሕማማት ሳምንት ክስተቶችን ጨምሮ ታዋቂ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ወቅቶችን የሚያሳዩ በመሆናቸው አስፈላጊ እንደሆኑ አስረድተዋል።
የኢየሱስን ሚና የሚተውነው ዮናተን ሩሚ በመግለጫው፥ የዚህ ሥራ ክፍል ዓይኑን የሚከፍት እንደሚሆን ገልጾ፥ “በቫቲካን ውስጥ መቆየቱ እግዚአብሔር ብዙ ሰዎችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ የማምጣት ተልዕኮውን መቀጠል እንደሚፈልግ ማሳያ ነው” በማለት ስሜቱን ገልጿል።
የድራማው አዘጋጅ ዳላስ ጄንኪንስ በበኩሉ፥ 'The Chosen' የተሰኘ ድራማ ተከታታይ ክፍልን ለማዘጋጀት በተጠቀማቸው የመጨረሻ ግብ ቁልፍ ነጥቦች ላይ ተወያይቷል። የተሳካ ትርዒት ማዘጋጀት ለእርሱ አስፈላጊ እንደሆነ ተናግሮ ነገር ግን የመጨረሻ ተልዕኮው ዘወትር ተመልካቾችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ማንነት ማመላከት እንደሆነ ገልጿል። ከ 30% በላይ የሚሆኑት የ 'The Chosen' ድራማ ታዳሚዎች ከክርስትና እምነት ጋር ግንኙነት የሌላቸው በመሆናቸው ታዳሚዎቹን ከቅዱስ ወንጌል ታሪኮች ጋር ማስተዋወቅ መቻል ለእርሱ እጅግ ጠቃሚ የሥራው ክፍል እንደሆነ አስረድቷል።
ጄንኪንስ እንዳብራራው ትርዒቱ አማኞች ያልሆኑ ሰዎችን ብቻ ሳይሆን አማኞች የሆንን እኛንም ጥያቄዎችን እንድንጠይቅ በመጋበዝ አሁንም መማር ያለብን ብዙ ነገሮች እንዳሉ የሚያሳይ መሆኑን አስረድቷል።
ከተከታታይ ድራማዎች ባሻገር
በመግለጫው ወቅት ከተዋኒያን እና ከቡድኑ አባላት ጋር በተደረገው ውይይት፥ የአዲሱ ሰሞን ትርዒቶች ከትርዒትነት በተጨማሪም በዓለማችን ውስጥ እየጨመረ ስላለው አለመረጋጋት እና እንዲሁም የወንጌልን መልዕክት መከተል በዓለማችን ውስጥ ሰላምን የሚያመጣ መሆኑ ተነግሯዋል።
“በሰብዓዊነታችን እርስ በርስ መገናኘት ከቻልን ዓለማችን ውብ ሥፍራ ይሆን ነበር” ያለው ተዋናይ ዮናተን ሩሚ፣ የዸም መሪዎች “የዓለማችንን ችግሮች ለመፍታት ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ ምሳሌ ሊጠቀሙት ይገባል” ሲሉ አሳስበዋል።
ከመግለጫው በኋላ ተዋንያኑ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የኅብረት ፎቶግራፎችን ተነስተው ከአድናቂዎቻቸው ጋርም ተገናኝተው ስለ ልምዳቸው ተነጋግረዋል። በርካታ አድናቂዎች፥ ትርዒቶቹ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥራዎች እና አስተምህሮዎች ላይ ያላቸውን አመለካከት የለወጠ መሆኑን ገልጸው፥ ለተዋኒያኑ ስጦታዎችን ለማቅረብ እና ታሪኮቻቸውን ለመናገር ጓጉተው እንደ ነበር ተመልክቷል።
በምሽት በቫቲካን የቀረበውን የአዲሱ ሰሞን የምዕራፍ አራት ልዩ ትርዒት ተዋኒያኑ እና ታዳሚዎች በኅብረት ያዩት ሲሆን፥ ጄንኪንስ ይህን ክፍል የመረጠበት ምክንያት ጠቃሚ የሆኑ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ታሪችን የሚያሳይ፣ በተዋኒያኑ እና በቡድኑ ላይ ስሜታዊ ተጽእኖን ያሳደረ በመሆኑ እንደሆነ አብራርቷል።