የሶርያ ከተማ በሆነችው ደማስቆ በሚገኘው የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በደረሰ የአጥፍቶ መጥፋት ጥቃት ከሃያ በላይ ሰዎች መሞታቸው ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
በደማስቆ ቤተክርስትያን ላይ በተፈፀመ የአጥፍቶ መጥፋት ጥቃት ቢያንስ 20 ሰዎች ሲገደሉ 63 ሰዎች ቆስለዋል ሲል የሶሪያ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ያስታወቀ ሲሆን፥ በአደጋውም የቤተክርስቲያኑ የመሰዊያ ሥፍራ እና በመስታወት የተሸፈኑት ምሶሶዎች ከባድ ጉዳት እንደደረሰባቸው ከስፍራው የወጡ መረጃዎች አሳይተዋል።
ሰኔ 15 ቀን 2017 ዓ.ም. እሁድ ምሽት በዲዊላ ሰፈር ውስጥ በሚገኘው ነቢዩ ኤልያስ የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ውስጥ በፀሎት ሥነ ስርዓት ላይ አንድ ሰው ፈንጂ በማፈንዳቱ 20 ሰዎች ሲገደሉ 63 ሰዎች መቁሰላቸውን የሃገሪቱ የጤና ጥበቃ ሚንስቴር ባረጋገጠበት በዚህ ጥቃት፥ የሶሪያ መገናኛ ብዙሃን መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የቦምብ ፍንዳታው በቤተክርስቲያኑ መግቢያ ላይ የተፈፀመ ሲሆን፥ በህንፃው ውስጥም ሆነ በአቅራቢያው የነበሩ ሰዎች ህይወትን መቅጠፉ ገልጸዋል።
የሶሪያ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር እስካሁን ድረስ ለጥቃቱ ሃላፊነቱን የወሰደ ቡድን እንደሌለ ጠቅሶ፥ ጥቃቱን የፈጸመው ግለሰብ እስላማዊ መንግስት እየተባለ የሚጠራው ቡድን አባል እንደነበር ይፋ አድርጓል።
የዓይን ምሥክር የሆነው ላውረንስ ማማሪ ለጋዜጠኞች እንደተናገረው “አንድ ሰው መሳሪያ ይዞ ከውጭ ወደ ቤተክርስቲያኑ ውስጥ ገብቶ መተኮስ እንደጀመረ፥ ራሱን ከማፈንዳቱ በፊት ሰዎች ሊያስቆሙት ሞክረው እንደነበር አብራርቷል።
በአቅራቢያው ባለ ሱቅ ውስጥ የነበረ ሌላ ሰው ደግሞ የተኩስ ድምጽ መስማቱን እና ፍንዳታውን ተከትሎ መስታወት ሲሰባበር፥ በቤተክርስቲያኑ ውስጥ እሳት ተነስቶ የእንጨት አግዳሚ ወንበሮች ስብርባሪ እስከ መግቢያው ድረስ ሲፈነጣጠሩ ማየቱን ተናግሯል።
የግሪክ ኦርቶዶክስ ፓትርያርክ የአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን ባወጣው መግለጫ “በአምላካዊ ሥርዓተ ቅዳሴ ላይ በክፉው እጅ ተመታን፣ ሕይወታችንን ቀጠፈ፣ በዛሬው ዕለት በሰማዕትነት የሞቱት ወገኖቻችንን አምላክ ነብስ ይማር” በማለት ሃዘኑን ገልጿል።
የፓትርያርኩ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሶሪያ ጊዜያዊ ባለሥልጣናት “የአብያተ ክርስቲያናትን ቅድስናን በመረዳት ለተፈጠረው እና እየተፈጸመ ላለው ነገር ሙሉ ኃላፊነት እንዲወስዱ እና ለዜጎች ሁሉ ጥበቃ እንዲያደርግ” ጥሪ አቅርቧል።
የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር አናስ ኻታብ እንዳሉት ከሚኒስቴሩ የተውጣጡ ልዩ ቡድኖች "የሚያስወቅስ ወንጀል" ብለው የጠሩትን የጥቃት ሁኔታዎች መመርመር መጀመራቸውን ገልጸው፥ “እነዚህ የሽብር ድርጊቶች የሶሪያ መንግስት ህዝባዊ ሰላምን ለማስፈን የሚያደርገውን ጥረት አያስቆምም" ሲሉም አክለዋል።
የተባበሩት መንግስታት የሶሪያ ልዩ መልዕክተኛ ፅህፈት ቤት ሃላፊ በበኩላቸው ጥቃቱን አውግዘው ሶሪያውያን “ሽብርተኝነትን፣ ጽንፈኝነትን፣ ማነሳሳትን እና የትኛውንም ማህበረሰብ ኢላማ የሚያደርጉ ጥቃቶችን በመቃወም አንድ እንዲሆኑ” አሳስበዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ ልዩ መልዕክተኛ ቶም ባራክ እንዳሉት “እነዚህ አጸያፊ የፈሪነት ድርጊቶች ሶሪያውያን እያሳዩት ባለው የተቀናጀ የመቻቻል እና የመደመር ተግባራት ውስጥ ምንም ቦታ የላቸውም” ያሉ ሲሆን፥ የተባበሩት መንግስታት በየካቲት ወር ባወጣው ዘገባ የአይ.ኤስ እና አጋሮቹ ስጋት አሁንም ከፍተኛ መሆኑን በማሳሰብ፥ ቡድኑ በሶሪያ ያለውን የሽግግር እድል በመጠቀም ጥቃቶችን በማባባስ እና ሀገሪቱን የውጪ ተዋጊዎችን የመመልመያ ማዕከል ሊያደርጋት እንደሚችል ማስጠንቀቁ ይታወሳል።
የሶሪያ የማስታወቂያ ሚንስትር ሃምዛ ሙስጣፋ በበኩላቸው ድርጊቱ የአሸባሪዎች ጥቃት መሆኑን በኤክስ ገፃቸው ላይ በለጠፉት ጽሁፍ ገልጸው፥ “ይህ የፈሪዎች ድርጊት እኛን እርስ በርስ የሚያቀራርቡንን የዜግነት እሴቶቻችንን የሚጻረር ነው” በማለት ከገለጹ በኋላ፥ ሁሉም ዜጎች እኩል መብት እንዳላቸው ለማረጋገጥ ከገቡበት ቁርጠኝነት ወደ ኋላ እንደማይመልሳቸው፥ እንዲሁም መንግስት ወንጀለኛ ድርጅቶችን ለመዋጋት እና የህብረተሰቡን ደህንነት አደጋ ላይ ከሚጥሉ ጥቃቶች ለመጠበቅ ሁሉንም ጥረቶችን ለማድረግ ቃል መግባቱን አረጋግጠዋል።
የአንጾኪያ እና የመላው ምስራቅ የግሪክ ኦርቶዶክስ ሃገረ ስብከት ረዳት ጳጳስ የሆኑት ብጹእ አቡነ ሞይስ ሙሳ ኤል ግለሰቡ የእጅ ቦምብ ወደ ቤተክርስቲያኑ መወርወሩን የገለጹ ሲሆን፥ በሌላ በኩል ‘ዋይት ሄልሜትስ’ በመባል የሚታወቀው የሶሪያ ሲቪል መከላከያ ቦታው ላይ ደርሶ በቤተክርስቲያኑ ውስጥ የተደረማመሱ ምሰሶዎችን እና ጉዳት የደረሰባቸውን አግዳሚ ወንበሮችን ጨምሮ የጥፋት ተግባሩን ውጤት የሚያሳዩ ቪዲዮዎችን መውሰዱ ተገልጿል።
ይህ የአጥፍቶ ጠፊ ጥቃት የሶሪያው ፕሬዝዳንት አህመድ አል ሻራ በታህሳስ ወር ላይ የቀድሞውን የሃገሪቱ ፕረዚዳንት ባሽር አል አሳድን አስወግደው ስልጣን ከያዙ በኋላ በደማስቆ የተፈጸመ የመጀመርያው ጥቃት መሆኑ ተገልጿል።
የቅዱስ ኤልያስ ግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በደማስቆ ውስጥ ካሉ ታላላቅ የክርስትና ቤተ ክርስቲያናት አንዷ ስትሆን፣ በጥልቅ መንፈሳዊ እና ታሪካዊ ጠቀሜታዋ ትታወቃለች። በነቢዩ ኤልያስ ስም የተሰየመችው ቤተ ክርስቲያን በሃይማኖታዊ በዓላት ወቅት ለምእመናን ወሳኝ የመሰብሰቢያ ቦታ ሆኖ የሚያገለግል ሲሆን የተለያዩ የማህበረሰብ እንቅስቃሴዎችንም ታስተናግዳለች። የአል አረቢያ ሶሪያ ዘጋቢ እንደገለጸው ቤተ ክርስቲያኑ "በደማስቆ ውስጥ የክርስትና መገኘት ዘላቂ ምልክቶች አንዱ" ሲሆን፣ ዒላማ መደረጓም "በሶሪያ ዋና ከተማ ውስጥ ያለውን መረጋጋት እና የሃይማኖቶች መቻቻልን ለማናጋት ያለመ ክፉ መልእክት" መሆኑን አብራርተዋል።
በቅዱስ ኤልያስ ቤተ ክርስቲያን ላይ የተፈጸመው አሰቃቂ ጥቃት የሶሪያን ጦርነት ጥልቅ ቁስሎችን እንደገና የሚያድስ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፥ ጥቃቱ በድንጋይ ግድግዳዎች ላይ የተፈጸመ ጥቃት ብቻ ሳይሆን በእምነት፣ በተስፋ እና የክርስትና መገኘት ላይ የተሰነዘረ ቀጥተኛ ጥቃት ነው ተብሏል።
የግሪክ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥቃቱን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ ይሄንን ‘አስጸያፊ የአሸባሪዎች የአጥፍቶ መጥፋት ጥቃት’ በማውገዝ፥ “የሶሪያ የሽግግር ባለስልጣናት በጥቃቱ ላይ የተሳተፉትን ተጠያቂ ለማድረግ እና የክርስቲያን ማህበረሰቦችን እና ሁሉንም የሃይማኖት ቡድኖችን ደህንነት ለማረጋገጥ እርምጃዎችን እንደሚወስድ ጠቅሶ፥ የማንኛውም ሃይማኖት ተከታይ ያለ ፍርሃት የመኖር መብት አለው በማለት ገልጿል።