በራፋህ እርዳታ በመጠባበቅ ላይ የነበሩ ፍልስጤማውያን በእስራኤል ጥቃት መገደላቸው ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ራፋህ በሚገኘው በአሜሪካ እና በእስራኤል የሚደገፈው የጋዛ ሰብዓዊ ፋውንዴሽን (ጂኤችኤፍ) ማዕከል እርዳታ ሲጠብቁ የነበሩ ፍልስጤማዊያን ላይ የእስራኤል ወታደሮች ባደረሱት ጥቃት በትንሹ 24 ሰዎች ሲሞቱ በደርዘን የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን የጋዛ የጤና ባለስልጣናት ገልጸዋል።
የጋዛ የጤና ባለስልጣናት ክስተቱን አስመልክተው እንደተናገሩት ጥቃቱ የተከሰተው በምዕራብ ራፋህ ውስጥ በሚገኘው የሰብአዊ እርዳታ ማዕከል ላይ በርካታ ህዝብ እርዳታ ለመቀበል በተሰበሰበበት ወቅት እንደሆነ ተናግረዋል።
ዸም አቀፉ ቀይ መስቀል 179 ተጎጂዎች በሆስፒታሉ መቀበሉን በመግለጽ ከነዚህም ውስጥ 21 ሰዎች መገደላቸውን ይፋ ያደረገ ሲሆን፥ በሐማስ የሚመራው የሲቪል መከላከያ ኤጀንሲ በበኩሉ የተገደሉ ፍልስጤማውያንን ቁጥር 31 መድረሱን ገልጿል።
የእስራኤል ጦር በበኩሉ ወታደሮቹ በእርዳታ ማከፋፈያው ማዕከል ወይም አቅራቢያ ላይ በሲቪሎች ላይ ተኩስ ከፍተዋል መባሉን በማስተባበል፥ ክስተቱ የተከሰተው ህዝቡ ከተፈቀደው መንገድ ውጪ ወደ ዕርዳታ ማከፋፈያ ቦታ መንቀሳቀስ በጀመረበት ወቅት መሆኑን ገልጿል።
የእስራኤል ጦር ሰኞ ዕለት በሰጠው መግለጫ በጋዛ ሰርጥ የሚያደርጋቸውን የምድር ላይ ዘመቻዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል መግለጹ ይታወሳል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የግብፁ ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ እና የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በፍልስጤም ጉዳይ ላይ በማተኮር በቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸው የተነገረ ሲሆን፥ አል ሲሲ ፈረንሳይ ለፍልስጤማዊያን መብት መከበር የምታደርገውን ድጋፍ በደስታ እንደሚቀበሉ በመግለጽ፥ ግብፅ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ፣ የታጋቾችን ልውውጥ ለማመቻቸት እና ሰብአዊ እርዳታ በጋዛ ለሚገኙ ሲቪሎች መድረሱን ለማረጋገጥ የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልጸዋል።
በሌላ ዜና በሳምንቱ መጨረሻ የአረብ እስላማዊ የሚኒስትሮች ኮሚቴ ልኡካን ቡድን ጦርነቱን ለማስቆም እና የፍልስጤማዊያንን ሉዓላዊነት ለመደገፍ ያለውን ቁርጠኝነት ያረጋገጠ ሲሆን፥ የልዑካን ቡድኑ ወደ ራማላህ ሊያደርገው ያቀደውን ጉብኝት እስራኤል መከልከሏን ተከትሎ ከፍልስጤም ፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስ ጋር አማን ላይ በመገናኘት ስለቀጠናው ውይይት እንዳደረጉ ተገልጿል።
በውይይቱም ፕረዚዳንት ማህሙድ አባስ ኮሚቴው ዸም አቀፍ ድጋፍን በማሰባሰብ እና የሁለት ሀገራት መፍትሄ እንዲመጣ እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀዋል።