በእስራኤል እና ኢራን መካከል ያለው ውጥረት ተባብሶ ቀጥሏል
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
እስራኤል እና ኢራን በትናንትናው ሌሊት አዲስ የሚሳኤል ጥቃት በመሰንዘር ቀድሞውኑ የቀጠናውን እና ዸም አቀፍ ትኩረት ያገኘውን ግጭት ማባባሱ ተነግሯል።
የኢራን ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አሜሪካ በግጭቱ ውስጥ የምትሳተፍ ከሆነ ቀጠናው "ሲኦል" ይሆናል ሲሉ ተናግረው የነበር ሲሆን፥ ኢራን በትናንትናው ዕለት በፈጸመችው የሚሳኤል ጥቃት ከሆስፒታል አቅራቢያ ያለ ወታደራዊ ስፍራ ማነጣጠሩን ገልፃለች።
ኢራን ባስወነጨፈቻቸው ሚሳኤሎች በደቡባዊ እስራኤል ባርሺባ ከተማ የሚገኘውና በእስራኤል ትልቁ ከሚባሉት አንዱ የሆነውን ሶሮካ ሆስፒታል መመታቱን እስራኤል አስታውቃለች።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በእስራኤል እና ኢራን ግጭት አስቸኳይ ስብሰባ ሊያካሂድ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፥ የእስራኤል የድንገተኛ አደጋ አገልግሎት ሃላፊ የሆኑት ማጌን ዴቪድ አዶም እንደገለጹት በቤርሳቤህ በሚገኘው የሶሮካ ህክምና ማዕከል ላይ በቀጥታ የተቃጣውን የኢራን ጥቃት ጨምሮ ቢያንስ 89 ሰዎች መቁሰላቸውን ገልጸዋል። የእስራኤል ባለስልጣናት ምንም እንኳን በሰው ህይወት ላይ የደረሰ ጉዳት መኖሩን ባያረጋግጡም ሆስፒታሉ ግን ጉዳት እንደደረሰበት ተናግረዋል።
እስራኤል አጸፋውን ለመመለስ ዝታለች
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የኢራን መሪዎች ለጥቃቱ “ከፍተኛ ዋጋ እንደሚከፍሉ” በማስጠንቀቅ አጸፋውን እንደሚወስዱ የዛቱ ሲሆን፥ በኢራን መንግስት የሚተዳደረው ሚዲያ በበኩሉ ሚሳኤሉ ከሆስፒታሉ አጠገብ በሚገኘው የእስራኤል የስለላ ተቋም እና በወታደራዊ ማዘዣ ማእከል ላይ ያነጣጠረ መሆኑን ገልጿል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ እስራኤል የኒውክሌር ማበልጸጊያ ከሚገኙባቸው የኢራን ከተሞች ከሆኑት ኮንዳብ እና አራክ ነዋሪዎች ለቀው እንዲወጡ ያስጠነቀቀች ሲሆን፥ ይህም ወሳኝ በሆኑ ቦታዎች ላይ ጥቃት ሊደርስ እንደሚችል ያሳያል ተብሏል።
የእስራኤል ጦር በአረብኛ እና በፋርሲ ቋንቋ ሲቪሎች በአስቸኳይ ስፍራውን ለቀው እንዲወጡ የማስጠንቀቂያ መልዕክት ያወጣ ሲሆን፥ እሮብ ዕለት አመሻሹ ላይ እስራኤል የወሰደችውን ጥቃት ተከትሎ ከኢራን የተረጋገጠ የተጎጂዎች ቁጥር እስካሁን አልተገኘም።
እየተባባሰ የመጣው ቀውስ
ይህ በእንዲህ እንዳለ በጋዛ ቢያንስ 18 ፍልስጤማውያን ሃሙስ ማለዳ ላይ እስራኤል ባደረሰችው የአየር ድብደባ መገደላቸውን የሲቪል መከላከያ ምንጮች የገለጹ ሲሆን፥ አብዛኛዎቹ ተጎጂዎች በማእከላዊ ጋዛ በሚገኘው የእርዳታ ማከፋፈያ ጣቢያ አከባቢ የአደጋ ጊዜ እርዳታ እየጠበቁ ነበር ተብሏል።
የእስላማዊ ትብብር ድርጅት አስቸኳይ ጉባዔ ለማድረግ ለአባል ሀገሮች ጥሪ ያቀረበ ሲሆን፥ የድርጅቱ ጉባዔ የሚደረገው በቱርክ ኢስታንቡል ከተማ መሆኑን አስታውቋል። የፊታችን ቅዳሜ ሰኔ 14 ቀን 2017 ዓ.ም. የሚካሄደው የድርጅቱ አስቸኳይ ጉባዔ የተጠራው፤ እስራኤል በኢራን ላይ ጥቃት በመሰንዘር ሁለቱ ሀገሮች ወደ ጦርነት በገቡበት ወቅት ነው።
የኢራቅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፉአድ ሁሴን በዚህ ሳምንት መጨረሻ በኢስታንቡል በሚካሄደው የእስላማዊ ትብብር ድርጅት ጉባኤ ላይ የአረብ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችን አስቸኳይ ስብሰባ የጠሩ ሲሆን፥ ከግብፅ አቻቸው ጋር ባደረጉት ጥሪ ወቅት የቀረበው ሀሳብ፣ እየተባባሰ ለመጣው ቀውስ ክልላዊ ምላሽን ለማስተባበር ያለመ ነው ብለዋል።
በሌላ ዜና፣ በሞስኮ የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ማንኛውም የዩናይትድ ስቴትስ ወታደራዊ ተሳትፎ ጦርነቱ “ሌላ አስከፊ የመስፋፋት ሂደት” እንደሚያስከትል አስጠንቅቀዋል።