የቀድሞ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ኦልመርት ‘እርቅ ብቻ ሳይሆን ጦርነቱን ማቆም ያስፈልገናል’ ማለታቸው ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የቀድሞው የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ኢሁድ ኦልመርት ከላ ኦዘርቫቶሬ ሮማኖ እና ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በጋዛ ስላለው ግጭት አንስተው አሁን ባለው የመንግስት አካሄድ ላይ ጠንካራ ትችት የሰጡ ሲሆን፥ ኦልመርት “ከሁለቱ መንግስታት የጋራ የሆነ ገለልተኛ፣ ነፃ እና ሰላማዊ መንገድ ውጭ ሌላ አማራጭ የለም” በማለት ካሳሰቡ በኋላ፥ ለጋዛ ደግሞ ብቸኛው አዋጭ መፍትሄ ጦርነቱን በአስቸኳይ ማቆም እና ታጋቾችን በሰላም ወደየቤታቸው መመለስ ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የቀድሞ የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ኢሁድ ኦልመርት ከአንድ ወር በፊት እስራኤል በጋዛ ላይ የምታካሂደውን ጦርነት “ያለ ዓላማ የሚደረግ” በማለት ተችተው የነበረ ሲሆን፥ አክለውም በፍልስጤም ግዛት የሚፈፀመውን ጥቃት ማስቆም የሚችሉት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ብቻ እንደሆኑ በመግለጽ፥ ኔታንያሁ “ፖለቲካዊ ጦርነት” እያካሄዱ እንደሆነ እና የእስራኤል ወታደሮች በጋዛ እና በዌስት ባንክ “የጦር ወንጀሎችን” እንደፈፀሙ እና ከጦርነቱ ምንም ውጤት እንደማይገኝ ጠቁመው “በዚህ የሚከፈል ዋጋ የሚያስቆጭ” ነው ሲሉ ተደምጠዋል።
በጋዛ ጦርነት ሂደት ውስጥ ስላሉት ወንጀሎች በቅርቡ የሰጡት መግለጫ የዸምን ትኩረት መቀስቀሱ እና በእነዚህ መደምደሚያዎች ላይ እንዴት እንደደረሱ ከቫቲካን ሚዲያ የተጠየቁት አቶ ኦልመርት፥ አሁን ያለው የእስራኤል መንግስት በጋዛ ወንጀል ፈጽሟል ሲሉ በድጋሚ ከከሰሱ በኋላ ነገር ግን በጋዛ ውስጥ ያለው ጦርነት እና እነዚህ ወንጀሎች በ "የጦርነት ወንጀሎች" የህግ ምድብ ውስጥ መጠቃለሉን ለማረጋገጥ ዝርዝር መረጃዎች እንደሌላቸው በመጥቀስ፥ ሆኖም በዚህ ደረጃ፣ አሁን ሳይሆን ቀደም ብሎ፣ ታጋቾቹን ለመታደግ ከኔታንያሁ መንግሥት ምንም ዓይነት ትክክለኛ ጥረቶች እንዳልተደረጉ በማረጋገጥ፥ የዚህ ጦርነት ውጤቶች የበለጠ ለእስራኤል ወታደሮች ሞት፣ እስራኤላዊያን በሃማስ መታገታቸው መቀጠሉ እና የበርካታ ንፁሀን ፍልስጤማዊያን መገደል ብቻ ሊሆን እንደሚችል ገልጸው፥ በእነዚህ ምክንያቶች እና ሁኔታዎች ውስጥ ጦርነቱ በተጨባጭ ወንጀል መሆኑ ግልጽ ነው ሲሉ አስረድተዋል።
በጉዳዩ ላይ መግለጽ የፈለጉት ይሄንን መሆኑን በመጥቀስ በዌስት ባንክ ላይ ተመሳሳይ ችግር እየተፈጠረ እንደሆነ፥ በፍልስጤም ህዝብ ላይ በሰፋሪዎች የሚፈጸመው ጥቃት ፖሊስም ሆነ መከላከያ ሰራዊት ምንም ሳያደርግ መቀጠሉን ገልጸዋል።
የእርቅ ስምምነት ላይ ለመድረስ እና ጦርነቱን ለማቆም ምን ዓይነት እርምጃዎች መወሰድ እንዳለባቸው የተጠየቁት ኦልመርት፥ በእሳቸው እምነት በግብፅ፣ በኳታር እና በዩናይትድ ስቴትስ አደራዳሪነት በተደረገው ድርድር መሰረት ሁሉም ታጋቾች እንዲፈቱ ጦርነቱን ለማቆም መስማማት እንደሚገባ ያላቸውን እምነት ገልጸው፥ ይሄንን ሃማስ ለመቀበል ዝግጁ መሆኑ እንደተዘገበ በማስታወስ፥ ሃማስ ጦርነቱን በዘላቂነት ማቆም ካልተቻለ በማንኛውም ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት እንደማይስማማ፣ ይህ ከሆነ ግን ታጋቾቹን በሙሉ እንደሚለቅ አስታውቆ የነበረ መሆኑን አንስተው፥ ይህ ማለት ለሃማስ የወንጀለኞች ቡድን ጥያቄ መገዛት ሳይሆን፥ ታጋቾቹ አሁን ላይ ብቸኛ ቀሪ መያዣቸው መሆኑን እና ሃማስ ጦርነቱ በዘላቂነት የማቆም ስምምነት ላይ ካልተደረሰ ታጋቾቹን አሳልፎ እንደማይሰጥ በመረዳት ይሄንን እንደተናገሩ አብራርተው፥ በማከልም “አሁን ማድረግ የምንችለው ትክክለኛ ነገር ጦርነቱ በይፋ መቆሙን በማወጅ ታጋቾቹን ወደ ቤት መመለስ ይቻላል ብዬ አምናለሁ” በማለት ሃሳባቸውን ገልጸዋል።
በቤንያሚን ኔታንያሁ መንግስት እና በዶናልድ ትራምፕ ስር ባለው የአሜሪካ አስተዳደር መካከል ያለው ግንኙነት በአሁኑ ወቅት ጥሩ እንዳልሆነ እና በዚህ ላይ የእርሳቸው አመለካከት ምን እንደሆነ ተጠይቀው፥ አሁን ያለውን የእስራኤል እና የአሜሪካ ግንኙነት ሁኔታ ለመረዳት በጣም ከባድ መሆኑን በመጠቆም፥ ትራምፕ ብዙ ሰው እንደሚስማማበት በትክክል የማይገመቱ ፖለቲከኛ እንደሆኑ አንስተው፥ ስለዚህ በጠንካራ መሰረት ላይ ያረፉ ወይም የበፊቱን የግንኙነት ደረጃዎች የሚመጥኑ ነገሮችን መጠበቅ ከባድ እንደሆነ ከገለጹ በኋላ፥ ከቅርብ ጊዜዎቹ እርምጃዎች በመነሳት ትራምፕ የራሳቸውን ጥቅም ብቻ ለማስጠበቅ እንደሚሰሩ መልዕክት እያስተላለፉ እንደሆነ፥ ብሎም ከኔታንያሁ የተለየ አጀንዳ አላቸው ብዬ አስባለሁ ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በቅርቡ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ወደ ባህረ ሰላጤው ሃገራት ባደረጉት ጉብኝት ወደ እስራኤል ሳይጓዙ ከሳዑዲዎች፣ ኳታሮች፣ ኢሚሬቶች እና እንዲሁም ከአዲሱ የሶሪያ ፕሬዝዳንት አል ሻራ ጋር የተገናኙበት ሁኔታ ጉዳዩን በግልፅ ያሳያል ብለዋል።
ተጠባባቂ ወታደሮችን ጨምሮ አብዛኛው የእስራኤል ማህበረሰብ፣ ምንም ተጨባጭ ውጤት ሳይኖረው ማለቂያ የሌለው በሚመስለው ጦርነት እንደተሰላቸ በቃለ ምልልሱ ወቅት የተነሳ ሲሆን፥ በመንግስት ላይ የሚነሱ ተቃውሞዎች እየጨመሩ መምጣታቸውን፥ በዚህም የአመራር ለውጥ ሊኖር ይችል እንደሆን የተጠየቁት ኦልመርት፥ አብዛኛው እስራኤላውያን አሁን ላይ በዚህ መንግስት እና በዚህ ማለቂያ በሌለው ጦርነት እርካታ እንደሌለው ያላቸውን እምነት በመግለጽ፥ በመሠረቱ፣ በእስራኤል ውስጥ ማንም ሰው ኔታንያሁ ምን ዓይነት ስልት እንደሚከተሉ በግልጽ እንደማይረዳ፣ በጋዛ ያለው ወታደራዊ ዘመቻ እና በዌስት ባንክ የተደረገው ወረራ ተሳክቶ የሀማስ ታጣቂዎች እና መሪዎች በሙሉ ተገድለው ወይም ተሰደው ቢሆን ኖሮ ምን ሊከሰት እንደሚችል በመጠየቅ፥ አሁንም በእነዚያ አገሮች አምስት ሚሊዮን ተኩል ፍልስጤማውያን ይኖራሉ ብለዋል።
እስራኤል ስለ ወደፊቱ ጊዜ ምን አስባለች? የሚለው ጥያቄ መመለስ አለበት ያሉት ኦልመርት፥ እነዚህ ህዝቦች ቀስ በቀስ መሬታቸውን እንዲለቁ ማስገደድ ተገቢ እንዳልሆነ፥ በእውነት ይህ አሁን ያለው መንግስት ስልታዊ አካሄድ መሆን እንደሌለበት ብሎም እስራኤል በዚህ መንገድ ከቀጠለች ከዚህ ቀደም የነበራትን ዸም አቀፍ ስም እና ድጋፍ ታጣለች ብለዋል።
በእኛ እና በእነሱ መጪው ጊዜ ላይ ምን ማድረግ እንደምንፈልግ በግልጽ መታወቅ አለበት ያሉት ኦልመርት፥ መሬታቸውን ላልተወሰነ ጊዜ ይዞ መቆየት ነው? ወይንስ አካሄዳችንን ቀይረን የሁለት ተጎራባች እና ሰላማዊ መንግስታት ሃገር ሆኖ ከመቀጠል በስተቀር ሌላ መፍትሄ እንደሌለ ተረድተናል? በማለት በጥያቄ አጠቃለዋል።