MAP

ወትሮውን በጎብኚዎች ይጨናነቅ የነበረው በዌስት ባንክ ቤተልሔም ውስጥ የሚገኝ ጎዳና ጥቅምት 2017 ዓ.ም. ላይ ያለው እይታ ወትሮውን በጎብኚዎች ይጨናነቅ የነበረው በዌስት ባንክ ቤተልሔም ውስጥ የሚገኝ ጎዳና ጥቅምት 2017 ዓ.ም. ላይ ያለው እይታ  

የቤተልሔም ከተማ ነዋሪዎች በቀጠናው ያለው ሁኔታ እየተባባሰ በመምጣቱ ሥራ እና መሬታቸውን እያጡ እንደሆነ ተገለጸ

በእየሩሳሌም የሚገኘው እና ጳጳሳዊ ተልዕኮ የሆነው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የምስራቅ ሃገራት የበጎ አድራጎት ማህበር (CNEWA) ክልላዊ ዳይሬክተር የሆኑት ጆሴፍ ሃዝቦን እንደገለጹት በፍልስጤም ዌስት ባንክ ሥር ባለችው የቤተልሔም ከተማ ነዋሪዎች የሥራ-አጥነት ሁኔታ ወደ 31 በመቶ ከፍ ማለቱን እና የቱሪስቶች ቁጥር መቀነስ በኑሮአቸው ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ማሳደሩን ተናግረዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በኢየሩሳሌም የሚገኘው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን በጎ አድራጎት ጳጳሳዊ ተቋም ክልላዊ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ጆሴፍ እንደገለጹት የዓለሙ ማህበረሰብ አይን በጋዛ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ላይ አተኩሮ ባለበት በአሁኑ ወቅት፥ በፍልስጤም ዌስት ባንክ ቤተልሔም እና በዙሪያዋ ያሉ ማህበረሰቦች የኑሮ ሁኔታ እየተባባሰ መምጣቱን ጠቁመዋል።

ሥራ አጥነት ወደ 31 በመቶ ከፍ ማለቱን፣ እንዲሁም በጦርነቱ ምክንያት ቤተልሔም ከቱሪዝም ገቢ ታገኝ የነበረውን በየቀኑ በግምት 2.5 ሚሊዮን ዶላር እንደምታጣ የገለጹት አቶ ጆሴፍ፥ ይህም በአካባቢው ያሉ ሱቆች፣ ምግብ ቤቶች እና የባህል ተቋማት እንዲዘጉ በማድረጉ የፍልስጤም ቅርስ ጥበቃን ስጋት ላይ የጣለው መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከእነዚህ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በተጨማሪ እንደ ገና እና ፋሲካ ያሉ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ በዓላት ተጠናክሮ በቀጠለው ጦርነት ምክንያት የማይከበሩ ሲሆን፥ በአንድ ወቅት የክርስቲያን ከተማ ትባል ከነበረችው ቤተልሔም በርካታ ቤተሰቦች የተለያዩ ዕድሎችን ፍለጋ ወደ ሌላ ቦታ እየተሰደዱ መሆኑ ተገልጿል።

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የምስራቅ ሃገራት የበጎ አድራጎት ማህበር የሰኔ ወርን አስመልክቶ ባወጣው ዘገባ፣ የእስራኤል መንግስት በሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን የሥራ ፈቃዶችን መሰረዙን ይፋ ያደረገ ሲሆን፥ አቶ ጆሴፍ ከሪፖርቱ ጋር በላኩት ኢሜል ስለ አንድ ቤተሰብ ተሞክሮ በማንሳት እንደፃፉ እና በዚህም ‘ኤም’ የተባለ ግለሰብ በእስራኤል ውስጥ ይሠራ እንደነበረ፥ ነገር ግን ጦርነቱ ከተቀሰቀሰበት መስከረም 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ፈቃዱ መሰረዙን ጽፈዋል።

በዚህም ምክንያት አቶ ‘ኤም’ በደረሰበት የገንዘብ እጥረት እረፍት አልባ እና አቅመ ቢስ በመሆኑ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው የቤተሰቡ አባላት የሆኑትን ሚስቱን እና ሴት ልጁን ማስተዳደር እንዳልቻለ እና የቤት ውስጥ ኑሮን አስቸጋሪ እንዳደረገ ገልጸዋል።

ከሦስት ወራት በፊት ለአንዳንድ ሰዎች ምስጋና ይግባውና የሦስት ወር የሥራ ፈቃድ አውጥተውለት እንደነበር ያስታወሱት አቶ ጆሴፍ፥ በእነዚህ ጊዜያት አመለካከቱ እና አኗኗሩ በሙሉ በመቀየሩ፥ ወጣቶቹ ባልና ሚስት በመጨረሻ ሁለተኛ ልጃቸውን ለመውለድ ማሰብ እንደጀመሩ አስታውሰው፥ ሆኖም ግን ፈቃዱ ባለመታደሱ አቶ ኤም እንደገና ሥራ አጥ መሆኑን በሃዘኔታ ከገለጹ በኋላ፥ “ይህ በጦርነቱ ምክንያት ያለ ወንጀላቸው እና ያለ ጥፋታቸው እየተሰቃዩ ከሚገኙት በሺዎች ከሚቆጠሩ ሰዎች መካከል አንዱ ማሳያ ብቻ ነው” ብለዋል።

የአቶ ጆሴፍ ሪፖርት ያተኮረው በቤተልሔም ጠቅላይ ግዛት፣ ከኢየሩሳሌም በስተደቡብ የሚገኝ አካባቢን፣ ቤተልሔምን የሚያካትተውን ዌስት ባንክን፣ አንዳንድ መንደሮችን እና ሦስት የስደተኞች ካምፖችን ያካተተ ሲሆን፥ እስራኤል 85 በመቶ የሚሆነውን የዚህን መሬት ስፋት ‘ኤሪያ ሲ’ በማለት እንደሰየመች እና በእስራኤላዊያን ቁጥጥር ሥር እንዳደረገች ይታወቃል።

በጠቅላይ ግዛቱ ውስጥ በአብዛኛው በወታደራዊ ሃይል የሚጠበቁ ኬላዎችን፣ መውጫ እና መግቢያ በሮችን፣ የድንበር አጥሮችን እና የሲሚንቶ ብሎኮችን ያካተቱ በግምት 76 የሚሆኑ እንቅስቃሴን የሚገድቡ መሰናክሎች እንዳሉ የተገለጸ ሲሆን፥ እነዚህም ወደ ሥራ፣ ትምህርት ቤቶች እና የህክምና ማዕከላት የሚወስዱ መንገዶች እንዲዘጉ ማድረጉን አቶ ጆሴፍ ተናግረዋል።

ግንቦት ወር ላይ የእስራኤል ካቢኔ ‘እ.አ.አ. ከ 1967 ጀምሮ ለመጀመሪያ ጊዜ እና የዸም አቀፍ ህግን በመጣስ’ የመጨረሻው የመሬት ባለቤትነት መብት ምዝገባ እንዲጀምር ማፅደቁ የሚታወስ ሲሆን፥ አቶ ጆሴፍ እንደጠቆሙት በዚህ ውሳኔ መሰረት ፍልስጤማዊያን በራሳቸው መሬት ላይ መብታቸውን ማረጋገጥ ስለሚከብዳቸው ወደ ከባድ ችግር እንደሚመራቸው ይጠበቃል ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ የቅርብ ምሳሌዎችን በመጥቀስ በእስራኤላውያን ሰፈሮች ዙሪያ እንደ ማቋቋሚያ ዞኖች የተያዘውን መሬት ጨምሮ፣ የእስራኤል መንግስት በቤተልሔም ውስጥ መሬቶችን መያዙን እንደቀጠለ ገልጸዋል።

ጳጳሳዊ ተቋም የሆነውን የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የምስራቅ ሃገራት የበጎ አድራጎት ማህበር እና አጋሮቹ ጊዜያዊ የስራ እድሎችን፣ አነስተኛ የጤና እንክብካቤ ድጋፎችን በተለይ ለሴቶች እና ህጻናት፣ የማህበራዊ አገልግሎት ፕሮጀክቶችን እና በቤተልሔም አካባቢ ያሉ ሌሎች የገንዘብ ችግር ያለባቸው አጋር ተቋማትን መደገፉን አጠናክሮ መቀጠሉ የተገለጸ ሲሆን፥ ከዚህም በተጨማሪ ከጳጳሳዊ ተቋሙ ጋር የሚሰሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተማሪዎቹ በዳር አል-ቃሊማ ዩኒቨርሲቲ እና በቤተልሔም ዩኒቨርሲቲ እንዲማሩ እገዛ እያደረጉ እንደሆነ ተገልጿል።

አቶ ጆሴፍ በመጨረሻም እንደተናገሩት አንዱ በአስቸኳይ እርዳታ ይፈልግ የነበረው ተቋም፣ እውቅና ያለው ፍትሃዊ የንግድ ድርጅት የሆነው የቅድስት ሀገር የእጅ ሥራዎች ኅብረት ሥራ ማህበር እንደነበር ገልጸው፥ ይህ ድርጅት ምርቶቹን ለዸም አቀፍ ገበያ እንዲያቀርብ ድጋፍ ሊደረግለት ይገባ ነበር ብለዋል።
 

12 Jun 2025, 15:23