እስራኤል በጋዛ በፈጸመችው የአየር ጥቃት 54 ሰዎች መሞታቸው ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የእስራኤል ጦር ግንቦት 18 ቀን 2017 ዓ.ም. በጋዛ ላይ ባደረሰው የአየር ጥቃት ቢያንስ 54 ፍልስጤማውያን የተገደሉ ሲሆን፥ ከነዚህም መካከል በደርዘን የሚቆጠሩ በአንድ ትምህርት ቤት ውስጥ ተጠልለው የነበሩ መሆናቸው ተገልጿል።
በጋዛ ከተማ የሚገኘው ፋህሚ አል-ጃርጋዊ ትምህርት ቤት ውስጥ በእስራኤል ከፍተኛ የቦምብ ጥቃት እየተፈፀመበት ከሚገኘው ቤተ ላሂያ የተፈናቀሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማዊያን ቤተሰቦች ተጠልለውበት የሚገኝ ሲሆን፥ ሰኞ ዕለት እስራኤል ትምህርት ቤቱ ላይ በፈጸመችው ጥቃት ቢያንስ 35 ሰዎች መሞታቸውን የአከባቢው ባለስልጣናት ተናግረዋል።
በጋዛ ሃማስ የሚመራ ሲቪል መከላከያ እንደገለፀው ፍልስጤማዊያኑ አርፈውበት የነበሩ ሁለት የመማሪያ ክፍሎች ላይ በደረሰው ጥቃት ህጻናትን ጨምሮ ብዙዎቹ በእሳት የተቃጠሉ አስከሬኖች ከፍርስራሹ ሥር መገኘታቸውን የጠቆሙ ሲሆን፥ የእስራኤል መከላከያ ሃይል በበኩሉ ጥቃቱ ያነጣጠረው የሃማስ እና ኢስላሚክ ጂሃድ ማዘዣ ማዕከል ላይ መሆኑን ገልፆ፥ አካባቢው “አሸባሪው ሃይል የጋዛን ሕዝብ እንደ ከለላ እየተጠቀመ ጥቃት ለማቀነባበር የሚጠቀምበት ስፍራ ነው” በማለትም ገልጿል።
ከዚህም በተጨማሪ በሰሜን ጋዛ ጃባሊያ በሚገኝ መኖሪያ ቤት ላይ በተፈፀመ ጥቃት 19 ሰዎች መሞታቸው የተዘገበ ሲሆን፥ የእስራኤል ጦር እስከ አሁን ስለ ጥቃቱ እና ኢላማ ስለተደረገበት ነገር የሰጠው መግለጫ የለም።
እነዚህ ሁለት የአየር ድብደባዎች እስራኤል በሰሜን ጋዛ በስፋት እያደረሰችው ያለው የተጠናከረ ጥቃት አካል መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፥ በ48 ሰዓታት ውስጥ 200 ዒላማዎችን መምታቱን የእስራኤል መከላከያ አስታውቆ፥ እነዚህንም "የአሸባሪዎች መቀመጫ" ብሏቸዋል።
በሁለቱ ወገኖች መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ጥረቶች ቢቀጥሉም፣ ባለፈው ሳምንት ፍልስጤማዊ ሐኪም በሚኖርበት ቤት በደረሰ ጥቃት የአንድ ቤተሰብ አባል ከሆኑ 10 ልጆች ዘጠኙ መገደላቸው ይታወሳል።
እስራኤል ለ11 ሳምንታት ጋዛን ሙሉ ከበባ ውስጥ በማስገባት መድኃኒት እና ምግብ ወደ ጋዛ እንዳይገባ ያገደች ሲሆን፥ ወደ ጋዛ ባለፈው ሳምንት 107 እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች እንዲገቡ መፈቀዱን እስራኤል ብትገልጽም፣ ነገር ግን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደገለጸው ወደ ጋዛ በየቀኑ ከ500 እስከ 600 መኪና እርዳታ መግባት እንዳለበት አመላክቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የእስራኤል ጦር ከየመን ወደ እስራኤል የተወነጨፈ ሚሳኤልን ጠልፎ መጣሉን እና በዌስት ባንክ አንዳንድ ክፍሎች የማስጠንቀቂያ ደውሎችን ማሰማቱን ሰኞ ዕለት በሰጠው መግለጫ ያሳወቀ ሲሆን፥ በጥቃቱ ምንም አይነት ጉዳት እንዳልደረሰም ገልጿል።
ከህዳር 2015 ዓ.ም. ጀምሮ የየመን ሁቲ አማጽያን ከፍልስጤማውያን ጋር በመተባበር ሰው አልባ አውሮፕላኖችን እና ሚሳኤሎችን በእስራኤል ላይ ሲያስወነጭፉ እንደነበር ይታወቃል።
እስራኤል በጋዛ በፈጸመችው ጥቃት እስካሁን ቢያንስ 53,939 ሰዎች መገደላቸውንና ከእነዚህም መካከል 16,500 ሕጻናት እንደሆኑ ተገልጿል።
በአከባቢው ሰላም እንዲሰፍን የሚደረጉ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን በመቀላቀል ዮርዳኖስ እና ኖርዌይ በጋዛ አፋጣኝ የተኩስ አቁም ስምምነት እና ያልተገደበ ሰብአዊ እርዳታ እንዲደረግ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፥ ሁለቱ ሀገራት ለዘላቂ ሰላም መሰረት እንዲሆን የሁለት መንግስታት መፍትሄን እንደሚደግፉ ገልጸዋል።
በዮርዳኖስ ዋና ከተማ አማን ከተደረጉት ንግግሮች በኋላ የዮርዳኖስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንደተናገሩት ኖርዌይ ለፍልስጤም የሰጠችው እውቅና ለዸም አቀፍ ህግ እና ፍትህ ያላትን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል።