ሃማስ የመጨረሻውን አሜሪካዊ ታጋች ሊለቅ እንደሆነ ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ሃማስ በጋዛ ታግቶ ያለውን የመጨረሻውን በሕይወት ያለ የአሜሪካ ዜግነት ያለውን እስራኤላዊ ኤዳን አሌክሳንደርን እንደሚለቅ ባወጣው መግለጫ ያስታወቀ ሲሆን፥ የሃማስ የተኩስ አቁም ድርድር ቡድን መሪ እንደተናገሩት ሃማስ አሜሪካዊውን ታጋች የሚለቀው በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ የሚደረገው ጥረት አካል መሆኑን ገልጸው፥ የሃማስ ታጣቂ ቡድን ከዩናይትድ ስቴትስ አስተዳደር ጋር ‘ባለፉት ጥቂት ቀናት ውስጥ’ ግንኙነት ሲያደርግ እንደነበር እና በዚህም “ከፍተኛ አዎንታዊነትን ውጤቶችን አሳይቷል” ሲሉ አስታውቀዋል።
ሃማስ በጋዛ የሚገኘውን የአሜሪካ ዜግነት ያለውን ታጋች እንደሚለቅ የገለጸው፣ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ እና እርዳታ ወደ ጋዛ ዳግም እንዲገባ ለማድረግ ከአሜሪካ ጋር ቀጥተኛ ውይይት እያደረገ እንደሆነ በተነገረበት ወቅት ነው ተብሏል።
583 ቀናት በእገታ
ሃማስ በ2015 ዓ.ም. ጥቅምት ወር ላይ እስራኤል ላይ በፈጸመው ጥቃት 251 ሰዎች ሲታገቱ፣ 59ኙ አሁንም በሃማስ ቁጥጥር ስር ይገኛሉ ተብሎ ሲታመን፣ ከእነዚህ መካከል ደግሞ 24 ሰዎች በሕይወት መኖራቸው ይገመታል።
ከታጋቾቹ መካከል አምስቱ አሜሪካዊ ዜግነት ያላቸው መሆናቸው የተገለፀ ሲሆን፣ የ 21 ዓመቱ አሜሪካዊ አሌክሳንደር በዚህ ሰዓት በጋዛ ከሚገኙት 59 ታጋቾች ውስጥ አንዱ ሲሆን፥ ከ583 ቀናት በኋላ እንዲለቀቅ መወሰኑ እየተነገረ ይገኛል።
ሃማስ በጋዛ የሚገኘውን የአሜሪካ ዜግነት ያለውን ታጋች እንደሚለቅ ሲገልጽ፣ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ እና እስራኤል ወደ ጋዛ ምንም ዓይነት የሰብዓዊ እርዳታ እንዳይገባ ካገደች 70 ቀናት ማለፉን ተከትሎ እርዳታ ወደ ጋዛ ዳግም እንዲገባ ለማድረግ ከአሜሪካ ጋር ቀጥተኛ ውይይት እያደረገ መሆኑን በመግለጽ፥ ይህ ውሳኔ የተኩስ አቁም ስምምነቱ አንዱ እርምጃ መሆኑን አስታውቋል።
ፍልስጤማዊው ፖለቲከኛ ካሊል አል-ሃያ ይህ እርምጃ “በአስቸኳይ የተጠናከረ ድርድር ለመጀመር ያለውን ዝግጁነት እና ጦርነቱን እንዲቆም የመጨረሻ ስምምነት ላይ ለመድረስ ከፍተኛ ጥረት ለማድረግ ያለውን ዝግጁነት” ማረጋገጫ ነው በማለት ገልጸዋል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት በበኩሉ ምንም አይነት የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ቃል እንዳልተገባ በመጥቀስ፥ ነገር ግን የመጨረሻውን አሜሪካዊ ታጋች ለማስለቀቅ አስተማማኝ መንገድ ይሄ ብቻ እንደሆነ ገልጿል።
ድርድሩን በቅርበት የሚከታተሉ አንድ ከፍተኛ የሃማስ ባለስልጣን የፍልስጤም ታጣቂ ቡድን በኳታር ከአንድ የአሜሪካ አስተዳደር ባለስልጣን ጋር ቀጥተኛ ድርድር እያደረገ መሆኑን እና የአሌክሳንደር መለቀቅ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ማክሰኞ ግንቦት 5 ቀን 2017 ዓ.ም. ወደ መካከለኛው ምስራቅ ከሚያደርጉት ጉብኝት በፊት መደረጉ ጥሩ የሚባል ምልክት እንደሆነ ዘግቧል።
የጋዛ ሰብአዊ ቀውስ
ይህ በእንዲህ እንዳለ በጋዛ የረሃብ አደጋ የማይቀር መሆኑ ግልጽ እየሆነ መምጣቱ፣ ገዳይ ወረርሽኞች የመስፋፋት አቅም እየጨመረ መሄዱ እና ግብርና ሙሉ በሙሉ የመውደም አፋፍ ላይ በመድረሱ ምክንያት በአከባቢው ያለው ሁኔታ እጅግ አስከፊ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፥ የተባበሩት መንግስታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት ሰብአዊ እርዳታ ወደ ጋዛ ሰርጥ እንዲገባ እነዚህን እገዳዎች ማንሳት አስፈላጊ መሆኑን አበክሮ ገልጿል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደዘገበው ከዓመቱ መጀመሪያ ጀምሮ በጋዛ 10,000 የሚጠጉ ህጻናት ላይ ከፍተኛ የሆነ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት መከሰቱን እና በአከባቢው በካፍተኛ ሁኔታ የምግብ ዋጋ በ1,400 በመቶ መጨመሩን ይፋ አድርጓል።