ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለቡርኪና ፋሶ ፕሬዝደንት የተላከ በማስመሰል የተላለፈው መልዕክት የሃሰት መሆኑ ተረጋገጠ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
“ለክቡር ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ትራኦሬ፣ የሉዓላዊ ሀገር ቡርኪናፋሶ ፕሬዝዳንት፣ የአፍሪካ ምድር ልጅ፣ የህዝቡ ጠባቂ፤ ጸጋ እና ሰላም በጥበብ፣ በድፍረት እና እውነት በኩል ያብዛልህ” ብሎ የሚጀምረው እና በእንግሊዘኛ የተጻፈ ነው ተብሎ የሚታሰበው መልዕክት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ እንደፃፉት ተደርጎ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ በኩል እንደተሰራ ተገልጿል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ሰኞ ግንቦት 4 ቀን 2017 ዓ.ም. ከተለያዩ ሃገራት ከመጡ ጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ ወቅት የተወሰደ ትክክለኛ ቀረጻን እንደ ግብዓት በመጠቀም በሰው ሰራሽ አስተውሎት የተሰራው ይህ የ36 ደቂቃ ቪዲዮ “የፓን አፍሪካን ህልሞች” የሚል መለያ ያለው ዩቲዩብ ላይ እንደተለቀቀ ተገልጿል።
ከዚህም በተጨማሪ ይህ አዲሱ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት እንደተናገሩት ተደርጎ አስመስሎ የተሰራው ተንቀሳቃሽ ምስል “ሞርፊንግ” ተብሎ በሚታወቀው የሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘዴ የተሰራ ሲሆን፥ ይህም ዘዴ ምስሉን በመለወጥ የከንፈር እንቅስቃሴን በሰው ሰራሽ አስተውሎት ከተፈጠሩ ቃላቶች ጋር በማዛመድ የሚሰራ እንደሆነ ባለሙያዎች ይገልፃሉ።
ሃሰተኛ ቪዲዮው “ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ የእውነት፣ የፍትህ እና የእርቅ መልእክት በሚል ለካፒቴን ኢብራሂም ትራኦሬ ምላሽ ሰጡ” የሚል አርዕስት እንደተሰጠውም ለማወቅ ተችሏል።
ተንቀሳቃሽ ምስሉን የሚመለከቱ ሰዎች አዲሱ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የቡርኪና ፋሶው ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ትራኦሬ ለፃፉት ደብዳቤ የሰጡት ምላሽ ተደርጎ እንዲያምኑ ጥረት የተደረገ ሲሆን፥ በቪዲዮው ላይ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛን ድምጽ በማስመሰል “የፃፉትን ደብዳቤ አንድ ጊዜ ሳይሆን ደጋግሜ አንብቤያለሁ፣ እናም እያንዳንዱ ቃላት ከመጨረሻው የበለጠ ጥልቅ ነው፣ ከዚህም የተነሳ በድምፅዎ ውስጥ የእርሶን ቁጣ ብቻ ሳይሆን የአህጉሪቱን ለዘመናት የዘለቁ በግፈኞች መንታ ሰይፍ የደረሰባት የረጅም ጊዜ የመከራ ቁስሎች ጩኸት ሰምቻለው” በማለት ተመልካቹን ለማሳመን ጥረት ያደርጋል።
ይህ ቪዲዮ ግንቦት 7 ቀን 2017 ዓ.ም. በቢቢሲ ዜና (https://www.bbc.com/afrique/articles/c3rpw8n0zvxo) ሽፋን ከተሰጣቸው ተከታታይ የውሸት መልዕክቶች ውስጥ አንዱ ሲሆን፥ ከዚህም በተጨማሪ “ኑ ሴ ሌግ-ሊዝ” የሚል መለያ ባለው ዩቲዩብ ቻናል ላይ በአነስተኛ ጥራት እና ደቂቃዎች ቆይታ በድጋሚ መለጠፉ ተገልጿል።
በዚህ ሃሰተኛ የቪዲዮ ምስል ላይ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ምስል መደጋገሙ የሚታወቅ ሲሆን፥ ብጹእነታቸው በዚህ በጠቅላላው 36 ደቂቃ በሚፈጀው የሃሰት መልእክት ውስጥ ተመሳሳይ ሁለት ወረቀቶችን ብቻ ይዘው እንደነበር ይታያል።
ምንም እንኳን ሁሉም የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ንግግሮች፣ መልዕክቶች እና ጽሑፎች ሙሉ በሙሉ በትክክለኛው የቫቲካን ዜና ድህረ ገጽ (vatican.va) ላይ የሚገኙ መሆኑ ቢታወቅም፥ ነገር ግን በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ለአዲሱ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የተላኩ በማስመሰል የተሰሩ ጽሑፎች ምንም ዓይነት ምንጭ ሳይጠቀስ እየተሰራጩ እንደሚገኝ ተገልፆ፥ ትክክለኛውን የብጹእነታቸውን መልዕክቶች እና ሃዋሪያዊ ክንውኖች በበርካታ ቋንቋዎች ተተርጉመው በቫቲካን ዜና ድህረ ገጽ ላይ እንዲሁም የቫቲካን ጋዜጣ በሆነው በላ ኦዘርቫቶሬ ሮማኖ ድህረ ገጽ ላይ ብቻ ማግኘት እንደሚቻል ማስታወስ ተገቢ ነው ተብሏል።
(ትክክለኛ መረጃዎችን ለማግኘት vaticannews.va እና osservatoreromano.va. ይጠቀሙ።)