ካሪታስ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በሃገሪቱ ከደረሰው አውዳሚ የጎርፍ አደጋ በኋላ ለአካባቢ ጥበቃ ቅድሚያ እንዲሰጥ ጠየቀ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ምሥራቃዊ ክፍል በተከሰተው የጎርፍ አደጋ ከ100 በላይ ሰዎች እንደሞቱ፣ 50 ሰዎች ደግሞ እስካሁን እንዳልተገኙ እና በትንሹ 28 ሰዎች አካላዊ ጉዳት እንደደረሰባቸው የተገለጸ ሲሆን፥ በአከባቢው በጣለው ከባድ ዝናብ የካሳባ ወንዝ ሞልቶ በታንጋኒካ ሀይቅ ዙሪያ ያሉትን በርካታ መንደሮችን ጠራርጎ መውሰዱ ተነግሯል።
አብዛኞቹ ተጎጂዎች ህጻናት እና አዛውንቶች መሆናቸውን የክልሉ አስተዳዳሪ ያረጋገጡ ሲሆን፥ በተከሰተው የጎርፍ አደጋ “ከፍተኛ የሆነ ቁሳዊ ጉዳት” እንደደረሰ ገልጸዋል።
ጎርፉ የተከሰተው በአከባቢው የጣለውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ ሲሆን በደቡብ ኪቩ ግዛት በሚገኘው ካሳባ መንደር ከሐሙስ እስከ አርብ ምሽት ድረስ መዝነቡ የክልሉ ባለስልጣን በርናርድ አኪሊ ተናግረዋል።
ከአደጋው በኋላ ምን ተከሰተ
በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የቡቴምቦ-ቤኒ ካሪታስ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር የሆኑት ኤሊ ቡለጌቲ ‘ክሩክስ’ ከተባለ የካቶሊክ ሚዲያ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የጎርፍ አደጋው በህብረተሰቡ ላይ ያደረሰውን አስከፊ ተጽእኖ በአጽንዖት የገለጹ ሲሆን፥ በአደጋው በርካታ መሰረተ ልማቶች ከመውደማቸው በተጨማሪ የጎርፍ ውሃው ከተማዋን ማጥለቅለቁን በመጥቀስ፥ “በዚህም ምክንያት በርካታ የንፅህና መሠረተ ልማቶች በመውደማቸው ከፍተኛ ሰብአዊ አደጋ ደርሷል” በማለት አብራርተዋል።
ዳይሬክተሩ አክለውም ወደ 2,000 የሚጠጉ አባወራዎች “መጠሊያ ማጣታቸውን” እና “የሚያርፉበት ቤት እንደሌላቸው” ተናግረዋል።
በደቡብ ኪቩ አውራጃ አካባቢዎች በተከሰተው የጎርፍ መጥለቅለቅ የስልክ መስመሮች በመውደማቸው ምክንያት አገልግሎቱ ስለተቋረጠ እና ይህም የነፍስ አድን ሥራዎችን በማስተጓጎሉ ከፍተኛ የሰብዓዊ ጉዳት መድረሱንም ጭምር ባለስልጣኑ አስረድተዋል።
ፖለቲካ፣ ግጭት እና ከባቢያዊ ችግር
አሁን የተከሰተው የጎርፍ አደጋ በዚህች አፍሪካዊት ሀገር ላይ የደረሰ የመጀመሪያው የተፈጥሮ አደጋ እንዳልሆነ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ የገለጸ ሲሆን፥ ተቋሙ እንዳስታወቀው ባለፈው ዓመት በምዕራብ እና መካከለኛው አፍሪካ አካባቢዎች በተመሳሳይ ሁኔታ በደረሰው የጎርፍ አደጋ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ላይ ጉዳት ማድረሱን በመግለጽ፥ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ብቻ 1.2 ሚሊዮን ሰዎች በከባድ የጎርፍ አደጋ መጎዳታቸውን አስታውሷል።
የካሪታስ ቡተምቦ-ቤኒ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር እንዳሉት ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የተፈጥሮ አደጋዎችን ተፅእኖ በመቅረፍ ረገድ ያለው የችግሩ አካል ነባር ህጎችን አለመተግበሩ ነው ብለዋል።
ለወደፊቱም እንደ ጎርፍ ያሉ አደጋዎችን ለመከላከል የአገሪቱ ባለስልጣናት “ተጠያቂነት በተሞላበት መንገድ የከተማ ፕላን ላይ በንቃት እንዲሳተፉ” ተቋማቸው እንደሚያበረታታ የገለጹት ዳይሬክተሩ፥ “ለዘላቂ ልማት ቅድሚያ መስጠት እንደሚገባ እና ተገቢውን የዞን ክፍፍል ህጎችን ማስከበር ወደፊት ስጋቶችን ለመቀነስ እንደሚረዳ” አፅንዖት ሰጥተዋል።
በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በተለይም በምስራቅ የሀገሪቱ ታላላቅ ሀይቆች ዳርቻ አካባቢ ያሉ ኮረብታዎች በደን ጭፍጨፋ የተዳከሙ በመሆናቸው እንደዚህ አይነት የተፈጥሮ አደጋዎች በብዛት ይከሰታሉ። በ 2015 ዓ.ም. በደቡብ ኪቩ አውራጃ በኪቩ ሐይቅ ዳርቻ በሚገኙ በርካታ ማህበረሰቦች ላይ የጎርፍ አደጋ ባስከተለው ውድመት 400 ሰዎችን የገደለ ሲሆን በተመሳሳይ ባለፈው ወር በዋና ከተማዋ ኪንሻሳ በደረሰ የጎርፍ አደጋ 33 ሰዎች ህይወት ማለፉ ይታወሳል።