MAP

በዩክሬን እየተካሄደ ያለው ጦርነት በዩክሬን እየተካሄደ ያለው ጦርነት   (AFP or licensors)

በዩክሬን የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ ተወካይ ‘እንደ ቤተ ክርስቲያንም ሆነ እንደ ሰብዓዊ ፍጡር መጸለይ እንቀጥላለን' አሉ

በዩክሬን የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ ተወካይ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ቪስቫልዳስ ኩልቦካስ እንደተናገሩት በቅርቡ በሩሲያ እና በዩክሬን የተደረገው የእስረኞች ልውውጥ ምንም እንኳን ፖለቲካዊ ጉዳዮች እስካሁን እልባት ባያገኙም፥ ውይይት ማድረግ ቢያንስ ከሰብአዊነት አንፃር ጠቃሚ መሆኑን ያሳያል ብለዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ሊቀ ጳጳስ ቪስቫልዳስ ኩልቦካስ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ረቡዕ ዕለት ባቀረቡት ሳምንታዊ ጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ላይ ያስተላለፉትን የሰላም ጥሪ አስተጋብተው፥ እስረኞችን መለዋወጥ የሚያመላክተን ነገር ቢኖር፥ ምንም እንኳን የፖለቲካ ጉዳዮች እልባት ባያገኙም፥ ቢያንስ ውይይት ማድረግ ከሰብአዊነት አንፃር ጠቃሚ መሆኑን ነው” ብለዋል።

በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በተደረገው ሳምንታዊ ጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ማጠቃለያ ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ምዕመናን በሁሉ ለዩክሬን ሰላም እንዲጸልዩ ተማጽነው፥ ከዚህም ባሻገር ጦርነቱ እንዲያበቃ ሁለቱ ሃገራት ውይይት እንዲጀምሩ ዸም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

ቅዱስ አባታችን አክለውም ብዙውን ጊዜ በሲቪሎች እና በመሠረተ ልማት አውታሮች ላይ በሚደርሱ ከባድ ጥቃቶች የተነሳ ከፍተኛ ጉዳት የሚደርስባቸውን የዩክሬን ህዝብ ማሰብ እንዳለብን አሳስበው፥ ሃዋሪያዊ ተወካዩ በቃለ ምልልሳቸው ወቅት ጭካኔ የተሞላባቸው ጥቃቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን አረጋግጠዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በሳምንታዊው ጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ወቅት በዩክሬን እየተካሄደ ስላለው ጦርነት ያቀረቡትን የሰላም ጥሪ በቃለ ምልልሳቸው ወቅት ያነሱት ሊቀ ጳጳሱ፥ በዩክሬን ከተሞች እና በመሠረተ ልማት ላይ ስለደረሰው ጥቃት፣ በተለይም ምዕመኑ ለሰላም እንዲጸልዩ ያቀረቡት ግብዣ በጣም አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፥ ምእመኑ በእሳቸው ጥሪ መሰረት ጸሎት እንዲያደርግ አሳስበዋል።

ነባራዊው ሁኔታው እንደሚያሳየው ጦርነቱ ከተጀመረ አራት ዓመት እንደሞላው ያስታወሱት ሊቀ ጳጳሱ፥ በከተሞች እና በሲቪል መሰረተ ልማቶች ላይ የሚደርሰው ጥቃት እየቀነሰ ሳይሆን እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመዋል።

በቅርቡ በዋና ከተማዋ ኪየቭ በየቀኑ እና በየምሽቱ ያልተቋረጡ የቦምብ ጥቃቶች መድረሳቸውን አስታውሰው፥ በዸም ላይ ዬትኛውም ሰራዊት ከእንደዚህ አይነት ከባድ ጥቃቶች እራሱን መከላከል እንደማይችል ጠቁመዋል።

ማንም ሰው የራሱን ሕይወት፣ ከተሞችን ወይም መሠረተ ልማቶችን ሙሉ በሙሉ መጠበቅ በማይችልበት እውነታ ውስጥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ባቀረቡት ጥሪ መሰረት ለሰላም መጸለይ እንደሚገባ አሳስበዋል።

አሁን ያለንበት የግንቦት ወር ለመቁጠሪያ ጸሎት የተሰጠ ወር መሆኑን ያስታወሱት ሊቀ ጳጳስ ቪስቫልዳስ፥ እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በፋጢማ የተናገረችውን ቃል ሁል ጊዜ እንደሚያስታዉሱ ገልጸው፥ እናታችን ደጋግማ ‘ጸልዩ፣ ጸልዩ፣ ጸልዩ፥ በጸሎት ጥፋትን እና ጦርነትን ታሸንፋላችሁ፥ እንዲሁም የልብን መለወጥ ታገኛላችሁ' ማለትዋን አስታውሰዋል።

ይህም በመሆኑ እንደ ቤተክርስቲያን እና እንደ ሰብአዊ ፍጡር ያለን ብቸኛው መሳሪያ ጸሎት መሆኑን ጠቁመው፥ ለዚህ ጥሪ ቅዱስ አባታችንን በግል በጣም እንደሚያመሰግኑ ገልጸዋል።

ቅድስት መንበር የእስረኞች ጉዳይ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያሳስባት እና በቅርቡ ደግሞ ጦርነቱ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በዩክሬን እና በሩሲያ መካከል ትልቁ የእስረኞች ልውውጥ መደረጉን መልካም ተግባር መሆኑን የገለጹት ሊቀ ጳጳሱ፥ እንደ ሃዋሪያዊ ተልዕኮ የጠፉ ወይም የታሰሩ፣ የሚወዷቸው ዘመዶቻቸውን ለማግኘት እርዳታ የሚፈልጉ ቤተሰቦችን ወይም ማህበራትን ብዙ ጊዜ እንደሚያነጋገሩ አንስተው፥ በሁለቱም ወገን 1,000 እስረኞች የተፈቱ በመሆኑ የተደረገው ልውውጥ በጣም ጠቃሚ እንደሆነ፥ ሰዎቹ ወደ ቤታቸው በሰላም መመለስ ስለቻሉም በእርግጥ ታላቅ ደስታ ነው ብለዋል።

ግንቦት 8 ቀን 2017 ዓ.ም. በኢስታንቡል በተካሄደው ድርድር የተገኘው ውጤት ምናልባትም ብቸኛው ውጤት እንደሆነ ቢታወቅም፥ ምንም እንኳን ፖለቲካዊ ጉዳዮች እስካሁን መፍትሄ ባያገኙም ውይይቱ ቢያንስ በሰብአዊነት ደረጃ በጣም ጥሩ ውጤት እንደሆነ ጠቁመዋል።

ሊቀ ጳጳስ ቪስቫልዳስ በመጨረሻም ትልቁ ጉዳይ በጣም አስቸጋሪ ወቅት ላይ እንደሆኑ እና ሙሉ ኃይላቸውን በየትኛው አቅጣጫ ማተኮር እንዳለባቸው በግልጽ ለማየት አስቸጋሪ እንደሆነ ገልጸው፥ "ጸሎታችንንም ሆነ ጥረታችንን ማጠናከር አለብን" ካሉ በኋላ፥ ሁለቱ ሃገራት ከተለዋወጡት እስረኞች ውስጥ ጥቂቶቹ ሲቪሎች እንደነበሩ፥ ይሄንንም በማየታቸው ደስተኛ እንደሆኑ፥ ይሁን እንጂ አሁንም ድረስ በዩክሬን ውስጥ የቀሩት ሲቪሎች በጣም ውስን ቢሆኑም፥ ነገር ግን በሌላኛው ወገን (ሩሲያ) እስር ላይ የሚገኙ ሲቪሎች በርካታ መሆኑን ጠቁመዋል።
 

30 May 2025, 15:16