በሱዳን በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ህፃናት ለረሃብ መጋለጣቸው ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
በሱዳን ሰሜን ዳርፉር ክልል በተቀሰቀሰው ግጭት ምክንያት 825,000 ህጻናት በአል-ፋሸር እና ዛምዛም ካምፖች ውስጥ ያለ ምንም መሰረታዊ ፍላጎቶች አቅርቦት ለረሃብ ተጋልጠው እንዳሉ የተገለጸ ሲሆን፥ በያዝነው ዓመት መጀመሪያ ወራቶች ጀምሮ በልጆች ላይ የሚደርሱ ከባድ የመብት ጥሰቶች ተባብሰው መቀጠላቸውን እና በአል-ፋሸር ብቻ ከ70 በላይ እንደተገደሉ እና በርካቶች ደግሞ እንደቆሰሉ ከስፍራው የወጡ መረጃዎች ያሳያሉ።
ከዚህም በተጨማሪ በዛምዛም ካምፕ ውስጥ በተፈፀመው የምድር እና የአየር ጥቃት ምክንያት ካምፑ ውስጥ ካሉ ህፃናት መካከል 16 በመቶው ጉዳት እንደደረሰባቸው ቢነገርም፥ ትክክለኛ ጉዳቱ ከዚህ ከፍ ያለ ሊሆን እንደሚችል ተነግሯል።
በሱዳን የዩኒሴፍ ተወካይ የሆኑት ሼልደን ዬት ጉዳዩን አስመልክተው እንደተናገሩት “በአል-ፋሸር እና ዛምዛም ካምፕ ያሉ ህጻናት ከአዕምሮ በላይ የሆነ ጥፋት እየደረሰባቸው ይገኛል፥ በሚደረገው ጥቃት፣ በረሃብ ወይም አስፈላጊ አገልግሎቶች በመቆማቸው ምክንያት ሞት የዕለት ተዕለት እውነታ ሆኗል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ዩኒሴፍ ባሳለፍነው ሃሙስ በሰጠው መግለጫ ከባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር ጀምሮ ከሰሜን ዳርፉር 300,000 ህጻናትን ጨምሮ 600,000 ሰዎች መፈናቀላቸውን ያስታወቀ ሲሆን፥ ባለፉት ስድስት ሳምንታት ውስጥ ብቻ ተጨማሪ 60,000 ሰዎች መሰደዳቸውን ይፋ አድርጓል። ይህ በእንዲህ እንዳለ 1.65 ሚሊዮን ሰዎች ሰብዓዊ እርዳታ ማግኘት ባለመቻላቸው በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንዳሉ አስጠንቅቋል።
ከታዊላ ግዛት እስከ ዘምዘም የሚወስደው መንገድ በአንድ ወቅት ወሳኝ የአቅርቦት መስመር የነበረ ሲሆን፥ አሁን ላይ ግን ታጣቂ ቡድኖች ሰብዓዊ ዕርዳታው የሚመላለስበትን መንገድ በመታቸው ማህበረሰቡን ያለ ምግብ፣ ውሃ እና የህክምና አቅርቦቶች እያስቀሩ በመሆኑ በአከባቢው የሚገኙ ሰዎች ከባድ ችግር ውስጥ መግባታቸው ተገልጿል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የምግብ ዋጋ በሦስት ወራት ውስጥ ብቻ በእጥፍ በመጨመሩ ህዝቡ በከፍተኛ ሁኔታ ተስፋ መቁረጥ ውስጥ እንደገባ ይነገራል።
ዩኒሴፍ እና ሌሎች ግብረሰናይ ድርጅቶች ዕርዳታ ለማቅረብ ጥረት እያደረጉ ቢሆንም፥ ነገር ግን በአከባቢው ያለው የደህንነት ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን እየገለጹ የሚገኝ ሲሆን፥ በሰሜን ዳርፉር ብቻ 457,000 ከፍተኛ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ያለባቸው ህጻናት የሚገኙ ሲሆን፥ ከነዚህም መካከል 146,000 ህፃናት እጅግ የከፋ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት (SAM) ውስጥ እንደሚገኙ እና የገምቢ ምግቦች ክምችት መሟጠጡን ጠቁመዋል።
ከዚህም በተጨማሪ የህክምና አገልግሎት ማዕከሎች እየፈራረሱ እንደሆነ እና በዩኒሴፍ በሚደገፉ የጤና ባለሙያዎች እየደረሰ ባለው ጥቃት ምክንያት አከባቢው ለቀው ለመውጣት መገደዳቸውን፣ በዚህም ምክንያት የታመሙ እና የቆሰሉ ህጻናት እንክብካቤ እያገኙ እንዳልሆነ የተገለጸ ሲሆን፥ የጤና፣ የተመጣጠነ ምግብ እና የንጹህ ውሃ አቅርቦቶች በመታገዳቸው እጅግ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች መድረስ አልተቻለም ተብሏል።
ይሄን ተከትሎ ዩኒሴፍ ሁሉም ወገኖች ደህንነቱ የተጠበቀ የሰብአዊ አገልግሎት እንዲሰጡ ያሳሰበ ሲሆን፥ ይሄንን አስመልክተው የዩኒሴፍ ተወካዩ ሼልደን ዬት እንደተናገሩት “ከዚህ የምድር ሲኦል ዓይናችንን ለአፍታ ማንሳት ዬለብንም፥ የዸም ማህበረሰብ በአስቸኳይ እርምጃ መውሰድ አለበት” በማለት አስጠንቅቀዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ የሱዳንን ጦርነት “በዸም ላይ ካሉት እጅግ አስከፊ ሰብዓዊ ቀውስ” በማለት በመግለጽ፥ ሁሉም ወገኖች ጦርነቱን እንዲያቆሙ ደጋግመው የሰላም ጥሪ ማቅረባቸው ይታወቃል።
ዩኒሴፍ የሱዳን ቀውስ እየተባባሰ በመሄዱ አስቸኳይ ጣልቃ ገብነት እንደሚያስፈልገው እና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ህጻናት እጣ ፈንታ አስከፊ ሁኔታ ላይ እንደሚወድቅ አስጠንቅቋል።