በሄይቲ ለሚደረገው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ህዝቡ ተስፋ እንዳደረገ ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
አዲሱ የሽግግር ፕሬዚዳንታዊ ምክር ቤት መሪ ፍሪትዝ አልፎንሴ ዣን በዚህ ሳምንት በዋና ከተማዋ ፖርት ኦው ፕሪንስ ላይ ሌላ ጥቃት የከፈቱት የጎዳና ላይ ወሮበሎች ችግር ትልቅ ደረጃ ላይ መድረሱን በመግለጽ፥ ይህ ሕገ-ወጥ የወንጀለኞች ጥምረት ሰማንያ አምስት በመቶውን የሃገሪቷን መዲና እንደተቆጣጠረ እና አሁንም በመስፋፋት ላይ እንደሚገኝ ጠቁመው፥ “ሀገራችን በጦርነት ላይ ነች፥ ይሄንን አሸንፎ ለማለፍ አንድ መሆን አለብን” ሲሉ አጥብቀው አሳስበዋል።
በምዕራቡ የዓለማችን ንፍቀ ክበብ የምትገኘው እና የደቀቀ የምጣሄ ሃብት ባላት በጣም ድሃዋ ሀገር ሄይቲ የተቀሰቀሰው አመጽ ተባብሶ ቀጥሎ እና የአገሪቱ ዜጎች ለምግብ እጥረት ተጋልጠው በሚገኙበት በአሁኑ ወቅት የትራምፕ አስተዳደር የአሜሪካ መንግስት በዩኤስ ኤአይዲ (USAID) በኩል ያደርግ የነበረውን ድጋፍ በማቆሙ ከፍተኛ ችግር ውስጥ መግባቷ የተነገረ ቢሆንም፥ ይህ አዲሱ የትራንፕ የኢኮኖሚ ተሃድሶ አካል ከአጠቃላይ አንድ ሺህ ያህል የሰው ሃይል ውስጥ ስምንት መቶ የሚሆነውን በኬንያ የሚመራው መድብለ ብሄራዊ የድጋፍ ተልዕኮ የሚሰጠውን ድጋፍ እንደማያካትት የተነገረ ሲሆን፥ የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ሰሞኑን ከዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ጋር ባደረጉት የስልክ ውይይት ሁለቱም ሃገራት የነበራቸውን ትብብር ለማጠናከር ያላቸውን ቁርጠኝነት በድጋሚ አረጋግጠውላቸዋል።
ወደ ሃገሪቷ ያቀናው የኬኒያ የጸጥታ አስከባሪው ኃይል እ.አ.አ. በ 2023 ዓ.ም. በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ሥልጣን ተሰጥቶት የነበረ ሲሆን፥ ምንም እንኳን በቁጥር አነስተኛ ቢሆኑም በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያለውን የሄይቲ ሕግና ሥርዓት በማጠናከር ረገድ ከፍተኛ ለውጥ ያመጣሉ ተብሎ ተስፋ ተጥሎባቸዋል ተብሏል።
ሰኔ 30 ቀን 2013 ዓ.ም. የቀድሞው የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ጆቨኔል ሞይስ በኮሎምቢያ ቅጥረኞች መገደላቸውን ተከትሎ ቀድሞውንም አስከፊ የነበረው የሃገሪቷ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ሲሆን፥ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለው፣ ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች ደግሞ ቤት አልባ በመሆናቸው በሄይቲ የዴሞክራሲ ህልውና በቀጭን ክር ላይ የተንጠለጠለ ነው ተብሏል።
ባለፉት ዓመታት የተከሰቱት አለመረጋጋቶች፣ አምባገነናዊ ስርዓት እና የተፈጥሮ አደጋዎች ሄይቲ ሰላም እና አለመረጋጋት እንዲርቃት የሚያደርጉ ምክንያቶች ሆነው ቆይተዋል።
እ.አ.አ. 2010 ላይ በሄይቲ አጋጥሞ የነበረው የመሬት መንቀጥቀጥ ከ200ሺህ በላይ ሰዎችን ከመግደሉ በላይ የአገሪቱን መሠረተ ልማቶች በከፍተኛ ደረጃ እንዳወደመ ይታወቃል።