MAP

የስፔን ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ፣ የፊንላንድ ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ስቱብ እና የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ የካቲት 23 ቀን 2017 ዓ.ም. በብሪታኒያ ዋና ከተማ ለንደን፣ ላንካስተር ሃውስ ውስጥ የዩክሬን ወቅታዊ ሁኔታን አስመልክቶ በተካሄደው ስብሰባ ላይ የስፔን ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ፣ የፊንላንድ ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ስቱብ እና የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ የካቲት 23 ቀን 2017 ዓ.ም. በብሪታኒያ ዋና ከተማ ለንደን፣ ላንካስተር ሃውስ ውስጥ የዩክሬን ወቅታዊ ሁኔታን አስመልክቶ በተካሄደው ስብሰባ ላይ   (ANSA)

የአውሮፓ መሪዎች በለንደን ካደረጉት ስብሰባ በኋላ ለዩክሬን የሰላም እቅድ ቃል መግባታቸው ተነገረ

የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኬይር ስታርመር የካቲት 23 ቀን 2017 ዓ.ም. እሁድ ዕለት የዩክሬኑን ፕሬዚደንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪን ጨምሮ በአብዛኛው ከአውሮፓ የሆኑ 18 መሪዎች የተሳተፉበት ጉባኤ ተከትሎ ዩክሬን ለአሜሪካ የምታቀርበውን የሰላም እቅድ በጋራ ለማውጣት የአውሮፓ መሪዎች ተስማምተዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በለንደን በተካሄደው የመሪዎች ጉባኤ ላይ የአውሮፓ መሪዎች አህጉሪቱ ራሷን መጠበቅ እንደምትችል ለአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለማሳየት የመከላከያ አቅማቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው ተስማምተዋል።

የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስቴር ስታርመር የዩክሬኑን ፕሬዚደንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪን ጨምሮ በአብዛኛው ከአውሮፓ የሆኑ 18 መሪዎች በተሳተፉበት ጉባኤ ላይ “አውሮፓ በታሪኳ መስቀለኛ መንገድ ላይ ነች” ብለዋል።

የአውሮፓ አገራት በጥምረቱ ሰላምን ለማምጣት ጥረታቸውን እንደሚቀጥሉ የገለጹት ስታርመር፥ ዩክሬንን ለመደገፍ በሚደረገው ጥረት አሜሪካ እንድትቀላቀል እንደሚፈልጉም የገለጹ ሲሆን፥ ብሪታንያ፣ ፈረንሳይ፣ ዩክሬን እና አንዳንድ ሌሎች ሀገራት በጋራ በመሆን “የፍቃደኞች ጥምረት” እንደሚመሰርቱ እና በዩክሬን እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ለማስቆም ባለ 4-ነጥብ እቅድ ይነድፋሉ ብለዋል።

ስታርመር እንዳሉት የአውሮፓ ሃገራት ለዩክሬን በሚያደርጉት ድጋፍ ላይ ዩናይትድ ስቴትስን ለማሳተፍ እና የሰላም እቅዱን በጋራ ለመስራት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።

ጉባዔው ከመካሄዱ ቀደም ብሎ የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ለፈረንሳይ ጋዜጣ እንደተናገሩት የዩክሬን የሰላም እቅድ የአየር እና የባህር ላይ ጥቃትን የሚመለከት የአንድ ወር የተኩስ አቁምን እንደሚያካትት አስታውሰው፥ ነገር ግን የምድር ላይ ውጊያን እንደማያጠቃልል ገልጸው፥ ከፍተኛ የሰላም ስምምነት ከተደረሰ የአውሮፓ ወታደሮች እንደሚሰማሩ ማክሮን ተናግረዋል።

የአውሮፓ መሪዎች ባለፈው አርብ የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ከዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና ከምክትላቸው ጄዲ ቫንስ ጋር በዋይት ሀውስ በነበራቸው የውይይት ወቅት ከተፈጠረው ግጭት በኋላ ኪየቭ ከማንኛውም የሰላም ድርድር እንዳትገለል ለማድረግ እየጣሩ እንደሆነ የተነገረ ሲሆን፥ በዚህ ግጭት ሳቢያ ትራምፕ ለዩክሬን የሚያደርጉትን ድጋፍ አቁመው ሩሲያን ብቻ ያሳተፈ የሰላም እቅድ ሊያወጡ ይችላሉ የሚል ስጋትን ፈጥሯል።

የዩክሬኑ ፕረዚዳንት ዘለንስኪ ከጉባዔው በኋላ በብሪታንያውን ንጉስ ቻርልስ በተዘጋጀው ሌላ የድጋፍ ዝግጅት ላይ ለመገኘት በምስራቅ እንግሊዝ በሚገኘው የንጉሱ መኖሪያ ቤት እንዳቀኑም ጭምር ተገልጿል።

ከጉባኤው በኋላ በተደረገው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ዜለንስኪ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ዩክሬን በዚህ ደረጃ ላይ ሩሲያ የወሰደችውን ግዛት የሰላም ስምምነቱ አካል አድርጎ ለመወያየት ፈቃደኛ አለመሆኗን፥ ነገር ግን አሁንም ከአሜሪካ ጋር የማዕድን ስምምነት ለመፈራረም ፈቃደኛ እንደሆኑ የገለጹ ሲሆን፥ ዜለንስኪ ወደ ሃገራቸው ሲመለሱ ዩናይትድ ስቴትስ ለዩክሬን ላደረገችው ድጋፍ ምስጋናቸውን በድጋሚ ገልጸዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሩሲያ በዩክሬን የምታደርገው ወታደራዊ ዘመቻ ሁሉም ኢላማዎቿ ከግብ እስኪደርሱ ድረስ እንደሚቀጥል ያስታወቀች ሲሆን፥ ክሬምሊን ሰኞ ዕለት ባወጣው መግለጫ በዜለንስኪ እና በትራምፕ መካከል ስለተፈጠረው ግጭት በሰጠው አስተያየት ዜለንስኪ በአጠቃላይ ዲፕሎማሲያዊ ብቃት እንደሌላቸው በመውቀስ፥ ‘የምዕራቡን አንድነት ለመከፋፈል ጥረት እያደረጉ ነው’ በማለት ከሷቸዋል።
 

04 Mar 2025, 14:13