MAP

ሃምሌ 14 ቀን 2017 ዓ.ም በኩባ የተካሄደውን የተቃውሞ ሰልፍን ተከትሎ የታሰሩ አንዳንድ እስረኞች ሲለቀቁ የሚያሳይ ፎቶ ሃምሌ 14 ቀን 2017 ዓ.ም በኩባ የተካሄደውን የተቃውሞ ሰልፍን ተከትሎ የታሰሩ አንዳንድ እስረኞች ሲለቀቁ የሚያሳይ ፎቶ  (AFP or licensors)

በቫቲካን አደራዳሪነት ኩባ የገባችውን እስረኞችን የመልቀቅ ስምምነት ማጠናቀቋ ተነገረ

በቅድስት መንበር ሸምጋይነት እና በቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ ፕረዚዳንት ጆ ባይደን የመጨረሻ ቀናት የስራ ጊዜያት ውስጥ የተደረሰውን ስምምነት ማጠናቀቅ ተከትሎ ኩባ 553 እስረኞችን መልቀቋ ተነግሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ ፕረዚዳንት ጆ ባይደን በመጨረሻ የሥራ ዘመናቸው ባደረጉት ይፋዊ ተግባራት መካከል ጥር 6 ቀን 2017 ዓ.ም. ኩባን ከአሜሪካ የሽብርተኝነት ጥቁር መዝገብ ውስጥ ማውጣታቸው እና በቫቲካን አደራዳሪነት ከኩባ መንግስት ጋር የተደረገውን ስምምነት ተከትሎ የኩባ መንግስት 553 እስረኞችን መልቀቁ ተገልጿል።

ዩናይትድ ስቴትስ፣ የአውሮፓ ህብረት፣ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን እና የመብት ተሟጋች ድርጅቶች ከ 1959 ኙ የፊደል ካስትሮ አብዮት በኋላ ትልቁ ተቃውሞ መሆኑ የተነገረለትን እና ሃምሌ 14 ቀን 2017 ዓ.ም የተካሄደውን ፀረ-መንግስት ተቃውሞዎችን ተከትሎ በመቶዎች የሚቆጠሩ የታሰሩ ተቃዋሚዎችን እንድትፈታ የኩባ መንግስት ላይ ጫና ሲያደርጉ እንደነበር የሚታወስ ነው።

እስረኞችን ለመፍታት ከተደረሰው ስምምነት በኋላ የኩባው ፕሬዝዳንት ሚጌል ዲያዝ ካኔል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “ከቫቲካን መንግስት ጋር ካለን ቅርብ እና ጥብቅ ግንኙነት አካል እንደመሆኔ፥ ለርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በ2025 ኢዮቤልዩ መንፈስ [እስረኞችን የመፍታት ውሳኔ] ላይ መድረሳችንን አሳውቃለው” ብለዋል።

ዶናልድ ትራምፕ ቃለ መሃላ ከፈጸሙ ከስድስት ቀናት በኋላ በአዲሱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንትነት ስምምነቱ የተሻረ ቢሆንም እስረኞች አልፎ አልፎ መፈታታቸውን ቀጥለዋል።

በየካቲት ወር የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን የኩባ እስረኞችን ቀስ በቀስ መፈታት በቅዱስ ዓመት መጀመሪያ ላይ የተደረገ “የታላቅ ተስፋ ምልክት” ነው ሲሉ ገልጸው፥ በኢዮቤልዩ መንፈስ ከኩባ መንግስት ተጨማሪ “የምሕረት መግለጫዎች” እንደሚሰሙ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

ሰኞ ረፋድ ላይ በመንግስታዊው ቴሌቪዥን ንግግር ያደረጉት የኩባ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ሂደቱ በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን ተናግረዋል።

የመብት ተሟጋቾች እንደጠቆሙት ከተፈቱት እስረኞች መካከል ተቃዋሚ አክቲቪስቶች እና የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ እንደሚገኙበት በመግለጽ፥ ነገር ግን ሁለት ተቃዋሚ አርቲስቶች እና የፀረ-መንግስት ተቃውሞ መዝሙር ደራሲ ሙዚቀኛ አሁንም በእስር ላይ መሆናቸውን የጠቆሙ ሲሆን፥ ከተፈቱት መካከል አብዛኛዎቹ የፖለቲካ እስረኞች እንዳልሆኑ አንዳንድ ታዛቢዎች እየተናገሩ ይገኛሉ።

ይፋ በተደረገው አኃዝ መሠረት ሃምሌ 14 ቀን 2017 ዓ.ም. በተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ በአንዳንድ ሁኔታዎች እስከ 25 ዓመት እስራት የተፈረደባቸውን ጨምሮ ወደ 500 የሚጠጉ ተቃዋሚዎች በቁጥጥር ስር ውለው እንደተፈረደባቸው ተገልጿል።
 

12 Mar 2025, 13:50