የአረብ መሪዎች ከጋዛ ጦርነት በኋላ መደረግ ስለሚገባው ነገር ላይ ተወያዩ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ይህ ጉባኤ በግብፁ ፕሬዝዳንት አብደልፋታህ ኤል ሲሲ የተዘጋጀ ሲሆን፥ ሳውዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶችን ጨምሮ የክልሉ ሃገራት መሪዎች የተሳተፉ ሲሆን፥ የአረብ መንግስታቱ ድጋፍ ከጋዛ ጦርነት በኋላ ላለው ማንኛውም ፕሮጀክት ወሳኝ ነውም ተብሏል።
መሪዎቹ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ፍልስጤማውያንን አፈናቅለው ጋዛን ለመቆጣጠር የያዙትን እቅድ ሲያወግዙ ቆይተዋል።
በአሁኑ ምክክራቸውም ካይሮ የትራምፕን የጋዛ እቅድ የሚተካና ፍልስጤማውያንን ከርስታቸው የማያፈናቅል ነው በሚል ባቀረበችው የጋዛ መልሶ ማልማት እቅድ ዙሪያ ይወያያሉ ነው የተባለው።
በጦርነቱ ምክንያት የፈራረሱት በጋዛ ሰርጥ ውስጥ የሚገኙ ከተሞች እንደገና በሚገነቡበት ጊዜ ፍልስጤማውያን ሳይፈናቀሉ እዛው ጋዛ ውስጥ በሚገነቡ ጊዜያዊ ተንቀሳቃሽ መኖሪያ ቤቶች እና መጠለያዎች ተገንብቶላቸው ከመልሶ ልማቱ በኋላ ወደ ቋሚ ስፍራዎቻቸው የሚመለሱበት የአሰራር ዕቅድ ላይ እንደሚወያዩ የሚጠበቅ ሲሆን፥ ሃማስ ግን የተሻሻለው የፍልስጤም አስተዳደርን መቆጣጠር እስኪችል ድረስ ስልጣኑን ለፖለቲካ ነፃ አውጪዎች ጊዜያዊ አስተዳደር ይሰጣል ተብሏል።
የአረብ ሃገራት መሪዎች በካይሮ ለመሰባሰብ ያነሳሳቸው ዋናው ምክንያት የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ 2 ሚሊዮን የሚጠጉ የጋዛ ነዋሪዎችን በሌሎች ሀገራት ለማስፈር እና ዩናይትድ ስቴትስ በጦርነት የተጎዳውን ግዛት በባለቤትነት በመያዝ አከባቢውን የመካከለኛው ምስራቅ “ሪቪዬራ” አስመስሎ ለመገንባት ባለፈው ወር ያቀረቡትን ሀሳብ ተከትሎ ነው።
ተጠናክረው የቀጠሉት የእስራኤል ጥቃቶች
ይህ በእንዲህ እንዳለ የእስራኤል ጦር በዌስት ባንክ ላይ ጥቃት መፈፀሙን በቀጠለበት በአሁኑ ወቅት የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቢሮ ሃማስ እስካሁን በእገታ ላይ ከሚገኙት 59 ታጋቾች መካከል ተጨማሪ ታጋቾችን ለማስለቀቅ ዝግጁ እስከሆነ ድረስ መንግስታቸው ሁለተኛውን የጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት ለመቀጠል ዝግጁ መሆኑን ማክሰኞ ዕለት ይፋ አድርጓል።
የመንግስታቱ ድርጅት፣ የዸም ባንክ እና የአውሮፓ ህብረት ባለፈው ወር ይፋ ባደረጉት የጋራ ሪፖርት ጋዛን መልሶ ለመገንባት በጥቂቱ 53.2 ቢሊየን ዶላር ያስፈልጋል ብለዋል።
እስራኤል ለ15 ወራት በጋዛ የፈጸመችው ድብደባ የፍልስጤምን መሰረተ ልማቶች ማውደሙን ያነሳው ሪፖርቱ፥ የሰርጡን ኢኮኖሚ ክፉኛ ማንኮታኮቱንም አብራርቷል።
ጋዛ ውስጥ ከሚገኙ መኖሪያ ቤቶች እና ህንፃዎች ውስጥ 53 በመቶው መውደማቸውን በመጥቀስም የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት 30 ቢሊየን ዶላር እንደሚያስፈልግ ጠቁሞ፥ ጦርነቱ በጋዛ ያደረሰውን የኢኮኖሚ ጉዳት ለመጠገንም በጥቂቱ 19 ቢሊየን ዶላር ያስፈልጋል ብሏል።
የመንግስታቱ ድርጅት በቅርቡ ይፋ ባደረገው የጉዳት ግምገማ ሪፖርት በእስራኤል የቦምብ ጥቃት የተከመረውን ከ50 ሚሊዮን ቶን በላይ የሚመዝን ፍርስራሽ ለማጽዳት 21 ዓመታትን ሊወስድ እንደሚችል መጠቆሙ ይታወሳል፡፡ የጋዛን የፈራረሱ ህንጻዎች እና ቤቶች ዳግም ለመገንባትም እስከ 15 ዓመታት ይወስዳል ማለቱ አይዘነጋም።
ከጥር 11 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ በጋዛ የሚደረገው ጦርነት በዩናይትድ ስቴትስ ድጋፍ እንዲሁም በኳታር እና በግብፅ አሸማጋይነት በተዘጋጀው የእርቅ ስምምነት አማካይነት ለጊዜው መቆሙ የሚታወቅ ሲሆን፥ ሃማስ በነዚህ ጊዜያት 33 የእስራኤል ታጋቾችን እና አምስት የታይላንድ ዜጎችን ለቆ በምትኩ እስራኤል 2,000 ያክል የሚሆኑ ፍልስጤማውያን እስረኞችን መፍታቷ ዘገባዎች ያሳያሉ።
ነገር ግን በአሁኑ ወቅት የመጀመርያው የ42 ቀናት የተኩስ አቁም ስምምነት ጊዜው እንዳለቀ የሚታወቅ ሲሆን፥ የእስራኤል መንግስት ሃማስ አዲስ ሀሳብ እንዲቀበል ለማድረግ ወደ ጋዛ የሚገቡትን የምግብ፣ የነዳጅ፣ የመድሃኒት እና ሌሎች አቅርቦቶችን በመቷ እና ተጨማሪ እርምጃዎችን ልትወስድ እንደምትችል በማስጠንቀቋ ምክንያት የጋዛ ሰርጥ ዳግመኛ ወደ ጦርነት ሊመለስ ይችላል የሚል ስጋትን አሳድሯል።