MAP

የመን ባህር ዳርቻ ላይ ከሰጠመችው ጀልባ የተረፈ የሶማሊያ ስደተኛ - የማህደር  ፎቶ የመን ባህር ዳርቻ ላይ ከሰጠመችው ጀልባ የተረፈ የሶማሊያ ስደተኛ - የማህደር ፎቶ  (AFP or licensors)

በየመን እና በጅቡቲ የባህር ዳርቻዎች ላይ የስደተኛ ጀልባዎች ሰጥመው 186 ሰዎች ደብዛቸው መጥፋቱ ተነገረ

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ቢሮ እንደገለጸው አፍሪካውያን ስደተኞችን አሳፍረው የነበሩ አራት ጀልባዎች በየመን እና ጅቡቲ የባህር ድንበር ላይ ሰጥመው ሁለት ሰዎች መሞታቸው እና 186 ሰዎች ደግሞ ደብዛቸው መጥፋቱን ይፋ አድርጓል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኤጀንሲ ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ላይ እንደዘገበው መነሻቸው ከአፍሪካ እንደሆነ የተነገረው አራት ጀልባዎች በየመን እና ጅቡቲ የባህር ዳርቻዎች አከባቢ ተገልብጠው ቢያንስ የሁለት ሰዎች ህይወት ሲያልፍ፣ 186 ያህሉ ደግሞ እስካሁን የደረሱበት አልታወቀም ብሏል።

ዸም አቀፉ የስደተኞች ጉዳይ ድርጅት (IOM) እንደገለጸው ከሶስቱ ጀልባዎቹ መካከል ሁለቱ ባለፈው ሐሙስ አመሻሽ ላይ በየመን የባህር ክልል ውስጥ መስመጣቸውን ያሳወቀ ሲሆን፥ በጀልባዎቹ ውስጥ ከነበሩት መካከል 181 ስደተኞች እና አምስት የመናዊያን ሰራተኞች የገቡበት አልታወቀም ብሏል።

ከጀልባዎቹ ሰራተኞች መካከል ሁለቱ ከባህር ውስጥ በነፍስ አድን ሰራተኞች የወጡ ሲሆን፥ እነዚህ ከአደጋው የተረፉ ሰዎች እንደገለጹት ጀልባዎቹ ከአቅማቸው በላይ የሆነ ሰው በመጫናቸው የነበረውን አሰቃቂ ሁኔታ ገልፀዋል።

እንደ ዸም አቀፉ የስደተኞች ጉዳይ ድርጅት ዘገባ ከሆነ ከተሳፋሪዎቹ መካከል 57 ሴቶችን ጨምሮ በርካታዎቹ በዋነኛነት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ሲሆኑ፥ እነዚህም ስደተኞች አደገኛውን የባህር በር አከባቢ በመሻገር ወደ ባህረ ሰላጤው ሀገራት ለመድረስ ያለሙ እንደነበሩ ተገልጿል።

ከዚህም በተጨማሪ በዛው ሰሞን በጅቡቲ የባህር ዳርቻ ላይ ሁለት ተጨማሪ ጀልባዎች መገልበጣቸው የተነገረ ሲሆን፥ የነፍስ አድን ሰራተኞች ሁለት አስከሬን ማግኘታቸውን በመግለጽ፥ በነዚህ ጀልባዎች ውስጥ የነበሩ ሌሎች ተሳፋሪዎች በሙሉ ማትረፍ ችለዋል።

የአካባቢው ባለስልጣናት እንደጠቆሙት ለአደጋው መንስኤ የነበረው በአካባቢው የነበረ ኃይለኛ ንፋስ እንደሆነ ገልጸው፥ በዚህም ምክንያት ትንንሽ እና ከመጠን በላይ ጭነው የነበሩት እነዚህ ጀልባዎች ተረጋግተው መጓዝ እንዳልቻሉ ተናግረዋል።

ዸም አቀፉ የስደተኞች ጉዳይ ድርጅት አይ.ኦ.ኤም በጣም አስቸጋሪ ስለሆነው የኤደን ባህረ ሰላጤ እና ቀይ ባህር የስደተኞች መጓጓዣ መስመር አደገኛ ባህሪ በመግለጽ፥ እነዚህ የውሃ ክፍሎች በየዓመቱ በሺዎች ለሚቆጠሩ ስደተኞች በተለይም ከአፍሪካ ቀንድ ተነስተው በበለጸጉ የባህረ ሰላጤ ሀገራት የሥራ እድል ለሚፈልጉ ሰዎች እንደ መሸጋገሪያ መንገድ ሆነው ያገለግላሉ ብሏል።

ነገር ግን፣ ጉዞዎቹ ብዙ ጊዜ በአሰቃቂ አደጋዎች የሚያበቁት በባህር ላይ ለመጓጓዣነት በማይገቡ መርከቦች፣ ከልክ በላይ መጫን እና በመጥፎ የአየር ሁኔታዎች ምክንያት እንደሆነም ተገልጿል።

ስደተኞችም ከደህንነት ይልቅ ትርፍ በሚያስቀድሙ ህገወጥ አዘዋዋሪዎች ብዙ ጊዜ ብዝበዛ እንደሚደርስባቸው እና ብዙዎችን ለአካል ጉዳት ወይም ለሞት እንደሚዳረጉ ተመላክቷል።

ተጨማሪ የተረፉትን የማግኘት ተስፋ የደበዘዘ ቢሆንም፥ የጠፉትን ግለሰቦች ለማግኘት ፍለጋው እንደቀጠለ ተነግሯል።
 

10 Mar 2025, 13:06