MAP

በደማስቆ የተካሄደው የሶሪያ ብሔራዊ የምክክር ጉባኤ በደማስቆ የተካሄደው የሶሪያ ብሔራዊ የምክክር ጉባኤ  (ANSA)

ሴቶች እና አናሳዎች በሶሪያ ብሄራዊ የምክክር ጉባኤ ላይ መሳተፋቸው ተነገረ

ሶሪያን እየመራት የሚገኘው አዲሱ ጊዜያዊ መንግስት ከቀድሞው ፕሬዚደንት በሽር አላሳድ ውድቀት እና ወደ 14 ዓመታት የዘለቀው የእርስ በእርስ ጦርነት በኋላ ሀገሪቱን መልሶ ለመገንባት አሁን ያለንበት ወቅት “ብርቅዬ ታሪካዊ እድል” ነው በማለት ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረው ብሄራዊ የምክክር ጉባኤ ማክሰኞ ዕለት ማስጀመራቸው ተነግሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ታህሳስ ወር 2017 ዓ.ም. ላይ የአሳድ መንግስትን ያስወገደውን ጥቃት የመራው በቀድሞው እስላማዊው አማፂ ቡድን ሀያት ታህሪር አል ሻም ወይም ኤችቲኤስ ተብሎ በሚታወቀው ቡድን የሚመራው አዲሱ ጊዜያዊ መንግስት በተዘጋጀው እና በደማስቆ በተካሄደው ብሄራዊ የምክክር ጉባኤ ላይ እንዲገኙ ከተጋበዙት 600 ያህል ሶሪያዊያን መካከል ሴቶች እና አናሳ ሀይማኖቶች እንደተካተቱበት ተገልጿል።

የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት የሆኑት አህመድ አልሻራ ጉባኤውን በንግግር የከፈቱት “ሶሪያ ራሷን ነፃ እንዳወጣች ሁሉ እራሷን በራሷ መገንባት ትችላለች” በማለት ሲሆን፥ ዛሬ ሶሪያውያን የህዝብን ጥቅም ለማስከበር ልዩ እና ብርቅዬ ታሪካዊ እድል እንዳላቸው ገልጸው፥ ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ሽግግር ለማድረግም ቃል ገብተዋል።

ግዜያዊ ፕረዚዳንቱ አክለውም በአሳድ የስልጣን ዘመን የተጣሉት ማዕቀቦች መነሳት አለመነሳታቸውን የሚመዝኑ ሀገራትን ጨምሮ ሶሪያውያን እና ዸም አቀፉ ማህበረሰብ በቅርበት እየተከታተለን ይገኛል ብለዋል።

ሶሪያ ኢኮኖሚውን እንደገና ከማንሰራራት እና በጦርነት የወደሙ መሰረተ ልማቶችን ከመገንባት ጀምሮ በጦር ወንጀሎች ለተከሰሱ ሰዎች አዲስ ሕገ መንግሥት እና የፍትህ ዘዴዎች እስከ ማቋቋም ድረስ ትላልቅ ፈተናዎች ከፊቷ እንደተጋረጡባት ይነገራል።

ምንም እንኳን የበቀል እርምጃዎች እና የጅምላ ቅጣቶች ከተጠበቀው በላይ የተስፋፉ ባይሆንም፥ ብዙዎቹ የሶሪያ አናሳ ማህበረሰቦች የሆኑት ኩርዶች፣ ክርስቲያኖች፣ ድሩዝ እና የአሳድ አላዊት ቡድን አባላት የወደፊት ዕጣ ፋንታቸው እንደሚያሳስባቸው እና ሁሉን አካታች ነው ተብሎ በተነገራቸው የአዲሱ አስተዳደር ተስፋዎች እርግጠኛ እንዳልሆኑ እየተነገረ ይገኛል።

የሀያት ታህሪር አል ሻም ቡድን ምንም እንኳን አሁን ላይ ግንኙነቱን ቢያቋርጥም ከዚህ ቀደም ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት እንደነበረው የሚታወቅ ሲሆን፥ ቡድኑ ወደ ስልጣን ከመጣ ጀምሮ ተቻችሎ በሰላም አብሮ ስለ መኖርን እየሰበከ እንደሚገኝ መረጃዎች ያሳያሉ።

በደማስቆ የተካሄደውን ጉባኤ ያዘጋጁ ሰዎች እንደተናገሩት ሁሉም የሶሪያ ማህበረሰብ በጉባኤው ላይ እንዲገኙ የተጋበዙ ሲሆን፥ ሴቶች እና አናሳ ሀይማኖታዊ ማህበረሰቦች ከተሳታፊዎች መካከል ይገኙበታል ብለዋል።

ብሄራው የምክክር ጉባኤው አዲስ ህገ መንግስት ከማዘጋጀት እና አዲስ መንግስት ከመመስረቱ በፊት በሀገሪቱ እየተተገበሩ በሚገኙ ጊዜያዊ ህጎች ላይ አስገዳጅ ያልሆኑ ምክረ ሃሳቦችንም ለማቅረብ ጭምር እንደሆነ ተገልጿል።
 

26 Feb 2025, 12:03