MAP

በሱዳን እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት የተፈናቀሉ ሰዎች በሱዳን እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት የተፈናቀሉ ሰዎች  (AFP or licensors)

ሱዳን ሰብዓዊ ቀውስ ውስጥ ባለችበት በአሁኑ ወቅት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አፋጣኝ እርምጃ እንዲወሰድ አሳሰበ

በሱዳን የሰብዓዊ ቀውሱ እየጨመረ በመምጣቱ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ አፋጣኝ እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት በሱዳን ለሁለት ዓመታት ያክል በተካሄደው የእርስ በርስ ግጭት ምክንያት የተከሰተውን ሰብአዊ ቀውስ ለመፍታት አፋጣኝ እርምጃ እንዲወሰድ መጠየቁ ተነግሯል።

በሱዳን ጦር ሃይሎች እና በፈጣን ድጋፍ ሰጪ ሃይሎች መካከል እየተካሄደ ያለው ግጭት ከፍተኛ ስቃይ አስከትሏል ያሉት የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ ተወካይ ኤደም ወሶርኑ፥ ከአገሪቱ ህዝብ ከግማሽ በላይ የሚሆነው ወደ 24.6 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ ለከፍተኛ ረሃብ የተጋለጠ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ጠቁመዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት ከ12 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ቤት ንብረታቸውን ጥለው እንደተፈናቀሉ እና 3.4 ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ ድንበር ጥሰው እንደተሰደዱ ገልጸዋል።

በሃገሪቱ የተከሰተው ግጭት የጤና አገልግሎት ተቋማትን ያወደመ ሲሆን፥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህጻናት ከትምህርት ገበታቸው ውጪ እንዲሆኑ እንዳደረገ እና ጦርነቱን ትከትሎ በአከባቢው ጾታዊ ጥቃት በእጅጉ መስፋፋቱ ተገልጿል።

አመፅ በመላ አገሪቱ ተስፋፍቷል
አቶ ወሶርኑ እንደገለጹት የዛምዛም የተፈናቃዮች ካምፕ እና ካርቱም እንዲሁም ደቡባዊ የሃገሪቱ ክልሎችን ጨምሮ በሰሜን ዳርፉር ግዛት አስደንጋጭ ክስተቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በውሳኔ ቁጥር 2739 (2024) ከስምንት ወራት በፊት የፈጣን ድጋፍ ሰጪ ሃይሉ የግዛቱ ዋና ከተማ በሆነችው ኤል ፋሸር ላይ የሚያደርገውን ከበባ እንዲያቆም ውሳኔ ቢያስተላልፍም፥ በሰሜን ዳርፉር የሚኖሩ ሰላማዊ ዜጎች አሁንም ድረስ ጥቃት እየደረሰባቸው እንደሆነ ተገልጿል።

ከዚህም ባለፈ በዛምዛም ካምፕ እና አካባቢው ያለው ሁከትና ብጥብጥ ተባብሶ የቀጠለ ሲሆን፥ የሳተላይት ምስሎች እንደሚያሳዩት ከባድ መሳሪያዎች ጥቅም ላይ መዋላችውን እና ዋና ዋና የገበያ ስፍራዎች መውደማቸውን በማረጋገጥ፥ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች በካምፑ ውስጥ ለከፍተኛ ረሃብ መጋለጣቸውን ጭምር አመላክቷል።

በአከባቢው የሚገኘው የጸጥታው ሁኔታ እያሽቆለቆለ በመምጣቱ ድንበር የለሽ የህክምና ባለሙያዎች ቡድን በዛምዛም ካምፕ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ለማቆም እንደተገደደ የገለጸ ሲሆን፥ የዸም ምግብ ፕሮግራም በበኩሉ በካርድ ላይ የተመሰረተ የምግብ እርዳታ ስርጭቱን ማቆሙን አረጋግጧል።

ተቋሙ ካለፈው ነሃሴ ወር ጀምሮ በዛምዛም ካምፕ የረሃብ ሁኔታ መከሰቱን ቢረጋገጥም አንድ ዙር የሰብአዊ አቅርቦቶችን ብቻ ወደ ካምፑ ማጓጓዙን ገልጿል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አፋጣኝ እርዳታ ካልተደረገ በሚቀጥሉት ሳምንታት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለረሃብ ሊጋረጡ እንደሚችሉ አስጠንቅቋል።
 

28 Feb 2025, 13:39