MAP

በዲሞክራሳዊት ሪፐብሊክ ኮንጎ ተባብሶ የቀጠለው ግጭት በዲሞክራሳዊት ሪፐብሊክ ኮንጎ ተባብሶ የቀጠለው ግጭት   (AFP or licensors)

የተ. መ. ድ. የኤም 23 አማፂያን ግስጋሴ እየተጠናከረ በመጣበት በአሁኑ ወቅት በዲሞክራሳዊት ሪፐብሊክ ኮንጎ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ጠየቀ

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ውስጥ የሚገኙ ፀረ-መንግስት ታጣቂዎች ጦርነቱን በአስቸኳይ እንዲያቆሙ እና አሁን ከተቆጣጠሩት ሁሉም አካባቢዎች ለቀው እንዲወጡ በሙሉ ድምጽ መጠየቁ ተገልጿል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ኮንጎ ውስጥ የሚገኙ ፀረ-መንግስት ታጣቂ አማፂያን ከያዟቸው የኮንጐ ከተሞች እንዲወጡ እና የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ጠይቋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በምስራቃዊ ኮንጎ የሚገኘው የኤም 23 አማፅያን ጦርነቱን በአስቸኳይ እንዲያቆም እና ከያዛቸው ግዛቶች እንዲወጣ የሚጠይቅ የውሳኔ ሃሳብ የካቲት 14 ቀን 2017 ዓ.ም. በሙሉ ድምጽ ያጸደቀ ሲሆን፥ ምክር ቤቱ ግጭቱን በሚያራዝሙ አካላት ላይ ማዕቀብ እንደሚጣልባቸውም ዝቷል።

ይህ ጥሪ የቀረበው የኤም 23 አማፂያን ጉልህ በሆነ ሁኔታ የሃገሪቷ ዋና ከተማ የሆነችውን ቡካቩን ሙሉ በሙሉ በመቆጣጠር ወደ ሌሎች ከተሞች በፍጥነት መስፋፋታቸውን ተከትሎ እንደሆነም ተነግሯል።

በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተልዕኮ ኃላፊ ቢንቱ ኬይታ እንዳሉት በሩዋንዳ የሚደገፉት ኤም 23 አማጽያን በምስራቃዊ ሰሜን ኪቩ ግዛት የሰላም ማስከበር ስራውን እያደናቀፉ እንደሆነ የገለጹ ሲሆን፥ በሩዋንዳ መከላከያ ሃይል በመታገዝ የሰሜን ኪቩ የተወሰኑ ክፍሎች በኤም 23 አማፅያን በመያዛቸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰላም አስከባሪ የተልእኮ መስፈርቶችን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ እንዳይችል ክፉኛ እንደጎዳው አሳስበዋል።

ኬይታ አክለውም አማፅያኑ የተልእኮው ቡድን ሲቪሎችን የመጠበቅ እና የህይወት አድን ስራዎችን እንዳይሰራ እንቅፋት እንደሆኑም ጭምር ገልጸው፥ በዚህም ምክንያት የሰብአዊ አደጋ ስጋትም እየጨመረ መምጣቱን አስረድተዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃ-ሪች በበኩላቸው እንደዘገቡት በደቡብ ኪቩ በምትገኘው ኡቪራ እየተካሄደ ባለው ግጭት የሰብአዊ እርዳታ ሰራተኞች ችግር ውስጥ የወደቁ ሰዎችን ለማግኘት እና የህክምና ዕርዳታ ለመስጠት ትልቅ ፈተና እየገጠማቸው መሆኑን ገልጸዋል።

በግጭቱ አከባቢ የሚገኙ ሆስፒታሎች በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን ሰላማዊ ዜጎች በየቀኑ ተቀብለው እያስተናገዱ እንደሆነም መረጃዎች እያሳዩ ይገኛሉ።

በካሌህ ግዛት ባለፈው ሳምንት ብቻ ከ50,000 በላይ ሰዎች አከባቢያቸውን ጥለው ለመሰደድ የተገደዱ ሲሆን፥ በርካቶች ጎረቤት ሃገር ወደሆነችው ቡሩንዲ እንደተሰደዱ ተገልጿል።

ከየካቲት ወር መጀመሪያ ጀምሮ አብዛኞቹ ሴቶች እና ህጻናት የሆኑበት ከ40,000 የሚበልጡ የኮንጎ ዜጎች ከለላ ለማግኘት ቡሩንዲ መግባታቸው ታውቋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ እና የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በጋራ በመሆን በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እየተካሄደ ያለው ግጭት በአፋጣኝ የተኩስ አቁም ስምምነት ተደርጎ እንዲቆም ጠይቀዋል።

ሁለቱ መሪዎች በስልክ ካደረጉት ውይይት በኋላ እንደገለጹት ቀውሱን ለማስቆም የሚያስችሉ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን ለመደገፍ ቃል የገቡ ሲሆን፥ ይህም የአመቻቾችን ሹመት፣ የተኩስ አቁም ትግበራን እና ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት ሰፊ የፖለቲካ ሂደትን እንደሚያካትትም ጭምር ገልጸዋል።
 

24 Feb 2025, 15:24