ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ፥ ሰብዓዊነትን በማክበር ሌሎችን ማገልገል እንደሚገባ አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
“ታሪክን መረዳት እና መተረክ፣ ከልብ በመነጨ ዕውቀት፣ ፍቅር በተሞላበት ጥበብ እና ግራ በማያጋቡ መንገዶች እውነትን እና ውሸትን በመለየት፥ ባጭሩ የበለጠ ሰው እየሆኑ መምጣት ይገባል” ሲሉ የቅድስት መንበር መገናኛዎች ጽሕፈት ቤት ዋና ተጠሪ ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ፥ በጋና መዲና አክራ እስከ ነሐሴ 11/2017 ዓ. ም. ድረስ፥ “በቴክኖሎጂ ዕድገት መካከል ያለው ሚዛን እና በሰው ሠራሽ አስተውሎት ዘመን እሴቶችን ጠብቆ ማቆየት” በሚል ጭብጥ ላይ በመካሄድ ላይ ለሚገኝ የአፍሪካ ካቶሊካዊ ጋዜጠኞች ኅብረት ጉባኤ መልዕክት ልከዋል።
እውነተኛው፣ ፍትሃዊ እና መልካም
ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ በመልዕክታቸው፥ በተቋማት እና በሕዝቦች መካከል የሚደረግ ግንኙነት ወደ ማኅበራዊ ሚዲያ ጽንሰ-ሃሳብ በተቀየረበት በዚህ ዘመን፥ አልጎሪዝም እና እነርሱን የሚያቀነባብሩት ማሽኖች የሰውን ልጅ በእውነት፣ በዕውቀት፣ በኅሊና እና በውበት እንዴት ሊያገለግሉ ይችላሉ” ሲሉ ያቀረቡትን ጥያቄ በቅድስት መንበር መገናኛዎች ጽሕፈት ቤት የነገረ-መለኮት እና ሐዋርያዊ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት የሆኑት ሞንሲኞር ጃንቪዬር ያሜዎጎ ከ 30 አገራት ለተወጣጡ 150 የጉባኤው ተሳታፊዎች በንባብ አቅርበዋል።
ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ፥ በሰው ልጅ እና በአልጎሪዝም መካከል ያለውን ግንኙነት ማሰላሰል እንደሚገባ ባሳሰቡት መልዕክታቸው፥ "አልጎሪዝም እና አቀናባሪዎቻቸው እውነተኛውን፣ ፍትሃዊ እና መልካም የሆነውን ችላ በማለት ሁሉን ነገር የሚያበላሽ የአገዛዝ ሥርዓት እንዳይፈጥሩ በመከላከል የግለሰብን ልዩነት እና ክብርን ለመጠበቅ መስዋዕትነትን መክፈል እንደሚገባ አሳስበዋል።
“መስቀለኛ መንገድ ላይ ነን” ያሉት ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ ቀጥለውም፥ በአንድ በኩል “በአምባገነን አስተሳሰብ የሚመራ የማሽን አምባገነንነት አለ” ብለው፥ በሌላ በኩል ደግሞ “እውነት የሌለበት የሰው ልጅ ነፃነት አለ” ብለው፥ በመሆኑም የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በቴክኖሎጂ ዕድገት በተለይም “በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ” ወይም በሰው ሠራሽ አስተውሎት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ባለው ዓለም ውስጥ የሰው ልጅ እሴቶችን በማሳደግ እና በማቆየት አስፈላጊነት ላይ የተለያዩ ተከታዮቻቸውን ለማስተማር ያላቸውን ችሎታ እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርበዋል።
እርስ በርስ በመደጋገፍ በኅብረት መጓዝ
“ከሁሉ በፊት የእርስ በርስ ግንኙነት የሚመሠረተው እራስን ለሌላው በጋራ በማቅረብ ነው” በማለት ያስረዱት ዶ/ር ሩፊኒ፥ “ኅብረት ማለት እርስ በርሳችን አባል እንድንሆን የሚያደርገን እና በሲኖዶሳዊነት መንፈስ የቤተ ክርስቲያን የግንኝነት መንገድ እንደሆነ አስረድተዋል። ዛሬ ምድራችን በሁከት እና በጦርነት አዙሪት በወደቀችበት ወቅት ለጋራ ጥቅም የመገናኛ እና የውይይት ቦታዎችን ማመቻቸት እና ስለ ሰላም ማሰብ አስቸጋሪ እየሆነ በመጣበት ወቅት የትኛውም ቤተ ክርስቲያን ወይም ማኅበረሰብ በተናጥል ለመኖር ማሰብ እንደሌለበት አሳስበው፥ ደኅንነታችን ከሌሎች ሰዎች ደኅንነት ጋር የተገናኘ መሆኑን አስረድተዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በቅርቡ እንደገለጹት፥ ቴክኖሎጂው የሚፈቅደንን ድንገተኛ እና መደበኛ ያልሆነ ትስስር እንደ ሃብት እና ጸጋ በማየት፥ እየጨመረ የመጣውን የቤተ ክርስቲያን የእኛነት ግንዛቤን እና አስተዋይነትን ለማስፋፋት “አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ” ወይም የሰው ሠራሽ አስተውሎት የቁጥጥር ማዕቀፎችን በተገቢ የሥነ-ምግባር አስተዳደር ውስጥ ጸንተው እንዲቆዩ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በጉባኤው ላይ የቀረቡ ዝግጅቶች
ባለፈው እሑድ በተካሄደው የጉባኤው መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ አዘጋጅ ኮሚቴው፥ ተሳታፊዎችቹ በእምነት፣ በሙያዊ ትብብር እና በጋራ ዓላማ እየተሰባሰቡ መሆናቸውን ገልጾ፥ የጋና ጋዜጠኞች ማኅበር የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ሥራቸውን ዘላቂ በሆነው እውነት፣ ፍትሃዊነት፣ ኃላፊነት እና ርህራሄ እሴቶች ላይ በቁርጠኝነት ማስቀጠል አስፈላጊ መሆኑን ገልጿል።