“ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እና የአልጄሪያ ሰማዕታት ምስክርነት”
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ “በሕዝቦች መካከል የሚደረግ ወዳጅነት” በሚል ርዕሥ ጣሊያን ውስጥ ሪሚኒ ከተማ ለተዘጋጀው ስብሰባ ባስተላለፉት መልዕክት፥ የአልጄሪያ ሰማዕታትን በማስመልከት የቀረበው ኤግዚቢሽን፥ “በሃይማኖቶች እና በባሕሎች መካከል ያለውን የመከፋፈል እና ያለመተማመን ግንብ በማፍረስ የእግዚአብሔር ልጅ ሙሉ በሙሉ ስጋን መልበስ እና ራሱን ለሌሎች ድነት አሳልፎ መስጠትን እንዲሁም በምድረ በዳ ውስጥ መኖርን አጉልቶ የሚያሳይ የቤተ ክርስቲያን ጥሪ ነው” ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ የእርስ በርስ ግንኙነት እና ትኅትና እውነተኛ የተልዕኮ መንገድ መሆናቸውን አስረድተዋል። ይህ በሪሚኒ ከተማ ለተሰበሰቡት ብቻ ሳይሆን ለመላዋ ቤተ ክርስቲያን ውድ እና ትርጉም ያለው ማሳሰቢያ ነው። “ሐዋርያዊ ተልዕኮ ማንነትን ከመግለጽ በተለየ ራስን ለሌሎች ማሳየትን የማይፈልግ እስከ ሰማዕትነት ድረስ ራስን በስጦታነት ማቅረብን፣ ሌተ ቀን በደስታም ሆነ በመከራ ወቅት ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ጌታ መሆኑን የሚገልጹበት መንገድ ነው” በማለት ተናግረዋል።
የአልጄሪያ ሰማዕታት ኤግዚቢሽን፥ ሰማዕታቱ ራሳቸውን ለአገልግሎት ሙሉ በሙሉ እንደሰጡ የሚያሳይ፣ በሁሉም መንገድ ሕይወትን ከሌሎች ጋር በመካፈል፣ በወንድማማችነት፣ በወዳጅነት፣ እርስ በርስ በመቀራረብ ተጨባጭ ዕርዳታን በማድረግ መስክረዋል። ትኩረትን ሳይፈልጉ፣ ስለ ብዛታቸው ሳይጨነቁ እና በጥንቃቄ በታቀዱ ስልቶች ላይ ሳይመኩ ኖረዋል።
እንደ ጎርጎርሳውያኑ በ1996 ዓ. ም. በሰማዕትነት የተገደሉት አቡነ ፒየር ክላቬሪ ባቀረቡት ስብከት ይህን በማስመልከት በግልጽ ተናግረዋል። በእስላማዊ ጽንፈኞች ከመገደላቸው ጥቂት ቀደም ብሎ አልጄሪያ ውስጥ የዕለት ተዕለት ሕይወታቸውን ለምን አደጋ ላይ እንደጣሉ በተጠየቁ ጊዜ ሲመልሱ፥ “እኛ ቤት የት አለን? በአልጄሪያ የምንኖረው በዚያ በተሰቀለው መሢሕ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምክንያት ነው። በሌላ ምክንያት ወይም ሌላን ሰው የመጠበቅ ፍላጎት እና ተጽዕኖ የለንም፤ ኃይልም የለንም። ነገር ግን በአልጄሪያ የምንኖረው የታመመ ወንድሙን እጅ እንደሚይዝ፣ ፊቱን እንደሚጠርግ ሰው በመሆን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር ስንል በግፍ የሚሠቃዩ በሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሐን ሰዎችን ለመርዳት ነው”
በመቀጠልም “የኢየሱስ ክርስቶስ አካል የሆነችው ቤተ ክርስቲያን ከሁሉም በፊት ካልሆነች የት መሆን አለባት? ቤተ ክርስቲያን ለኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ቅርብ ካልሆነች እንደምትሞት አምናለሁ። ቤተ ክርስቲያን እራሷን በሌሎች መካከል እንደ አንድ ሃይል የምታቀርብ ከሆነ፣ እንደ አንድ ሰብዓዊ ድርጅት ወይም አስደናቂ መንፈሳዊ እንቅስቃሴ የምትመለከት ከሆነ ለጊዜው ልታንጸባርቅ ትችል ይሆናል ነገር ግን እንደ እሳት የሚያቃጥል የእግዚአብሔርን ፍቅር በውስጧ የለም።
ስለታም እና አሳሳቢ ፍርድ ቢሆንም፥ ቤተ ክርስቲያን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ስትርቅ ትሞታለች። ዓለማዊ ሆና ራሷን ወደ ድርጅትነት ስትቀይር፣ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ሥልጣንን ስታሳድድ፣ በቁጥር ብዛት ስትመካ፣ ወንጌላዊነቷን የኢየሱስ ክርስቶስን ስም በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ እየደጋገመች ለመጥራት ስታስብ፣ እርሱን በመከተል ድሆችን በተጨባጭ የማትረዳ ከሆነ፣ የእምነት ምስክርነትን ወደ ትርኢት ስትቀይር፣ በሌላው ብርሃን መሆኑን ረስታ በራሷ ብርሃን እንደምታበራ የምታስብ ከሆነ ቤተ ክርስቲያን ትሞታለች።
የአልጄሪያ ሰማዕታት ምስክርነት ከዛሬው ራስ ወዳድነት የራቀ፥ ለተግዳሮት እና ለወንጌል ምንነት ማሳሰቢያን የሚያቀርብ ተቃራኒ ምልክት ነው። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ለስብሰባው ተሳታፊዎች ባስተላለፉት መልዕክት መዝጊያ ላይ፥ ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን እና ሐዋርያዊ አስተምህሮአቸውን አስታውሰው፥ ለድሆች ያለው አማራጭ ባሕላዊ፣ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ ወይም ፍልስፍናዊ ብቻ ሳይሆን ከምንም በፊት ሥነ-መለኮታዊ እንደሆነ፥ እግዚአብሔር ትሑታንን፣ ትንንሾችን እና አቅመ ደካሞችን በመምረጥ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ማኅፀን ውስጥ ሆኖ ታሪኩን ወደ ታሪካችን ለውጦ በመጻፍ ከእነርሱ መካከል አንዱ ሆነ። እውነተኛው እውነታ ግን ከሌላ አቅጣጫ የሚያዩትን የሚያጠቃልል፣ ከባድ ውሳኔ በሚደረግበት የሥልጣን ደረጃ ላይ የማይታዩ የእውነታ ገጽታዎችን የሚገነዘቡት ናቸው። የአልጄሪያ ሰማዕታት የክርስትና ደማቸውን ከብዙ ሙስሊሞች ጋር በማዋሃድ እስከ መጨረሻው ድረስ በመመስከር የአክራሪነት ሰለባ የሆኑት በዚህ መንገድ ነው።