MAP

ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን በኔፕልስ በተዘጋጀው 75ኛ ብሔራዊ የሥርዓተ አምልኮ ሳምንት መክፈቻ ላይ (ከግራ በኩል ሁለተኛ) ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን በኔፕልስ በተዘጋጀው 75ኛ ብሔራዊ የሥርዓተ አምልኮ ሳምንት መክፈቻ ላይ (ከግራ በኩል ሁለተኛ) 

ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን “በጋዛ እየሆነ ባለው ነገር እጅግ ተደናግጠናል” ሲሉ ተናገሩ

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን የጣሊያን ከተማ በሆነች ኔፕልስ ውስጥ በተዘጋጀው 75ኛ ብሔራዊ የሥርዓተ አምልኮ ሳምንት መክፈቻ ላይ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል። ብጹዕናታቸው ለተሳታፊዎች ባሰሙት ንግግር፥ እስራኤል በጋዛ ላይ በፈጸመችው የቦምብ ጥቃት የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን ገልጸው፥ “ጥቃቱ ምንም ትርጉም የለውም” ካሉ በኋላ ሰብዓዊ ቀውሱ እየተባባሰ እንደሚሄድ አስጠንቅቀዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን የጣሊያን ከተማ በሆነች ኔፕልስ ውስጥ በተዘጋጀው 75ኛ ብሔራዊ የሥርዓተ አምልኮ ሳምንት መክፈቻ ጎን ለጎን ባደረጉት ንግግር፥ “በጋዛ እየተፈጸመ ያለውን ነገር መላው ዓለም በአንድ አቋም አውግዞታል” ብለው፥ ሁኔታው እጅግ እንዳስደነገጣቸው ተናግረዋል።

እስራኤል በካን ዮኒስ በሚገኘው ናስር ሆስፒታል ላይ በፈጸመችው ጥቃት አምስት ጋዜጠኞችን ጨምሮ 20 ሰዎች መሞታቸውን ብጹዕነታቸው ጠቅሰው፥ “ይህ ጥቃት ትርጉም የለሽ ነው” ካሉ በኋላ “የእርቅ እና የሰላም መፍትሄን ለማግኘት በሩ ዝግ እንደሆነ፣ መከራው ​​እየጨመረ እና እየተወሳሰበ፣ ከሰብአዊነት አንፃር አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱ ከቀን ቀን እያየን ያለነውን መዘዝ አስከትሏል” ብለዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን በዩክሬን ያለው ጦርነት ብዙ ፖለቲካዊ ውይይቶች እንደሚያስፈልገው አበክረው ገልጸዋል። በንድፈ ሃሳብ ደርጃ ብዙ መፍትሄዎች እና ወደ ሰላም ሊመሩ የሚችሉ ብዙ መንገዶች መኖራቸውን ገልጸው፥ ነገር ግን በተግባር ላይ መዋል እንዳለባቸው እና ይህም ደግሞ የመንፈስ ዝግጁነቶችን እንደሚጠይቅ አስረድተዋል።

“መላው ዓለም ተስፋ ያስፈልገዋል” ብለው፥ ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የከፈቱትን የኢዮቤልዩ በዓል አስታውሰው በመቀጠልም፥ የበዓሉ ​​መሪ ቃል ዓላማ በትክክል የተስፋ ማገገም ጊዜን የሚገልጽ መሆኑን አስረድተዋል።

“በተለይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተስፋን የሚሰጡ ነገሮች በሌሉበት በዚህ ወቅት ከተስፋ በላይ ተስፋ እንደሚያስፈልግ ተናግረው፥ እነዚህ ቅርብ ቀናት በግጭት ውስጥ የሰላም መንገዶችን ማስኬድ አስቸጋሪ መሆኑን በድጋሚ እንደሚያሳዩ በማስረዳት፥ “ሆኖም ግን እጅ ከመስጠት ይልቅ ለሰላም እና ለእርቅ መሥራታችንን እንቀጥላለን” ሲሉ አጥብቀው ተናግረዋል።

 

 

26 Aug 2025, 17:03