MAP

የወጣቶች ኢዮቤልዩ በዓልን ለማክበር ወደ ሮም የመጡ ወጣት ተሬዛ እና ወጣት ሳሙኤል የወጣቶች ኢዮቤልዩ በዓልን ለማክበር ወደ ሮም የመጡ ወጣት ተሬዛ እና ወጣት ሳሙኤል  (© Matthias Linus Möller)

ወጣቶች በሮም የኢየሱስን ድንቅ ሥራ ማየት በመቻላቸው የተሰማቸውን ደስታ ገለጹ

በወጣቶች የኢዮቤልዩ በዓል ላይ ለመገኘት ከአውስትሪያ ወደ ሮም የመጡ ወጣቶች፥ የኢየሱስ ክርስቶስን ድንቅ ሥራ ለመመልከት በመቻላቸው ደስተኞች ነን” ሲሉ ገለጹ። “አንድ ሰው በእምነት ጠንክሮ ሲገኝ ለዓለም አቀፍ ሰላም መሥራት እንደሚቻል ማሰብ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው” ብለው፥ ቤተሰባቸውን እና ማኅበረሰባቸውን በሚመለከቱ ቅርብ ጉዳዮች ላይም ተወያይተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ወጣቶቹ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን እና ከተለያዩ አገራት የመጡ በርካታ ወጣቶች አንድ ላይ ተሰባስበው ኢየሱስ ክርስቶስን ሲመለከቱ ማየታቸው፣ ለእርሱ ሲኖሩ እና ሕይወታቸውን ለእርሱ አደራ ሲሰጡ ማየት ያስደሰታቸው መሆኑን፥ ከሰኞ ሐምሌ 20-27/2017 ዓ. ም. ድረስ በሮም በሚከበረው የወጣቶች ኢዮቤልዩ በዓል ላይ የተገኙት የአውስትሪያ ወጣቶች ገልጸዋል።

ከአውስትሪያ ሁለተኛዋ ሰፊ ግዛት ስቲሪያ የመጡት የሃያ ዓመት ዕድሜ ወጣት ሳሙኤል እና የአሥራ ስምንት ዓመት ዕድሜ ወጣት ቴሬዛ የአውስትሪያ ወጣቶች በሮም ማክሰኞ ሐምሌ 22/2017 ዓ. ም. ባካሄዱት ስብሰባ ላይ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል።

ወጣቶቹ ለስብሰባው ተሳታፊዎች ባደረጉት ንግግር፥ በሰፊው ሲጠበቅ የቆየውን የቅዱስ ዓመት ዝግጅቶችን ከእኩዮቻቸው ጋር በሮም ለመሳተፍ በመብቃታቸው እንዲሁም እምነታቸውንም ለሌሎች ወጣቶች ለማካፈል በመቻላቸው የተሰማቸውን ታላቅ ደስታ ገልጸዋል።

ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ መቅረብ

ወጣቶቹ በተጨማሪም የዓለም አቀፋዊት ቤተ ክርስቲያንን አንድነት በተጨባጭ መመልከታቸውን እና መለማመዳቸውን እንዲሁም ሙሉ በሙሉ የቤተ ክርስቲያን አባል መሆናቸው ደስታን እንዳጎናጸፋቸው ገልጸው፥ ቤተ ክርስቲያንም በበኩሏ ወጣቶችን የምትፈልግ መሆኗ አስረድተዋል።

ይህን ጉዞ ከታማኝ ጓደኞቻቸው ጋር ሆነው በኅብረት መጓዝ እና ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ እና ወደ አብ ዘንድ መቅረብ እጅግ አስደናቂ ነው” ያሉት ወጣቶቹ፥ የአምልኮት፣ የአስተንትኖ እና በምሽት የመቁጠሪያ ጸሎትን አብረው ማቅረባቸው አስደሳች የጋራ ጊዜያት ናቸው” ሲሉ አስረድተዋል።

እምነት ብርታትን ይሰጣል!

በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ያላሰለሰ የሰላም ጥሪ ላይ በማሰላሰል ሃሳባቸውን የገለጹት ወጣቶቹ፥ እምነት በአስቸጋሪ ጊዜያት ውስጥ ብርታት እንደሚሰጣቸው አብራርተው፥ ወጣት ሳሙኤል ተማሪ እንደመሆኑ በኅብረተሰብ እና በትምህርት ቤት ማኅበረሰቦች ውስጥ የሚታዩ አለመረጋጋቶች እና ጦርነቶች ተማሪዎችንም ጭምር እንደሚጎዱ ማስተዋሉን ተናግሮ፥ ያም ሆኖ እነዚህን ሁኔታዎች ለመቋቋም እና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለማስኬድ እምነት ኃይል እንደሆነ መረዳቱን ገልጿል።

“እምነታችንን በጋራ የምንኖርበት መንገድ ያበረታናል!”

ወጣት ቴሬዛ በበኩሏ በስብሰባው ወቅት ለቫቲካን መገናኛ እንደተናገረችው፥ “በችግር ውስጥ ብንገኝም ጠንካራ ማኅበረሰብ እንዳለን አምናለሁ” ብላ፥ ይህን የአውስትሪያ ወጣቶች ካደረጉት ስብሰባ መረዳት እንደሚቻል፣ በወጣቶቹ መካከል የነበረው ፈገግታ እና እምነትን በኅብረት ለመኖር የሚከተሉትን መንገድ የሚያበረታታ እንደሆነ እና ይህን ማድረጋቸውን ከቀጠሉ ነገሮች መልካም እንደሚሆኑ ያላትን እምነት ገልጻለች።

“ስለ ሰላም ካወራን ብዙ የሰላም ዓይነቶች አሉ” ያለች ወጣት ተሬዛ፥ በዛሬው ትውልድ ውስጥ ብዙውን ጊዜ የሚጎድለው የልብ ሰላም እንደሆነ ገልጻ፥ የአገሯ ወጣቶች ሰላማዊ በሆነች አውስትሪያ ውስጥ መኖራቸው ዕድለኞች እንደሚያደርጋቸው ተናግራ “ነገር ግን የልብ ሰላም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እና እንደዚህ ባለ ፌስቲቫል ላይ በአዲስነት ሊለማመዱት የሚችሉት ነገር እንደሆነ እና ይህም ብዙውን ጊዜ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ዓሥራ አራተኛ የሚናገሩት የሰላም ዓይነት እንደሆነ አምናለሁ” ስትል አስረድታለች።

በእምነት መቆም

“በእርግጥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ካኅናት፣ ምዕመናን ሁላችንም ለዓለም ሰላም በጋራ እንጸልያለን” ያለችው ወጣት ተሬዛ፥ ለውስጥ ሰላም መጸለይ እንደሚገባ ምክንያቱም ቤተ ክርስቲያን እያንዳንዱን ሰው በግል እንደምትመለከት እና እያንዳንዱ ሰው የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ አስረድታለች።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ የኢዮቤልዩ በዓላቸውን ለማክበር ወደ ሮም ለመጡት ወጣቶች ሰላምታ ሲሰጡ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ የኢዮቤልዩ በዓላቸውን ለማክበር ወደ ሮም ለመጡት ወጣቶች ሰላምታ ሲሰጡ   (@Vatican Media)

በዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ በግል እምነት ብቻችን መቆማችን እውነት ይመስለኛል” ያለችው ወጣት ተሬዛ፥ ዘወትር ከሚያምኑት ጓደኞች ጋር መሆን እንደማይቻል እና በዚህም ምክንያት የብቸኝነት ስሜት ሊሰማ እንደሚችል፥ ነገር ግን በእምነት የሚያበረታታ ማኅበረሰብ ከተገኘ እምነትን ማሳደግ እንደሚቻል እና ይህም በጎ ምልክት እንደሆነ አስረድታለች።

የአካባቢያችን እና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች

ወጣት ቴሬዛ የወጣቶች ኢዮቤልዩ በዓል የልብ ሰላምን ከሌሎች ጋር ለመካፈል እንዳስቻላት የገለጸች ሲሆን፥ ወጣትነት ብዙውን ጊዜ የተግዳሮት ወይም የችግር ጊዜ ተደርጎ እንደሚወሰድ ተናግራ፥ ነገር ግን በኢዮቤልዩ በዓል ወቅት ብዙ ወጣቶች ሮም ውስጥ በአንድነት ተሰብስበው ማየት ሰላምን እንዳጎናጸፋት አስረድታለች።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፥ “የምንገኘው ብዙ ግጭቶች እና ጦርነቶች ባሉበት ጊዜ ውስጥ ነው” ያለው ሌላው ወጣት ስቴፋን፥ ጦርነትን ጨምሮ በሌሎች ማኅበራዊ ችግሮች ምክንያት እጅግ በርካታ ሰዎች እየሞቱ እና የአካል ጉዳት እየደረሰባቸው እንደሚገኝ አስታውሶ፥ ነገር ግን ሌሎች በርካታ ሰዎች እነዚያን ዓለም አቀፍ ጉዳዮች በማስመልከት ሲናሚናገሩ መቆየታቸውን ገልጾ፥ ነገር ግን እርሱ ርቆ ሳይሄድ በአቅራቢያ የሚታዩትን ግጭቶችን መጠቆም እንደሚፈልግ፥ እነርሱም በቤተሰብ ውስጥ፣ በጓደኛሞች መካከል፣ በማኅበረሰቦች ውስጥ በየቀኑ የሚታዩ ክርክሮች እና ስሜታዊ ቁስሎች ዘላቂ ጠባሳ ትተው የሚያልፉ መሆናቸውን አስረድቷል።

በኢዮቤልዩ አውድ ውስጥ ቤተሰብን፣ ጓደኝነትን እና ማኅበረሰብን የሚያጋጥሙ በርካታ ተግዳሮቶችን ጠቅሶ እርስ በርስ ለመወያየት ዕድል በማግኘቱ ለወጣቶች ኢዮቤልዩ በዓል ያለውን አድናቆት ወጣት ስቴፋን ገልጿል።

02 Aug 2025, 17:04