MAP

ቱኒዝያ ውስጥ ድሆች የፕላስቲክ ዕቃዎችን ሲሰበስቡ   ቱኒዝያ ውስጥ ድሆች የፕላስቲክ ዕቃዎችን ሲሰበስቡ   (AFP or licensors)

ቅድስት መንበር በማደግ ላይ ያሉ ወደብ አልባ አገራትን ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጣለች

በማደግ ላይ የሚገኙ ወደብ አልባ አገራትን በማስመልከት በቱርክሜኒስታን ሦስተኛው ዓለም አቀፍ ጉባኤ ተካሂዷል። ጉባኤውን የተካፈሉት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ ሞንሲኞር አርናኡድ ዱ ቼይሮን ዴ ቦሞንት፥ ለጉባኤው ተሳታፊዎቹ ባስተላለፉት መልዕክት፥ ቅድስት መንበር በማደግ ላይ ያሉ ወደብ አልባ ሀገራትን ለመደገፍ ያላትን ቁርጠኝነት በድጋሚ በማረጋገጥ፥ድህነትን በማጥፋት እና መሠረታዊ የሰው ልጅ ዕድገትን በማጎልበት፥ በአንድነት እና በፍትህ ላይ ተጨባጭ ዕርምጃ እንዲወሰድ ጠይቀዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ወደብ አልባ አገራትን በማስመልከት በአዋዛ ከተማ ሐምሌ 30/2017 ዓ. ም. በተካሄደው ሦስተኛው ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ ንግግር ያደረጉት የቅድስት መንበር ልኡካን መሪ ሞንሲኞር አርናኡድ ዱ ቼይሮን ዴ ቦሞንት፥ ጉባኤውን ላዘጋጀች አገር ቱርክሜኒስታን እና ላስተባበረው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ምስጋናቸውን አቅርበው፥ “ጉባኤው በማደግ ላይ ለሚገኙ ወደብ አልባ አገራት የሚደረገውን ድጋፍ እና ሰብዓዊ ዕድገትን የሚጨምር የረዥም ጊዜ ዕርዳታን ለማረጋገጥ ዕድል የሚሰጥ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።

እጅግ አስቸኳይ ተግዳሮት

የቅድስት መንበር ተወካይ ሞንሲኞር ዴ ቦሞንት እንደተናገሩት፥ በማደግ ላይ የሚገኙት ወደብ አልባ አገራት ምንም እንኳን በመልክዓ-ምድራዊ፣ ባህላዊ እና ኢኮኖሚያዊ አውድ የተለያዩ ቢሆኑም፥ ሊቋቋሙት የማይችሉት ዘላቂ የዕዳ ሸክም፣ ከፍተኛ የትራንስፖርት ወጪዎች እና የአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነት እንደሚያጋጥማቸው ገልጸው፥ “ሆኖም ድህነት ትልቁ እና እጅግ አስቸኳይ ፈተና ሆኖ ቀጥሏል” ሲል አፅንዖት ሰጥቷል።

“ድህነት ኢኮኖሚያዊ ብቻ ሳይሆን ነገር ግን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መሠረታዊ ፍላጎቶችን በመንፈግ እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ ሰው የሰጠውን ሰብዓዊ ክብርን ይጎዳል” ሲሉ ተናግረው፥ በተለይም የአስፈላጊ አገልግሎቶች እጥረት በሚታይባቸው ገጠራማ አካባቢዎች ችግሩ እጅግ ከባድ እንደ ሆነ አስገንዝበዋል። “ድህነት የማይቀረፍ ነገር አይደለም” ያሉት የቅድስት መንበር ተወካይ ሞንሲኞር ዴ ቦሞንት፥ “ድህነት ፍትሃዊ ያልሆኑ መዋቅሮች እና የፖሊሲ ምርጫዎች ውጤት በመሆኑ ማሸነፍ እና ማስወገድ ይቻላል” ብለው፥ የድህነትን ባሕላዊ ገጽታ በማስታወስ የባሕል መብት መነፈግ እና የትምህርት ዕድል እጦት በሕዝቦች መካከል የኑሮ አለመመጣጠንን እንደሚያስከትል አስረድተዋል።

ንግድ እና ፍትህ

የቅድስት መንበር ልኡካን መሪ ሞንሲኞር ዴ ቦሞንት፥ በማደግ ላይ በሚገኙት ወደብ አልባ አገራት ውስጥ ያለውን ድህነትን ለማሸነፍ ትልቁ እንቅፋት ኢ-ፍትሐዊ የሆነ ዓለም አቀፍ ንግድ መሆኑን አስረድተዋል። “እውነተኛ ቸርነት” የሚለውን የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ አሥራ ስድስተኛ ሐዋርያዊ መልዕክት በመጥቀስ እንደተናገሩት፥ ንግድ በአግባቡ ከተያዘ ጠንካራ የዕድገት አንቀሳቃሽ ሊሆን እንደሚችል አስታውሰው፥ ነገር ግን ይህ እንዲሆን በፍትህ እና በአብሮነት የታነጸ፣ በዕቃዎች መዳረሻ መርህ ላይ የተመሠረተ እና ለሁሉ ሰው የተሟላ የዕድገት ሁኔታዎችን የሚያመቻች መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።

ፍትሃዊ ባልሆነ የንግድ ሥርዓት የተጎዱ አገራት የካፒታል እጥረት እና የውጭ ብድር ማሽቆልቆል እንደሚያጋጥማቸው፥ ይህ ደግሞ ዘላቂ ያልሆነ የአካባቢ ብዝበዛን በመፍጠር ድህነትን እንደሚስከትል በማስረዳት፣ ልማትን ወደ ምርት ልውውጥ ደረጃ ብቻ ከማውረድ ይልቅ የሳይንስ እና የቴክኖሎጂ ዕውቀት ማስተላለፍ ወደብ አልባ አገራት ራሳቸውን ችለው ድህነትን እንዲቋቋሙ የሚያስችል መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።

የሰውን ልጅ ማዕከል ማድረግ  

የቅድስት መንበር ልኡካን መሪ ሞንሲኞር ዴ ቦሞንት በመልዕክታቸው፥ “የሰው ልጅ የሁሉም ዓይነት የልማት ውጥኖች ማዕከል ሆኖ መቆየት አለበት” ብለው፥ “የንግድ እና የኢኮኖሚ ዕድገት ዓላማ ራሳቸውን ሳይሆን ነገር ግን የእያንዳንዱን ሰው ሁለንተናዊ ዕድገት እና የጋራ ተጠቃሚነትን ማስተዋወቅ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

በተባበሩት መንግሥታት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ ሞንሲኞር ዴ ቦሞንት፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛን በመጥቀስ ንግግራቸውን ሲያጠቃልሉ፥ የቅድስት መንበር ዘላቂ ተልዕኮ በሕዝቦች መካከል ስምምነትን በመፍጠር፥ እጅግ ለተቸገሩት እና ቅስማቸው ለተሰበረባቸው በሩቅ አካባቢዎች ለሚገኙ ሰዎች የማያቋርጥ አጋርነትን ማስፋፋት እንደሆነ አስረድተዋል።

 

11 Aug 2025, 16:17