በቅድስት መንበር የምእመናን፣ የቤተሰብ እና የሕይወት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አወቃቀር
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሁሉም የባህል እና የመልክዓ ምድራዊ አቀመጣጥ ሁኔታዎች ውስጥ የሚገኙ ወንዶችን እና ሴቶችን ለማቀፍ ባላቸው ፍላጎት የምእመናን ጳጳሳዊ ምክር ቤት እና የቤተሰብ ጳጳሳዊ ምክር ቤት ኃላፊነቶችን በማጣመር እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2016 ዓ. ም. በቅድስት መንበር ውስጥ ይህን አዲስ መዋቅር መሥርተዋል።
ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ጽሕፈት ቤቱ በመስኮች ስለ ብዙ ሰዎች የዕለት ተዕለት ሕይወት ማሰቡ ታዋቂ እንደሚያደርገው ገልጸዋል። የጽሕፈት ቤቱ ርዕሠ መስተዳድር ብጹዕ ካርዲናል ኬቪን ጆሴፍ ፋሬል ሲሆኑ አመራሩን በረዳት ጸሐፊነት የሚያግዙት አቡነ ዳሪዮ ጄርቫሲ እና ጸሐፊያቸው ዶ/ር ግሌሰን ደ ፓውላ ሱዛ ናቸው።
ታሪካዊ ማስታወሻዎች
ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “Sedula Mater” ወይም “ታታሪ እናት” በሚለው ደንብ መሠረት በሐዋርያዊ ሥልጣናቸው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በነሐሴ ወር 2016 ዓ. ም. ያቋቋሙት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቱ ምእመናንን፣ ቤተሰብን እና ሕይወትን የሚመለከቱ ጉዳዮችን የሚከታተል ሲሆን፥ ከዚህ ቀደም ለምእመናን እና ቤተሰብ ጳጳሳዊ ምክር ቤት በአደራ የተሰጠ ነበር።
ቀድሞ የነበረውን ጽሕፈት ቤት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ፥ “Catholicam Christi Ecclesiam” ወይም “የክርስቶስ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን” በሚለው ደንብ መሠረት በሐዋርያዊ ሥልጣናቸው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1967 ዓ. ም. የመሠረቱት ሲሆን፥ ይህም ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ በሰጠው ሃሳብ መሠረት “Apostolicam actuositatem” ወይም “ሐዋርያዊ ተግባር” ይፋ ያደረገውን ደንብ እውን አድርጓል።
ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ያቋቋሙት የወጣቶች ክፍል ከምዕመናን ጳጳሳዊ ምክር ቤት ጋር በመተባበር እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ1985 ዓ. ም. ጀምሮ የዓለም ወጣቶች ቀንን ከአገር ውስጥ ኮሚቴዎች ጋር በማዘጋጀት ተግባር ላይ ተሳትፏል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በሰኔ ወር 1988 ዓ. ም. ጽሕፈት ቤቱን እና አወቃቀሩን “Pastor Bonus” ወይም “መልካም እረኛ” በሚለው ሐዋርያዊ ደንብ መሠረት ከቅድስት መንበር ከፍተኛ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች ወይም “ሮማን ኩሪያ” መካከል እንዱ በማድረግ መሠረቱ።
የቤተሰብ መርምሪያው በበኩሉ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 1973 ዓ. ም. ያቋቋሙትን የቤተሰብ ኮሚቴ በመተካት፥ “Familia a Deo instituta” ወይም “በእግዚአብሔር የተመሠረተ ቤተሰብ” በሚለው ደንብ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1981 ዓ. ም. ተቋቋመ። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ1994 ዓ. ም. ጀምሮ ሲከበር ከቆየው የቤተሰብ ዓመት ጋር ጳጳሳዊ ምክር ቤቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በሮም የተካሄደውን ጨምሮ ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ጉባኤዎችን በማዘጋጀት ላይ ይገኛል።
የብቃት መመዘኛዎች
በቅድስት መንበር የምእመናን፣ የቤተሰብ እና የሕይወት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት፥ “Praedicate Evangelium” ወይም “ወንጌልን ስበኩ” በሚለው ሐዋርያዊ ደንብ መሠረት፥ በእግዚአብሔር ዕቅድ መሠረት የምእመናንን ሐዋርያነት፣ የወጣቶችን ሐዋርያዊ እንክብካቤን፣ ቤተሰብን እና ተልዕኮውን፣ አረጋውያንን እና ሕይወትን የማሳደግ እና የመጠበቅ ኃላፊነት አለበት። ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቱ እንደ ግለሰብም ሆነ እንደ ማኅበር፣ የሁሉንም ምእመናን ማለትም የመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች እና የማኅበረሰብ አባላት፣ በሲቪል እና በቤተ ክህነት ውስጥ የሚገኙ አባላት ጥሪ እና ተልዕኮ ያበረታታል።
ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቱ ቤተ ክርስቲያን ለወጣቶች ያላትን አሳቢነት ይገልፃል። በዓለም ፈተናዎች መካከል ያላቸውን ንቁ ተሳትፎአቸውን ያስተዋውቃል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ትብብርን በማጎልበት የድርጅት ስብሰባዎችን ለማበረታታት በወጣቶች ሐዋርያዊ አገልግሎት መስክ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን ተነሳሽነት ይደግፋል። በጳጳሳት ጉባኤዎች፣ ለዓለም አቀፍ የወጣት ማኅበራት እና እንቅስቃሴዎች ድጋፍ በመስጠት ላይ ይገኛል።
የሴቶችን እና የወንዶችን ማንነት እና ተልእኮ በቤተ ክርስቲያን እና በኅብረተሰብ ውስጥ በማንፀባረቅ፣ ተሳትፎአቸውን በማሳደግ፣ ባህሪያቸውን በመገምገም እና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለሴቶች የመሪነት ሚና ሞዴሎችን በማዳበር የበኩሉን አስተዋፅዖ ያደርጋል።
ለቤተ ክርስቲያን ሕይወት እና ተልዕኮ የጋራ ሃላፊነት ስሜትን ለማሳደግ በምስጢረ ጥምቀት አማካኝነት በምእመናን እና በተሾሙ አገልጋዮች መካከል ያለውን ትብብር የተመለከቱ ጉዳዮችን ያጠናል። ሥራው በልዩ የቤተ ክርስቲያን ፍላጎቶች መሠረት ለምእመናን በአደራ የሚሰጣቸውን አዳዲስ የአገልግሎት መሥሪያ ቤቶችን እና የቤተ ክህነት ጽ/ቤቶችን በሚመለከት ከጳጳሳት ጉባኤዎች የሚቀርብለትን ሃሳብ መገምገም እና ማጽደቅ ነው።
ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቱ የቤተ ክርስቲያን እንቅስቃሴዎች እና ማኅበራት ሕይወት እና ዕድገት ይከታተላል። የቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤት ብቃት እንደተጠበቀ ሆኖ በሕግ ቀኖና በተደነገገው መሠረት ዓለም አቀፋዊ ባህሪ ላላቸው ማኅበራት እውቅናን ይሰጣል ወይም ያቋቁማል፣ ደንቦቻቸውንም ያጸድቃል። ከምእመናን ሕይወት እና ሐዋርያዊነት ጋር የተያያዙ ማንኛውንም አቤቱታዎች ይመለከታል።
ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቱ በቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ መሠረት የጋብቻን እና የቤተሰብ ሐዋርያዊ እንክብካቤን ያበረታታል። በቤተ ክርስቲያን፣ በኅብረተሰብ፣ በኢኮኖሚ እና በፖለቲካው ዓለም ውስጥ የትዳር ጓደኞች እና የቤተሰብ መብቶች እና ግዴታዎች እውቅናን እንዲያገኙ ይሠራል። ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችን እና ዝግጅቶችን ያስተዋውቃል። ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቱ ከወንጌል አከልግሎት፣ ከባህል እና ከትምህርት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች ጋር በመተባበር እምነትን በቤተሰብ ውስጥ ለማስተላለፍ ሞዴሎችን ማዘጋጀት እና ማሰራጨት ይደግፋል። እንዲሁም ወላጆች በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ውስጥ እምነታቸውን በተጨባጭ እንዲኖሩ ያበረታታል። በባለሙያዎች ድጋፍ በትዳር እና በቤተሰብ ውስጥ የሚከሰቱ ቀውሶችን ያጠናል፣ ይመረምራል። በተጨማሪም ለተፋቱት እና እንደገና ለተጋቡት የሚቀርብ የሐዋርያዊ እንክብካቤ ሞዴሎችን ይሰበስባል፣ ያቀርባል።
ከተለያዩ የስነ-መለኮት ትምህርቶች እና ሌሎች ተዛማጅ ሳይንሶች ጋር በመወያየት የባዮሜዲሲን እና የሰውን ሕይወት የሚመለከቱ የሕግ ችግሮችን ያጠናል። ከእምነት አስተምህሮ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ጋር በመተባበር የሰውን ልጅ ሕይወት እና የዘርን እውነታ የሚመለከቱ ንድፈ ሐሳቦችን ይመረምራል። ከጳጳሳዊ የሕይወት አካዳሚ እና ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የጋብቻ እና የቤተሰብ ሳይንሶች ሥነ-መለኮታዊ ተቋም ጋር ይተባበራል።
ለወንጌል ስብከት አብሮ መጓዝ
ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ የምእመናን፣ የቤተሰብ እና የሕይወት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በየካቲት ወር 2023 ዓ. ም. ባዘጋጀው ጉባኤ ላይ ለተገኙት አባላት ባደረጉት ንግግር፥ “ይህን አስደሳች የቤተ ክርስቲያን ራዕይ ሁላችንም በአእምሯችን እና በልባችን ውስጥ እንድንከባከበው እመኛለሁ!” ብለው፥ በተልዕኮ ላይ ያለች ቤተ ክርስቲያን የተጠመቁት በሙሉ በኅብረት ሆነው ወንጌልን ለመስበክ በጋራ የሚጓዙባት ናት” ሲሉ አስረድተዋል።
ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በማከልም፥ “በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እኛን የሚያስተሳስረን መጠመቃችን እና የኢየሱስ ክርስቶስ መሆናችን ነው” ብለው፥ “ቤተ ክርስቲያን የተጠመቁት በሙሉ በእያንዳንዱ የእረኝነት ሕይወት ውስጥ በየቀኑ ተጋግዘው በሚሠሩ ምእመናን እና አባቶች መካከል ወንድማማችነትን የምታሳድግ ናት” ሲሉ ተናግረዋል።