በቅድስት መንበር የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ጽሕፈት ቤት አወቃቀር
በቅድስት መንበር ሥር የሚገኘው የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ጽሕፈት ቤት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን በመወከል ከኢትዮጵያ እስከ መካከለኛው ምሥራቅ፣ ከአውሮፓ እስከ ሕንድ ድረስ በሚዘረጉ አካባቢዎች የሚገኙ የምሥራቅ ካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት ጉዳዮችን የሚከታተል ሲሆን፥ ከተጠቀሱት ክልሎች በተጨማሪ ወጣ ብሎ በመላው ዓለም የሚገኙ ራስ ገዝ “sui iuris” ካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት የዳያስፖራ ማኅበረሰቦችንም የሚያገለግል ነው።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ጽሕፈት ቤት ርዕሥ ሊቃነ ጳጳሳትን በመወከል ሰዎችን ወይም ልዩ ልዩ ጉዳዮችን የሚያካትቱ በራስ ገዝ “sui iuris” አካባቢዎች በሚገኙ በምሥራቅ ካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት ላይ ተጽዕኖን የሚያሳድሩ ጉዳዮችን ይከታተላል። እነዚህ አብያተ ክርስቲያናት ከኢትዮጵያ እስከ መካከለኛው ምሥራቅ፣ ከአውሮፓ እስከ ሕንድ ድረስ ያሉትን ሐዋርያዊ ክልሎችን የሚያጠቃልሉ ሲሆን በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የየራሳቸውን የዲያስፖራ ማኅበረሰቦችንም ያጠቃልላሉ።
የጽሕፈት ቤቱ የወቅቱ ዋና አስተባባሪ ብጹዕ ካርዲናል ክላውዲዮ ጉጄሮቲ ሲሆኑ ጸሐፊቸው ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሚሼል ጃላክ “OAM” ናቸው።
ታሪካዊ ማስታወሻዎች
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ግሬጎሪ 12ኛ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1573 ዓ. ም. የባይዛንታይን ወይም የግሪክ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት አምልኮን የሚከተሉ ካቶሊክ ምዕመናን ሕይወት የመከታተል ኃላፊነት የተጣለበት የምሥራቅ ቤተ ክርስቲያን የአምልኮ ሥርዓት የእምነት ማስፋፊያ ጉባኤን ከእምነት መስፋፊያ ቅዱስ ጉባኤ ጋር ተመሳሳይ ሃላፊነትን በመስጠት “Congregatio de rebus Graecorum” ወይም የግሪክ ቤተ ክርስቲያን ጉዳዮች ጉባኤን አቋቋሙ። ጉባኤው በሌሎች የምሥራቅ ክርስቲያኖች መካከል እምነትን እንዲያስተዋውቅ ኃላፊነት ተሰጥቶታል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮ 11ኛ በእምነት ማስፋፊያ ቅዱስ ጉባኤ ሥር ለሚገኝ የምሥራቅ ሥርዓተ አምልኮ የእምነት ማስፋፊያ ጉባኤ ተመሳሳይ ሃላፊነቶችን በመስጠት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 1862 ዓ. ም. አቋቋሙ።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክቶስ 15ኛ “Dei providentis” ወይም “የእግዚአብሔር ችሮታ” በሚለው የግል ሐዋርያዊ ሥልጣን የምሥራቅ ቤተ ክርስቲያን ጉባኤን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1917 ዓ. ም. አቋቋሙ።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ “ጠቅላላ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር” በሚለው ሐዋርያዊ ደንብ መሠረት ስሙን በመለወጥ የምሥራቃውያን አብያተ ክርስቲያናት ጽሕፈት ቤት በማለት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 1967 አቋቋሙ። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ስሙን እንደገና በመቀየር “ወንጌልን ስበኩ” በሚለው ሐዋርያዊ ደንብ መሠረት የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ጽሕፈት ቤት በሚል ስያሜ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2022 ዓ. ም. አቋቋሙ።
ከተለያዩ የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ሠነዶች መካከል አስደናቂውን የምሥራቅ ካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት ዓለም ለማወቅ የሚከተሉትን ሠነዶች መመልከቱ አስፈላጊ ይሆናል። “Orientalium dignitas” ወይም “የምሥራቃውያን ክብር” የሚለው ሐዋርያዊ መልዕክት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ ሁለተኛ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1895 ዓ. ም. ምሥራቃዊ ወጎች አስፈላጊነትን በመላው ቤተ ክርስቲያን ዘንድ ለማስጠበቅ የፈለጉበት፣ ቅድስት መንበር ማንነታቸውን ለማስጠበቅ ያላትን ፍላጎት አጉልቶ አሳይቷል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1964 ዓ. ም. ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ስለ ምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ያወጣውን አዋጅ ይፋ አደረጉ።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 1990 ዓ. ም. የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ሕገ ቀኖናዎችን ይፋ ካደረጉ በኋላ ከአምስት ዓመታት በኋላ በ “Orientalium dignitas” ወይም “የምሥራቃውያን ክብር” በሚለው ሐዋርያዊ መልዕክት መቶኛ ዓመት መታሰቢያ ላይ “Orientale lumen” ወይም “ምሥራቃዊ ብርሃን” የተባለ ሐዋርያዊ መልዕክት አሳተሙ።
የጽሕፈት ቤቱ የሥራ ብቃት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይፋ ባደረጉት “Praedicate Evangelium” ወይም “ወንጌልን ስበኩ” በተሰኘው ሐዋርያዊ ደንብ ውስጥ እንደተጠቀሰው፥ በቅድስት መንበር ሥር የሚገኘው የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ጽሕፈት ቤት ከኢትዮጵያ እስከ መካከለኛው ምሥራቅ፣ ከአውሮፓ እስከ ሕንድ ድረስ ካሉት ሐዋርያዊ ክልሎች በተጨማሪ በመላው ዓለም የሚገኙ ራስ ገዝ “sui iuris” የምሥራቅ ካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት ጉዳዮችን እና የዳያስፖራ ማኅበረሰቦች ሁኔታን ይከታተላል። (አንቀጽ 82/ 1)
ጽሕፈት ቤቱ በአንቀጽ 84/1 ላይ እንደተጠቀሰው የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናትን በሚመለከቱ ጉዳዮች ሁሉ ለሐዋርያዊ መንበር መቅረብ ያለበትን የአብያተ ክርስቲያናት አወቃቀር እና አደረጃጀት፣ የማስተማር፣ የመቀደስ እና የአስተዳደር ተግባራትን መተግበር እንዲሁም የሰዎችን መብቶች እና ግዴታዎችን በተመለከተ በሁሉም ጉዳዮች ላይ ብቃቱን በተግባር ይገልጻል።
በተጨማሪም በምሥራቅ ቤተ ክርስቲያናት ውስጥ የሚገኙ ጳጳሳት፣ ካኅናት፣ ገዳማውያን እና ገዳማውያት፣ ምዕመናን እና ሐዋርያዊ ሕይወት የሚከተሉ ማኅበራትን እና የካቶሊክ ትምህርትን እንደ ቅደም ተከተላቸው መሠረት የላቲን ሥርዓተ አምልኮን የሚከተሉ ሀገረ ስብከቶችን፣ ብጹዓን ጳጳስትን፣ ካኅናትን፣ ገዳማውያን እና ገዳማውያትን እና ምዕምናንን በሃላፊነት ይከታተላል።
ጽሕፈት ቤቱ “ዳያስፖራ” በመባል በሚታወቀው የላቲን ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ ክልል ውስጥ የሚገኙትን የምሥራቅ ቤተ ክርስቲያን ምዕምናንን በቅርበት ከመከታተል በተጨማሪ የምዕመናን ብዛት በሚጠይቀው መሠረት በሐዋርያዊ ክልል ውስጥ ልዩ ልዩ አብያተ ክርስቲያናትን የማቋቋም ኃላፊነት ያለበትን ጽሕፈት ቤት ካማከረ በኋላ መንፈሳዊ ፍላጎቶቻቸውን በተንከባካቢዎቻቸው ወይም በራሱ የሥልጣን ተዋረድ በኩል ያስፈጽማል።
የምሥራቅ ቤተ ክርስቲያን የአምልኮ ሥርዓቶች ለረጅም ጊዜ በተስፋፉባቸው ክልሎች ውስጥ ሐዋርያዊ አገልግሎት እና ሚስዮናዊ እንቅስቃሴ በላቲን ቤተ ክርስቲያን ምዕምናን በኩል ቢቀርብም በዚህ ጽሕፈት ቤት ላይ ብቻ የሚመራ ነው። ስለዚህ ጽሕፈት ቤቱ በቡልጋሪያ፣ በቆጵሮስ፣ በግብፅ፣ በዮርዳኖስ፣ በግሪክ፣ በኢራቅ፣ በኢራን፣ በእስራኤል፣ በሊባኖስ፣ በፍልስጤም፣ በሶርያ እና በቱርክ ውስጥ በሚገኙ የላቲን ሥርዓተ አምልኮን በሚከተሉ ምዕመናን ሐዋርያዊ ክልል ላይ ስልጣን አለው።
ጽሕፈት ቤቱ ከምሥራቅ ቤተ ክርስቲያን በተለይም ለስልጠና ወደ ሮም የሚመጡ ተማሪዎችን በማበረታታት የምሥራቅ ቤተ ክርስቲያን የክርስትና ሥርዓተ አምልኮ ቅርሶችን የሚጠብቅ እና የሚያስተዋወቅ፣ ልዩ የጥናት ኮሚሽን፣ የቤተ ክኅነት፣ የገዳማውያን እና ገዳማውያት ምስረታ ልዩ ኮሚሽንን ያጠቃልላል።
ለምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት የዕርዳታ ማሰባሰቢያ ኤጀንሲዎች ኅብረት (ROACO) ከተለያዩ የዓለም አገራት የተውጣጡ ኤጀንሲዎችን እና ድርጅቶችን በማሰባሰብ ለምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት በተለያዩ ዘርፎች ማለትም ከአምልኮ ቦታዎች ግንባታ እስከ ነጻ የትምህርት ዕድል፣ ከትምህርታዊ እስከ ማኅበራዊ እና የጤና አጠባበቅ ተቋማት ድረስ የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ የተሠማሩትን ኤጀንሲዎች በማሰባሰብ በፕሬዚዳንትነት የሚመራ ሲሆን ምክትል ጸሐፊም አለው።
በመጨረሻም ይህ ጽሕፈት ቤት ፍቅርን እና የቤተ ክርስቲያንን የጋራ ኃላፊነት በቅድስት ሀገር ላይ የማስተዋወቅ ተግባር ያለው ሲሆን፥ ለዚህም ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደባት ምድር የሚገኙ ካቶሊክ ማኅበረሰቦችን እና ተቋማትን ለመደገፍ ምእመናን መንፈሳዊ እና የቁሳቁስ ዕርዳታ እንዲያደርጉ ግንዛቤን ለማስጨበጥ የሚረዳ መልዕክት ለሁሉም ብጹዓን ጳጳሳት በየዓመቱ ይልካል።
የምሥራቅ ቤተ ክርስቲያን ምስጢራዊ ስሜትን እንደገና መመለስ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ግንቦት 14/2025 ዓ. ም. የኢዮቤልዩ በዓልን ምክንያት በማድረግ ከምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ሐዋርያዊ አባቶች እና ምዕመናን አገልጋዮች ጋር ባደረጉት ውይይት፥ የምሥራቅ ቤተ ክርስቲያን ምስጢራዊ ስሜትን ወደ ነበረበት እንደገና መመለስ አስፈላጊ እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተዋል።
“ቤተ ክርስቲያን ትፈልጋችኋለች” ባሉት መልዕክታቸው፥ “ዛሬ የምሥራቅ ቤተ ክርስቲያን የምታበረክትልን አስተዋፅዖ እጅግ የላቀ ነው” ብለው፥ “በሥርዓተ አምልኮአችሁ ውስጥ ሕያው ሆኖ የሚቀረውን ምስጢራዊ ስሜት፣ የሰውን ልጅ በሙሉ የሚያሳትፍ፣ የመዳንን ውበት የሚዘምር እና ሰብዓዊ ድክመታችንን የሚያቅፍ የእግዚአብሔር ግርማ አስደናቂ ስሜት መልሰን ማግኘት እንፈልጋለን!” ሲሉ ተናግረዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ንግግራቸውን ሲያጠቃልሉ፥ የምሥራቅ ቤተ ክርስቲያን ምስጢራዊ ስሜቶች የእምነት፣ የተስፋ እና የበጎ አድራጎት ምሳሌዎች ሆነው እንደሚቀጥሉ ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፥ ኢየሱስ ክርስቶስ የፍትህ ፀሐይ ሆኖ የወጣባቸውን የምሥራቅ አገራት ወንድሞች እና እህቶች በዓለማችን ውስጥ ብርሃን ሆነው በመገኘታቸው አመስግነው፥ ሐዋርያዊ አባቶች በተለይም በጳጳሳት ሲኖዶስ ውስጥ የወንድማማችነት እና ትክክለኛ የጋራ ኃላፊነት ቦታዎች በመሆን በቅንነት የጋራ መግባባትን እንዲያበረታቱ አደራ ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ሰኔ 26/2025 ዓ. ም. ከምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት የዕርዳታ ማሰባሰቢያ ኤጀንሲዎች ኅብረት (ROACO) አባላት ጋር በተገናኙበት ወቅት በድጋሚ ባቀረቡት ግብዣ፥ “የጥበብ እና የድነት ብርሃን በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሰፊው በማይታወቅባቸው ቦታዎች በደንብ እንዲታወቅ እፈልጋለሁ” ብለው፥ “ጎረቤቶቻችን የሆኑት የምሥራቅ ቤተ ክርስቲያን ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን እንግዳ የሆነ የአምልኮ ሥርዓት ያላቸው ሳይሆኑ ነገር ግን በግዳጅ ምክንያት የተሰደዱ፣ ስለ ቅድስና ባላቸው ስሜት፣ በመከራ የተረጋገጠ ጥልቅ እምነት እና መንፈሳዊነት፣ መለኮታዊ ምስጢራትን የሚያድስ እና ለእግዚአብሔር ያላቸው ጥማት ምዕራቡን ዓለም ዛሬም ቢሆን ሊያረካ የሚችል ነው” ሲሉ ተናግረዋል።