በቫቲካን የባህልና የትምህርት ጉዳዮችን የሚመለከተው የቅድስት መንበር ጽ/ቤት ተልዕኮ እና ተግባር
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
ትምህርት ቤቶች እና የትምህርት አለም በወንጌል መንፈስ መሞላት አለበት። ይህ በቫቲካን የባህልና የትምህርት ጉዳዮችን የሚመለከተው የቅድስት መንበር ጽ/ቤት ተልእኮ ነው፣ በላቲን ቋንቋ "Praedicate Evangelium" (ወንጌልን ስበኩ) በተሰኘው በሐዋርያዊ የመተዳደሪያ ደንብ ላይ እንደተገለጸው፣ “በክርስቲያናዊ አንትሮፖሎጂ (ስነ-ሰብዕ) አውድ ውስጥ የሰዎችን ሰብዓዊ እሴቶች ለማዳበር የሚሠራ፣ የክርስቲያን ደቀ መዝሙርነት ሙሉ በሙሉ እውን እንዲሆን አስተዋጽኦ ያደርጋል" ሲል ገልጿል።
በቫቲካን የባህልና የትምህርት ጉዳዮችን የሚመለከተው የቅድስት መንበር ጽ/ቤት ተልዕኮው በሁለት ዘርፎች ላይ ያተኮረ ነው፣ በባህል እና በትምህርት መካከል ወሳኝ የሆነ ጥምረት እንዲኖር ይሰራል፥ ጽ/ቤቱ የሐዋርያዊ ተግባራት እንቅስቃሴ እና የባህል ቅርሶችን ለማሳደግ የተዘጋጀ የባህል ክፍል እና የትምህርት ጥራትን ከፍ የምያደርግ ክፍል፣ የካቶሊክ ትምህርት ቤቶችን እና የከፍተኛ የትምህርት እና የምርምር ተቋማትን በተመለከተ መሰረታዊ የትምህርት መርሆችን የሚያዘጋጅ እና በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ተዋረዳዊ ትምህርቶችን ለመስጠት ብቁ የሆነ የትምህርት ክፍልን ያቀፈ ነው።
የወቅቱ በቫቲካን የባህልና የትምህርት ጉዳዮችን የሚመለከተው የቅድስት መንበር ጽ/ቤት አስተዳዳሪ ብፁዕ ካርዲናል ሆሴ ቶለንቲኖ ደ ሜንዶንካ ናቸው። ጸሐፊዎቻቸው ደግሞ ጳጳስ ፖል ዴዝሞንድ ቲጌ እና ሊቀ ጳጳስ ካርሎ ማሪያ ፖልቫኒ ናቸው።
ታሪካዊ ማስታወሻዎች
በቫቲካን የባህልና የትምህርት ጉዳዮችን የሚመለከተው የቅድስት መንበር ጽ/ቤት የቀድሞ የካቶሊክ ትምህርት ጉባኤ እና የባህል ጳጳሳዊ ምክር ቤት አንድ ላይ ያሰባስባል።
የካቶሊክ ትምህርት ጉባኤ ጅምር ከመካከለኛው ዘመን ጋር የተያያዘ ነው። እ.አ.አ. በ1588 ዓ.ም በወቅቱ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በነበሩት ስክስቱስ 5ኛ በጣሊያነኛ ቋንቋ " Immensa" (ግዙፍ) በተሰኘው ሐዋርያዊ የመተዳደሪያ ደንብ የሮም ዩኒቨርሲቲን እና ሌሎች ታዋቂ ዩኒቨርሲቲዎችን ጥናት ለመምራት በ1588 ዓ.ም "ያ መለኮታዊ ጥበብ" የተሰኘ ተቋም በሮም ተቋቋመ። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 12ኛ "ያ መለኮታዊ ጥበብ" በሚል አርዕስት ይፋ ባደረጉት ሐዋርያዊ ሕገ ደንብ የቅድስት መንበር የትምህርት ተቋማትን የሚመለከት ደንብ ይፋ ሆነ።
የጳጳሳዊ የባህል ምክር ቤት መነሻ ከሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ጀምሮ ነው፣ እሱም ከብዙ አጽንዖቶቹ መካከል፣ ዛሬም አስፈላጊ የሆነውን ጠቃሚነት ጠቁሟል፡ የባህል መሠረታዊ ጠቀሜታ ለሰው ልጅ ሙሉ እድገት ጠቃሚ እንደሆነም ተገልጿል።
ባህል
የባህል ክፍል በቅድስት መንበር እና በባህል ዓለም መካከል ያለውን ግንኙነት ያበረታታል እና ይደግፋል።
የተለያዩ ባህሎች ለወንጌል ይበልጥ ክፍት እንዲሆኑ እንዲሁም የክርስትና እምነት ለእነሱ ክፍት እንዲሆን እና የሥነ ጥበብ ፣ ሥነ ጽሑፍ ፣ ሳይንስ ፣ ቴክኖሎጂ እና ስፖርት ወዳጆች በእውነተኛ አገልግሎት እና በመልካም አገልግሎት ውስጥ ያሉ ሰዎች በቤተክርስቲያን ዘንድ እውቅና እንዲያገኙ፣ ውይይት እንደ አስፈላጊ የመገናኛ ፣ የእርስ በእርስ መስተጋብር መፍጠሪያ እና ማበልፀጊያ መሳሪያ በመሆን በውይይት ምርጫ ላይ ምላሽ ይሰጣል ።
የባህል ክፍል የቤተ ክህነት እውነታዎች ታሪካዊ፣ ጥበባዊ እና ባህላዊ ቅርሶች ጥበቃ፣ እና ህዝባዊ ጥቅም እና የአካባቢ ባህሎች መሻሻል እና ጥበቃን ይደግፋል።
በአማኞች እና በኢአማኒያን መካከል የተመረጡ በነገረ መለኮት እና ሰብአዊ ሳይንስ ውስጥ ግንባር ቀደም ዓለም አቀፍ ባለሙያዎችን ያካተተ የጳጳሳዊ አካዳሚዎች እንቅስቃሴዎችን ያስተባብራል።
ትምህርት
የትምህርት ክፍል የካቶሊክ ትምህርት መሰረታዊ መርሆችን፣ የትምህርት ቤቶችን እና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን የካቶሊክ ማንነትን እና የካቶሊክ ሃይማኖትን በየደረጃው በሚገኙ ትምህርት ቤቶች እንዲተገብሩ ያበረታታል፣ እንዲሁም የካቶሊክ እምነትን በአስተምህሮ ውስጥ ያለውን ታማኝነት ይጠብቃል።
በተጨማሪም የካቶሊክ እና የቤተ ክህነት ትምህርት ቤቶች እና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና ማኅበሮቻቸው በክርስቲያናዊ እውነት መሠረት የቅዱሳን ትምህርቶችን ፣ሰብአዊ እና ሳይንሳዊ ጥናቶችን ማቋቋም እና ትብብርን ይደግፋል ፣ ይቆጣጠራል።
የትምህርት ክፍሉ የሃይማኖት አባቶች፣ የተቀደሰ ሕይወት ተቋም አባላት እና ሐዋርያዊ ሕይወት ማኅበራት አባላት እና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለአገልግሎት የሚዘጋጁ ምእመናን አካዳሚያዊ ምስረታ ኃላፊነት አለበት።
በቅድስት መንበር ስም የተሰጡ የትምህርት ማረጋገጫ ድግሪዎችን ግዛቶች እውቅና እንዲሰጡ እና መምህራን የነገረ መለኮት ትምህርቶችን እንዲያስተምሩ የሚያስችለውን ፈቃድ የመስጠት አስፈላጊ ቅደመ ሁኔታዎችን የማዘጋጀት ኃላፊነት አለበት።
በሥፍራዎች እና በፕሮጀክቶች መካከል
በባህላዊ እና ትምህርታዊ መስኮች ፣ በቫቲካን የባህልና የትምህርት ጉዳዮችን የሚመለከተው የቅድስት መንበር ጽ/ቤት በዓለም አቀፍ አካላት እና ዝግጅቶች ላይ በመሳተፍ እና ልዩ ኮንፈረንስ በማደራጀት በሚመለከታቸው ብሄራዊ እና የበላይ ተቋማት የተከናወኑ የድርጊት መርሃ ግብሮችን ይከተላል ።
በቫቲካን የባህልና የትምህርት ጉዳዮችን የሚመለከተው የቅድስት መንበር ጽ/ቤት ተልእኮ የቅድስት መንበር እንደ "ቬኒስ ቢያናሌ" ባሉ ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽኖች ላይ ልዩ ቦታዎች መገኘቱን ማረጋገጥን ያካትታል።
በቫቲካን የባህልና የትምህርት ጉዳዮችን የሚመለከተው የቅድስት መንበር ጽ/ቤት የተለያዩ ፕሮጀክቶችን የማስተዋወቅ ኃላፊነት አለበት። “Global compact on Education" (በትምህርት ላይ ዓለም አቀፍ ጽኑ አቋም) በተለይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በትምህርት እና በባህል መስክ በሚሰሩት ሁሉ መካከል ያለውን ትብብር ለማሳደግ ዓላማው ዓለምን በትምህርት፣ በሥነ ጥበብ፣ በመዝናኛ፣ በስፖርት ወ.ዘ.ተ በመለወጥ አንድ ግብ በማሰብ ሁሉም ሰው በተለይም ወጣት ትውልዶችን በሁለንተናዊ ወንድማማችነት ለማስተማር ነው።
ስለዚህ በቫቲካን የባህልና የትምህርት ጉዳዮችን የሚመለከተው የቅድስት መንበር ጽ/ቤት የዚህ "ሁለት ዓይኖች" ናቸው። ቤተክርስቲያን አለምን የምታይባቸው ሁለት መሰረታዊ ሌንሶች ወይም መነጽሮች ናቸው።