የቅድስት መንበር መገናኛዎች ጽሕፈት ቤት አወቃቀር
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከጽሕፈት ቤቱ ሠራተኞች ጋር ጥቅምት 21/2017 ዓ. ም. ተገናኝተው ባሰሙት የመጨረሻ ንግግር፥ “የቅድስት መንበር መገናኛዎች ብዙዎች መከፋፈልን በሚቀሰቅሱበት፣ የአመለካከት ድግዳዎችን በሚገነቡበት እና ግድየለሽነትን በመረጡበት ወቅት በዘመናችን በሚታዩ አሳዛኝ ድራማዎች መካከል የመገናኛ ድልድዮችን ለመሥራት እና ኅብረት ለመፍጠር ጥረት እያደረገ የሚገኝ ጽሕፈት ቤት ነው” ማለታቸው ይታወሳል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያንን ለመምራት መመረጣቸውን ተከትሎ ከቫቲካን መገናኛዎች አባላት ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ተገናኝተው ባደረጉት ንግግር፥ ጽሕፈት ቤቱ ማንኛውምን ዓይነት ቅራኔን የማይፈልግ፣ ራሱን በአስከፊ ቃላት የማይጋርድ፣ የውድድር ሞዴል የማይከተል እና እውነትን በትሕትና ለማግኘት በሚፈልግ ፍቅር ላይ የተገነባ ግንኙነት ማድረግን እንዲቀጥል መጋበዛቸው ይታወሳል።
በኋላም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ የቫቲካን ሬዲዮ ማሰራጫ ማዕከልን ሳንታ ማርያ ዲ ጋሌሪያ በጎበኙበት ወቅት በላቲን አሜሪካ እና በአፍሪካ ያደረጉትን የሚስዮናዊነት አገልግሎት በማስታወስ፥ የቫቲካን ሬዲዮ አጭር ሞገድ ስርጭቶችን ሌሎች ጣቢያዎችን መድረስ በማይቻልባቸው አካባቢዎች በቀላሉ ማግኘት “በዋጋ ሊተመን የማይችል” በማለት የመገናኛ ሚስዮናዊ ጠቀሜታን በድጋሚ አረጋግጠዋል ።
እነዚህ የአሁኑ ሥራ መሠረቶች ከቅድስት መንበር መገናኛ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ እና ከዋና ጸሐፊው ሞንሲኞር ሉሲዮ ሩዪዝ የተገኙ መሆናቸው ታውቋል።
ታሪካዊ ማስታወሻዎች
የአሁኑ የቅድስት መንበር መገናኛ ጽሕፈት ቤት ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስ ፍራንችስኮስ በግል ሐዋርያዊ ስልጣናቸው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በሰኔ 27/2015 ዓ. ም. በአዲስ መልክ እንደገና በማደራጀት እንዲደራጅ በማድረግ ለቅድስት መንበር መገናኛዎች በአደራ የሰጡት ነው።
ጽሕፈት ቤት ከዚህ ቀደም ተለያይተው የሚገኙ የመገናኛ ዘርፎችን ማለትም የማኅበራዊ መገናኛ ጳጳሳዊ ምክር ቤትን፣ የቅድስት መንበር ኅትመት ቢሮን፣ የቫቲካን መግለጫ ክፍልን፣ የፎቶግራፍ አገልግሎትን፣ “ሎዜቫቶሬ ሮማኖ” የተሰኘ የቅድስት መንበር ዕለታ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍልን፣ የቫቲካን ማተሚያ ቤትን፣ የቫቲካን ሬዲዮን፣ የቫቲካን ቴሌቪዥን ማዕከልን እና የቫቲካን የኢንተርኔት አገልግሎት ማዕከልን ቀስ በቀስ አንድ ላይ በማድረግ በሮማን ኩሪያ ውስጥ ያካተተ ነው።
አንጋፋው የቫቲካን መግለጫ ቢሮ በቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሲስቶስ አምስተኛ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በሚያዝያ 27/1587 ዓ. ም. “የቫቲካን ማተሚያ ቤት” በመባል መቋቋሙ ይታወሳል። “ሎዜቫቶሬ ሮማኖ” በመባል በጣሊያንኛ የሚታተመው የቅድስት መንበር ዕለታዊ ጋዜጣ ለመጀመሪያ ጊዜ የታተመው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በሐምሌ 1/1861 ዓ. ም. ሲሆን፥ በተለያዩ ወርሃዊ እትሞችም በሌሎች ዋና ዋና የወቅቱ ቋንቋዎች ይታተም እንደ ነበር ይታወሳል።
የቅድስት መንበር የሕትመት ክፍል የሆነው የቫቲካን ማተሚያ ቤት (LEV) እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1926 ዓ. ም. ተመሠረተ። ካርዲናል ማተሚያ ቤቱ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን ጽሑፎች እንዲያትም በወቅቱ የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ በበሩት በብጹዕ ካርዲናል አንጄሎ ሶዳኖ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ግንቦት 31/2005 ዓ. ም. ልዩ የቅጂ መብት ተሰጠው።
የቫቲካን ሬድዮ፥ የስርጭት ጣቢያ በመሆን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በየካቲት 12/1931 ዓ. ም. በቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 11ኛ ተመርቆ ተከፈተ። በተሐድሶ ለውጥ ተደርጎበት በመልቲሚዲያ አቀራረብ ወደ ጋዜጠኝነት ሥራ ተቀይሮ ወቅታዊ መረጃዎችን በበይነ-መረብ ላይ በመጫን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከታህሳስ 2017 ዓ. ም. ጀምሮ የቫቲካን ዜናዎችን በዋና ዋና የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይ ማቅረብ ጀመረ።
የቅድስት መንበር መግለጫ ጽ/ቤት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ1939 ዓ. ም. ጀምሮ ስለ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት እና ስለ ሐዋርያዊ መንበር የተለያዩ ተግባራት የሚናገሩ መግለጫዎችን በይፋ ማሰራጨት ጀመረ። አስቀድሞ ከ “ሎዜቫቶሬ ሮማኖ” ዕለታዊ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ጋር የነበረው የመግለጫ ጽ/ቤቱ ራሱን እንደ “ልዩ የፕሬስ ቢሮ” በማቋቋም በሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ (1962-1965) ወቅት ራሱን ችሎ ተቋቋመ።
የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮ 12ኛ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ጥር 30/1948 ዓ. ም. ሃይማኖታዊ በሆኑ ሥነ-ምግባር ጉዳዮች ላይ የፊልሞች ጥናት እና የቤተ ክርስቲያን ግምገማ ጳጳሳዊ ኮሚሽን አቋቋሙ። የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ 23ኛ “መልካም እረኛ” በማለት ይፋ ባደረጉት የግል ሥልጣን መሠረት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 1959 ዓ. ም. ከቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤትነት ወደ ቅድስት መንበር ቋሚ ቢሮ ለወጡት።
ከዚያም የቀድሞው ር ዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ ስድስተኛ እንደ ጳጳሳዊ የማኅበራዊ መገናኛ ኮሚሽን በድጋሚ በማዋቀር የሲኒማ፣ የሬዲዮ፣ የቴሌቭዥን እና ወቅታዊ እና ዕለታዊ የሕትመት ሥራዎችን በር ዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት አስተምህሮ አንጻር የመከታተል እና የመገምገም ሃላፊነትን ከሰጡት በኋላ ቀጥለውም ወደ ጳጳሳዊ የማኅበራዊ መገናኛ ምክር ቤት ከፍ በማድረግ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 1971 ዓ. ም. ከታተመው “Communio et progressio” ወይም “አንድነት እና ዕድገት” በሚለው ሐዋርያዊ መመሪያ ላይ “Aetatis novae” ወይም “አዲሱ ዘመን” የሚለው ሐዋርያዊ መመሪያ ታክሎበት ዓለም አቀፍ የመገናኛ ቀን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 1967 ዓ. ም. መከበር ተጀመረ።
የቫቲካን ቴሌቭዥን ማዕከል (ሲቲቪ) የተቋቋመው በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1983 ዓ. ም. ሲሆን፥ ዓላማውም የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን ሐዋርያዊ አገልግሎቶች እና የሐዋርያዊ መንበርን እንቅስቃሴ በቴሌቪዥን ምስሎች ለመመዝገብ ነው። ከ1984 ጀምሮ የተቀረጸ እያንዳንዱ ቅጂ፣ ፕሮግራም ወይም ዘጋቢ ፊልም ለማኅደር ጥበቃ ምቹ በሆኑ ክፍሎች ውስጥ ተሰንዶ ይገኛል። የቅድስት መንበር መገናኛዎች ጽሕፈት ቤት ከተቋቋመ በኋላ የካቶሊክ ቴሌቪዥን ምርቶች በሙሉ አሁን በቫቲካን ሚዲያ ሥር ይገኛሉ።
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2006 ዓ. ም. የተቋቋመው፥ ፎቶግራፍ አንሺዎችን፣ ቤተ መዛግብትን እና ቴክኒሻኖችን ያቀፈው የሎዜርቫቶሬ ሮማኖ የፎቶግራፍ አገልግሎትም እንዲሁ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን እና የቅድስት መንበርን እንቅስቃሴ በፎቶግራፍ የሚዘግብ ነው። የአገልግሎቱ ዲጂታል ክፍል ለአታሚዎች እና ጋዜጦች እንዲሁም ለግለሰቦች አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል።
በመጨረሻም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በታኅሳስ 25/1995 ዓ. ም. የቫቲካን የኢንተርኔት አገልግሎት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የብርሃነ ልደት መልዕክት በማካተት እና በበይነ-መረብ ላይ በማተም በወቅቱ አዲስ የተፈጠረ www.vatcan.va የተሰኘ ድህረ-ገጽ ተከፈተ። ዛሬ የቴክኒክ እና የሠነድ-ግራፊክ ክፍል ሠራተኞች የቅድስት መንበር መገናኛዎች ጽሕፈት ቤት አካል ናቸው።
የብቃት መመዘኛዎች
የቅድስት መንበር መገናኛዎች ጽሕፈት ቤት Praedicate Evangelium” ወይም “ወንጌልን ስበኩ” በበሚለው በሐዋርያዊ ደንብ ውስጥ እንደተገለጸው፥ በጠቅላላው የሐዋርያዊ መንበር መገናኛ ሥርዓት ኃላፊነት ያለው እና በሁሉም የቅድስት መንበር መገናኛዎች መስክ ውስጥ የሚገኙትን አካላት አንድ የሚያደርግ በመሆኑ መላው ሥርዓት ለቤተ ክርስቲያን የወንጌል አገልግሎት ፍላጎት፣ በዲጂታል ሚዲያ እና ልማት መስተጋብር በሚገለጽበት አውድ ውስጥ ወጥ በሆነ መልኩ ምላሽ እንዲሰጥ ነው።
ይህንን ለማድረግ በአሁኑ ጊዜ ያሉትን እና ወደፊት ሊዳብሩ የሚችሉ የምርት ሞዴሎችን፣ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችን እና የመገናኛ ዘዴዎችን ይጠቀማል። ከተጨባጭ ተግባሮቹ በተጨማር የቤተ ክርስቲያኗን የግንኙነት ተግባራት ሥነ-መለኮታዊ እና ሐዋርያዊ ጉዳዮችን ይመረምራል፣ ያዳብራል። ከዚህ አንፃር ተግባቦቱ ወደ ቴክኖሎጂያዊ የመሣሪያ ፅንሰ-ሃሳቦች ደረጃ እንዳይወርድ የትምህርት ደረጃን ጨምሮ ይሠራል።
የቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ ተልዕኮ ለሥልጣኔ እና ለሥነ-ምግባር መሻሻል፥ አገልግሎት በርካታ የመገናኛ ዘዴዎች እንዲኖሩት እና ምእመናንም ጭምር ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ከማድረግ በተጨማሪ በተለይም ዓለም አቀፍ የመገናኛ ቀንን ምክንያት በማድረግ ይሠራል።
የቅድስት መንበር መገናኛ ጽ/ቤት ሥራውን በቅድስት መንበር በተደነገገው ልዩ ሕግ እና ዓለም አቀፍ ቃል ኪዳን መሠረት በቫቲካን ግዛት ውስጥ የሚገኝ የመገናኛ እና የኔትወርክ መሠረተ ልማትን ይጠቀማል። የቅድስት መንበር መገናኛ ጽ/ቤት ከቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤት ጋር በመተባበር የሚሠራ ሲሆን ሌሎች ከሮማ ከፍተኛ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች፣ ከቅድስት መንበር እና ከቫቲካን ከተማ አስተዳደር ጠቅላይ አስተዳደር ጋር ግንኙነት ያላቸው ቢሮዎችን እና ተቋማትን በመገናኛው ዘርፍ ይደግፋቸዋል።
ለበለጠ መረጃ የመገናኛ ጽሕፈት ቤት ድረ-ገጽ ይመልከቱ!