200 ምስጢረ ንስሐ የምያስገቡ አናዛዦች በሮም ለሚከናወነው የንስሐ ቀን ዝግጁ መሆናቸው ተገልጿል
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
ለዲጂታል ሚሲዮናውያን እና የካቶሊክ ተጽእኖ ፈጣሪዎች ኢዩቤሊዩ በወጣው የድርጊት መርሐግብር መሰረት ከባለፈው ሰኞ ሐምሌ 21/2017 ጀምሮ በመከናወን ላይ የሚገኘው ዝግጅት የአቀባበል ሥነ-ሥርዓት ተደጎ በይፋ የተጀመረ ሲሆን ማክሰኞ ሐምሌ 22/2017 ዓ.ም የመክፈቻ መስዋዕተ ቅዳሴ (በቫቲካን፣ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ) መከናወኑ ይታወሳል፣ ረቡዕ ሐምሌ 23/2017 ዓ.ም እና ሐሙስ ሐምሌ 24/2017 ዓ.ም በሮም ከተማው ባህላዊ፣ ጥበባዊ እና መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችን የማከናወን እና የመጎብኘት ሥነ-ሥርዓት ተከናውኗል። አርብ ሐምሌ 25/2017 ከረፋዱ ጀመሮ እስከ ምሽት 1 ሰዓት ድረስ የሕሊና ምርመራ እና ምስጢረ ንስሐ የሚደረግበት ክፍለ ጊዜ በሁኑ ወቅት በመካሄድ ላይ ይገኛል፣ ቅዳሜ ሐምሌ 26/2017 ዓ.ም አመሻሹ ላይ የመዝናኛ፣ የመተዋወቂያ፣ የመንፈሳዊ መዝሙሮች ዝግጅት እና የመንፈሳዊ ሕይወት ምስክርነቶች ይሰጣሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን በኢትዮጲያ የሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 3፡30 - 4፡30 ድረስ ከቅዱስ አባታችን ጋር የምሽት ዝግጅቶች ይከናወናል፣ ስፍራው በሮም ከተማ ዳርቻ ላይ በሚገኘው ቶር ቬርጋታ በመባል በሚታወቅ ሰፊ ስፍራ ላይ መሆኑም ተገልጿል። እሁድ ሐምሌ 27/2017 ዓ.ም በኢትዮጲያ የሰዓት አቆጣጠር ከረፋዱ 4፡30 ላይ በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የሚመራ መስዋዕተ ቅዳሴ በቶር ቬርጋታ ይከናወናል። በዚህ የዲጂታል ሚሲዮናውያን እና የካቶሊክ ተጽእኖ ፈጣሪዎች የኢዩቤሊዩ ላይ ለመሳተፍ ከ146 አገራት የተውጣጡ ከ500 ሺ በላይ ወጣቶች እየተሳተፉ እንደሚገኝ ተዘግቧል።
ለዐርብ ሐምሌ 25/2017 ዓ.ም የዲጂታል ሚሲዮናውያን እና የካቶሊክ ተጽእኖ ፈጣሪዎች የኢዩቤሊዩ በወጣው የድርጊት መርሐግብር መሰረት በኢትዮጲያ የሰዓት አቆጣጠር ከረፋዱ 5፡30 እስከ ምሽቱ 1 ሰዓት ድረስ በሮም ከተማ ውስጥ በሚገኘው የጥንቱ ሮማውያን መድረክ በሆነው ቺርኩስ ማክሲሙስ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ የሂልና ምርመራ እና የምስጢረ ንስሐ ሥርዓተ አምልኮ እየተከናወነ እንደሚገኝ የተገለጸ ሲሆን ምስጢረ ንስሐ የምያስፈጽሙ 200 የምያህሉ አናዛዢ ቀሳውስት መሰናዳታቸውም ተገልጿል። ለዚህ መንፈሳዊ ሥርዓተ አምልኮ የሚውሉ ከ10 ሺ በላይ የሚሆኑ መጽሐፍት በዱካት ፋውንዴሽን ተዘጋጅተው መቀረባቸው ተገልጿል።
ለኢዮቤልዩ ወደ ሮም ለመጡ በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ወጣት ምዕመናን አርብ የሕሊና ምርመራ እና የምስጢረ ንስሐ ሥርዓተ አምልኮ በመከናወን ላይ እንደሚገኝ ቀደም ሲል መግለጻችን የሚታወስ ሲሆን ከዚያን በመቀጠል፣ ቅዳሜ እና እሁድ ቀን ወጣቶቹ በቶር ቬርጋታ ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ጋር እንደ ሚገናኙ ይጠበቃል።
በተለያዩ ቋንቋዎች ምስጢረ ንስሐ የሚደረግባቸው ጣቢያዎች
ጣልያንኛ፣ ስፓኒሽ፣ እንግሊዘኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ ፖርቱጋልኛ እና ፖላንድኛ የሚናገሩ የዲጂታል ሚሲዮናውያን እና የካቶሊክ ተጽእኖ ፈጣሪዎች የኢዩቤሊዩ መንፈሳዊ ተጓዦች ቀኑን ሙሉ በራሳቸው ቋንቋ የኑዛዜ ጣቢያዎችን ያገኛሉ። ለጀርመን፣ ሃንጋሪ፣ ስሎቫክ፣ ኮሪያኛ እና ቻይንኛ ተናጋሪዎች ጣቢያዎች በተመደበው ጊዜ ይገኛሉ።
የዱካት ፋውንዴሽን መጽሃፍትን በሥርዓተ አምልኮ ወቅት አሰራጭቷል
በ"የንስሐ ቀን" ከዱካት ፋውንዴሽን የመጡ ሃያ በጎ ፈቃደኞች 10,000 የዱካት መጽሐፍ ለምስጢረ ንስሐ ዝግጅት ይሆን ዘንድ አሰራጭተዋል። ለወጣቶች ኢዮቤልዩ የታተመው ይህ ልዩ እትም በአራት ቋንቋዎች ማለትም በጣሊያንኛ፣ በእንግሊዝኛ፣ በፈረንሳይኛ እና በጀርመን ተጽፎ ይገኛል።
ለመጀመሪያ ጊዜ የታተመው እ.ኤ.አ. በ 2014 ዓ.ም ሲሆን አሁን እየተካሄደ ለሚገኘው የዲጂታል ሚሲዮናውያን እና የካቶሊክ ተጽእኖ ፈጣሪዎች የኢዩቤሊዩ ዝግጅት ይሆን ዘንድ የተሻሻለው መጽሐፉ ለወጣቶች ተደራሽ የሆነ የምስጢረ ንስሐ ሥርዓተ አምልኮ አገባብ አስተምህሮ ለመስጠት ያለመ ነው። አዲሱ እትም ሕሊናን መመርመርን፣ የኑዛዜን ትርጉም ማብራራት እና አንዳንድ ጠቃሚ ጸሎቶችን ያካትታል።