MAP

ዲጂታል ሚሲዮናውያን በስብሰባቸው መዝጊያ ላይ ዲጂታል ሚሲዮናውያን በስብሰባቸው መዝጊያ ላይ  

ቤተ ክርስቲያን የመጀመሪያውን የኢዮቤልዩ በዓል ለካቶሊክ ተጽእኖ ፈጣሪዎች ማዘጋጀቷ ተገለጸ

ሮም በሺዎች የሚቆጠሩ የዲጂታል ሚሲዮናውያን ከሐምሌ 21 እስከ 22/2017 ዓ. ም. የሚያደርጉትን አስደናቂ የጸሎት፣ የስልጠና እና የወንድማማችነት ስብሰባን ለማስተናገድ በመዘጋጀት ላይ እንደምትገኝ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ የዲጂታል ዘርፍን እንደ እውነተኛ የተልዕኮ መስክ በመገንዘብ በተለይ ለዲጂታል ሚስዮናውያን እና ለካቶሊክ ተፅእኖ ፈጣሪዎች በተሰጠ የቅዱስ ዓመት የኢዮቤልዩ በዓልን ታከብራለች።

ስብሰባው የሚካሄደው በሮም ከሐምሌ 21 እስከ 22/2017 ዓ. ም. ሲሆን ይህም ከወጣቶች ኢዮቤልዩ የመክፈቻ ቀናት ጋር ተያይዞ እንደሆነ ታውቋል። በማህበራዊ ሚዲያ ወንጌልን የሚሰብኩ ብዙ ወጣቶች በሁለቱም በዓላት ላይ ንቁ ተሳትፎ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

በቫቲካን የቅድስት መንበር ኮሙኒኬሽን ጽሕፈት ቤት አስተባባሪነት የተዘጋጀው ይህ በዓል ከዚህ በፊት ታይቶ የማያውቅ፥ ከላቲን አሜሪካ፣ ከካሪቢያን እና ከስፔን ጠንካራ ውክልና ያለው ወደ አንድ ሺህ የሚጠጉ ዲጂታል ሚሲዮናውያንን ከዓለም ዙሪያ የሚያሰባስብ እንደሆነ ታውቋል።

እነዚህ ወንጌላውያን የወንጌልን ደስታን በማኅበራዊ ሚዲያ፣ በቪዲዮ መድረኮች፣ በብሎጎች እና በልዩ ልዩ መተግበሪያዎች አማካይነት በማሰራጨት በዲጂታሉ ዓለም ውስጥ ተደራሽነት ያለውን የፈጠራ እና ክርስቲያናዊ ምሥክርነት ይሰጣሉ።

ወደ ሮም ለመጓዝ ለማይችሉት ሰዎች ትይዩ የሆኑ ምናባዊ ዝግጅቶችን በኦፊሴላዊው ድህረ ገጽ www.digitalismissio.org በመመዝገብ መከታተል እንደሚችሉ እና ይህም በሌሎች የአካባቢያቸው የተልዕኮ አውዶች ውስጥ መሳተፍ እንደሚያስችላቸው ታውቋል።

በአካል ቀርቦ መመዝገብ ሲያበቃ የበዓሉ ተሳታፊዎች አሁንም በመስመር ላይ እንዲቀላቀሉ እንደሚደረግ እና የኢዮቤልዩ ዋና ዋና ሁለት ክፍለ ጊዜዎች በዩቲዩብ ቻናል አማካይነት በቀጥታ ማግኘት እንደሚችሉ ታውቋል።

ተነሳሽነቱ ነፍስሔር ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሲኖዶሳዊነት ሂደት ወቅት ላቀረቡት ጥሪ ምላሽ ለመስጠት የተዘጋጀ ሲሆን፥ ይህም የምሥራቹን ቃል ወደ ዲጂታሉ ዓለም ማምጣት አስፈላጊ መሆኑን እና ማንም ሰው ከሲኖዶሳዊነት ጉዞ እንዳይገለል ለማድረግ እንደሆነ ተገልጿል።

መንፈሳዊነት፣ ሕንጸት እና ክብረ በዓል

የኢዮቤልዩ መርሃ ግብር ሦስት ዋና ዋና ክፍሎችን የያዘ ሲሆን፥ መንፈሳዊው አካል በቅዱስ በር በኩል ማለፍን የሚመለከት ሲሆን፥ የእያንዳንዱ ቅዱስ ዓመት መለያ እና የውስጥ መታደስ ምልክት እንደሆነ ታውቋል።

በአዳራሹ ውስጥ የሚደረጉ ዋና ዋና ገለጻዎችን፣ ወርክሾፖችን እና ምስክርነቶችን የያዘ የሕንጸት ምዕራፍሎችን የተከተል ሲሆን፥ የእነዚህ ዝግጅቶች ዓላማ የሐዋርያዊ አገልግሎት መሣሪያዎችን ለዲጂታል ተልዕኮ ለማዋል እና የጋራ አስተንትኖ ቦታዎችን ለማበረታታት እንደሆነ ታውቋል።

የመጨረሻው ምዕራፍ የበዓሉ አከባበር ጊዜን የሚመለከት ሲሆን፥ በአደባባይ ላይ የሚቀርቡ የሥነ-ጥበብ ሥራዎችን፣ ሙዚቃን እና የፈጠራ ሥራዎች በዲጂታሉ ዓለም ውስጥ በማስገባት የወንጌል እና የኅብረት ቋንቋዎችን የሚያጎላ ፌስቲቫል እንደሚሆን ታውቋል።

ርኅራኄ ያለው ወንጌል ምስክርነት በዲጂታል መድረክ

ይህ የኢዮቤልዩ በዓል ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ላቀረቡት በዲጂታል ዓለም ውስጥ የደጉ ሳምራዊነት ግብዣ መልስ የሚሰጥ እና ምእመናን በአውታረ መረብ ላይ በርኅራኄ፣ በሰብዓዊነት እና በቅርበት እንዲኖሩ አደራ ማለታቸውን የሚያሳስብ ብቻ ሳይሆን፣ በሐዋርያዊ አገልግሎት በኩል የተስፋ አቀራረብን እንዲማሩ የሚጋብዝ መሆኑ ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ከብዙኃን መገናኛ ባለሙያዎች ጋር ባደረጉት የመጀመሪያ ስብሰባ ላይ፥ መደማመጥ ያለበት ግንኙነት፣ የድምፅ አልባ ሰዎች ድምጽን የሚያጎላ እና በመከፋፈል ወይም በጠላትነት የተፈረጁ ቃላትን የሚያስወግድ የመግባቢያ ዘዴ እንደሚያስፈልግ ደጋግመው መግለጻቸው ይታወሳል።

ኢዮቤልዩ በዓል እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2023 በፖርቱጋል መዲና ሊዝበን ውስጥ በዓለም የወጣቶች ፌስቲቫል የተካሄደውን የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የዲጂታል ወንጌላውያን ስብሰባ ላይ የተገነባ እና ይህ ክስተት ዓለም አቀፍ የሚስዮናውያን ትስስር እንዲፈጠር ምክንያት እንደሆነ እና ተነሳሽነቱ እየተጠናከረ ወደፊትም የሚቀጥል መሆኑ ታውቋል።

ድምጾችን እና ባሕሎችን አንድ የሚያደርግ ዜማ

ከኢዮቤልዩ ዋና ዋና ዝግጅቶች መካከል አንዱ “ሁሉም ሰው” የተሰኘው ኦፊሴላዊ ዜማ ድርሰት ሲሆን፥ ዜማው በዓለም ዙሪያ ያሉ ካቶሊክ አርቲስቶችን አንድ የሚያደርግ የትብብር ውጥን እንደሆነ ታውቋል።

“ሁሉም ሰው” የሚለው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሊዝበን በተካሄደው የዓለም ወጣቶች ቀን፥ “በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለሁሉም ሰው የሚበቃ ቦታ አለ!” ማለታቸውን የሚያረጋግጥ ሲሆን፥ ዜማው ይህን የኢዮቤልዩ በዓል የሚያንቀሳቅስ አካታች፣ ሲኖዶሳዊ እና ሚሲዮናዊ መንፈስ የያዘ እንደሆነ ታውቋል።

“ሁሉም ሰው” የተሰኘው ኦፊሴላዊ ዜማ

 

16 Jul 2025, 16:29