የቅድስት መንበር ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት አወቃቀር
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የቅድስት መንበር ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት በሦስት ዋና ዋና ክፍሎች የተከፋለ ነው። የመጀመሪያው የጠቅላላ ጉዳዮች ክፍል፣ ሁለተኛው የመንግሥታት እና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ግንኙነት ክፍል እና ሦስተኛው የቅድስት መንበር ዲፕሎማሲ ሠራተኞች ክፍል ናቸው። የቅድስት መንበር ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን የሐዋርያዊ መንበር መሪነት ተግባር በማገዝ አገልግሎቱን በሁሉም ዘርፍ የማበርከት ተልዕኮ ተሰጥቶታል። የቅድስት መንበር ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር በቅርበት የሚሠሩ እና በሐዋርያዊ መንበር ውስጥ የሚገኙ ከፍተኛ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶችን እና ተቋማትን የሚያስተባብሩ እና በውጪ አገራትም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን የመወከል ኃላፊነት ያለባቸው የበርካታ አገራት ተወላጆች ስብጥር ነው። የቅድስት መንበር ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ቤተ ክርስቲያንን በማስተዳደር ረገድ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የቅርብ ተባባሪ ሲሆን የጽሕፈት ቤቱ የወቅቱ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን ናቸው።
ታሪካዊ ማስታወሻዎች
የቅድስት መንበር ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት በአሥራ አምስተኛው ክፍለ ዘመን የተመሠረተ ሲሆን፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በታኅሳስ 31/1487 ዓ. ም. በወጣው ሐዋርያዊ ሕግ መሠረት ሃያ አራት ሐዋርያዊ ጽሕፈት ቤቶችን “Secretaria Apostolica” በማቀፍ “Secretarius Domesticus” የሚል ስያሜ ተሰጥቶት የተቋቋመ ጽሕፈት ቤት ነው።
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1814 ዓ. ም. የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ፒዮስ ሰባተኛ ልዩ የቤተ ክርስቲያን ጉዳዮችን የሚከታተል ጉባኤን አቋቋሙ። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ፒዮስ አሥረኛ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ሰኔ 29/1908 ዓ. ም. ሐዋርያዊ ደንብን ተከትሎ የተቋቋመ ‘የጠቢባን ምክር ቤት’ ወይም “Sapienti consilio” የተሰኘ ምክር ቤት ከመሠረቱ በኋላ በሕገ ቀኖና ተሻሽሎ እንደገና እንዲዋቀር አድርገዋል።
የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1988 ዓ. ም. የሮማ ኩሪያን በአዲስ መልክ በማዋቀር እና የቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤትን በሁለት ክፍሎች የሚከፍለውን “” ወይም “መልካም እረኛ” የተሰኘ ሐዋርያዊ ደንብ አጽድቀዋል። በመጨረሻዎቹ ዓመታት ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2022 ዓ. ም. “” ወይም “ወንጌልን ስበኩ” በሚለው ሐዋርያዊ ደንብ መሠረት የተጠናቀቀውን አዲስ የማሻሻያ ሂደት ማስጀመራቸው ይታወሳል።
ጠቅላላ ጉዳይ የሚከታተል ክፍል
በቅድስት መንበር ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ጠቅላላ ጉዳዮችን የሚከታተል ክፍል በተተኪ ሊቀ ጳጳስ በብጹዕ አቡነ ኤድጋር ፔኛ ፓራ የሚመራ ሲሆን የክፍሉ ሃላፊነትም የከፍተኛ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች የዕለት ተዕለት ሥራን መከታተል፣ ዓለም አቀፋዊት ቤተ ክርስቲያንን መንከባከብ እና በቅድስት መንበር ሥር የሚገኙ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች እና ተቁማት መካከል ያለውን ትሥር ያበረታታል።
የጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች ራስ ገዝነትን በማይጎዳ መልኩ የልዩ ልዩ ተቋማት ኃላፊዎች ጉዳዮችን ይከታተላል። የቅድስት መንበር ተወካዮችን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ኃላፊነትን ይወስዳል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በአደራ የሰጡትን ሠነዶች ማርቀቅ እና መላክ፣ የቅድስት መንበር ኦፊሴላዊ መጽሔት ወይም “Acta Apostolicae Sedis” ህትመቶችን መቆጣጠር፣ ስለ ሁለቱም የሮም ጳጳስ ድርጊቶችን እና የቅድስት መንበር እንቅስቃሴ ኦፊሴላዊ ግንኙነቶችን በተመለከተ ለቅድስት መንበር መገናኛዎች መመሪያን ይሰጣል። ይህ ክፍል በሮም ጳጳስ የጸደቁ ሹመቶችን የሚመለከቱ ድርጊቶችን በሙሉ የማስተናገድ እና በዓለም ዙሪያ የምትገኝ ቤተ ክርስቲያንን አስመልክቶ የሚወጡ ስታቲስቲካዊ መረጃዎችን የማስተባበር እና የማተም ሃላፊነት አለበት።
ከመንግሥታት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር ያለው ግንኙነት
በዋና ጸሐፊው በሊቀ ጳጳስ ፖል ሪቻርድ ጋላገር የሚመራው የመንግሥታት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ግንኙነት ክፍል፥ ሲቪል መንግሥታትን የሚያካትቱ ጉዳዮችን የማስተናገድ ሃላፊነት አለበት። ይህ ክፍል የቅድስት መንበር ዲፕሎማሲያዊ እና ፖለቲካዊ ግንኙነት ወይም ከሌሎች ዓለም አቀፍ የሕግ ጉዳዮችን የመከታተል እንዲሁም ቅድስት መንበርን በዓለም አቀፍ ድርጅቶች እና መንግሥታዊ የባለብዙ ወገን ጉባኤዎች የመወከል ሃላፊነት አለበት። ይህ ክፍል ከፍተኛ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ወይም የሮማ ኩሪያ አካል ዓለም አቀፍ ግንኙነቶችን ወይም ከሲቪል ባለስልጣናት ጋር ያለውን ግንኙነት የሚመለከት መግለጫ ወይም ሠነድ ለማዘጋጀት ሲያቅድ ፈቃድ የመስጠት ኃላፊነት አለበት። ከዚህም በተጨማሪም በተለየ ሁኔታ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ስም ብቃት ያላቸውን ከፍተኛ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶችን ካማከረ በኋላ የተወሰኑ አብያተ ክርስቲያናትን በማቅረብ ምሥረታቸውን ወይም ማሻሻያቸውን የሚመለከቱ ጉዳዮችን ሁሉ ይፈጽማል።
የቅድስት መንበር ዲፕሎማቶች
በዋና ጸሐፊው ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሉቺያኖ ሩሶ የሚመራው ቅድስት መንበር ዲፕሎማሲያዊ አገልግሎት ክፍል፥ በተለይ በውስጡ የሚሠሩ ሰዎችን የኑሮ እና የሥራ ሁኔታቸውን እንዲሁም ቀጣይ ሥልጠናቸውን የሚመለከቱ ጉዳዮችን ያስፈጽማል። ለቅድስት መንበር ዲፕሎማሲያዊ አገልግሎት እጩዎችን በመምረጥ እና በማሰልጠን ከጳጳሳዊ ቤተ ክኅነት አካዳሚ ጋር በትብብር ይሠራል። የቅድስት መንበር ዲፕሎማሲያዊ ክፍል በነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በኅዳር 21/2017 ዓ. ም. የተቋቋመ ነው።
የሕዝብ እግዚአብሔር ተግዳሮቶችን እና ተስፋዎችን መጋራት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ለዚህ ጥንታዊ ተቋም አባላት ግንቦት 28/2017 ዓ. ም. ምስጋናን በማቅረብ ባደረጉት ንግግር፥ “ብቻዬን አለመሆኔን በማወቄ እጽናናለሁ፤ በዚህም የጠቅላላ አገልግሎት ኃላፊነቴን ከእናንተ ጋር መካፈል እችላለሁ” ማለታቸው ይታወሳል።
የቅድስት መንበር ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ለቤተ ክርስቲያን ሕይወት ውድ አገልግሎትን የሚያቀርብ ልዩ ልዩ ማኅበረሰብ የሚገኝበት ነው። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በንግግራቸው፥ “በጋራ ሆነን ጥያቄዎችን፣ ችግሮችን፣ ፈተናዎችን እና በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ተስፋዎች እና ተግዳሮቶች እናካፈላለን” ማለታቸው ይታወሳዋል።