MAP

ፕሮፌሰር ጆሴፊና ኢቻቫሪያ ፕሮፌሰር ጆሴፊና ኢቻቫሪያ  

በጦርነት ለተመሰቃቀለው ዓለም የሰላም ማስፈን ሃይማኖታዊ ገጽታዎች

“የሰላም ማስፈን ኃይማኖታዊ ገጽታዎች” በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሚና ላይ እንዲሁም በሌሎች የእምነት ተቋማት እና ሰላም ማስፈን ስራዎች ላይ ትኩረት ለማድረግ በቫቲካን እየተካሄደ ያለው ዓለም አቀፍ ጉባኤ ርዕስ ነው።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

በ3ኛው የዓለም ጦርነት በተናጠች ዓለም ውስጥ ለሁለት ቀናት በቫቲካን የተካሄደው ዓለም አቀፍ ጉባኤ፣ የሃይማኖት ተቋማት ሰላምን በማስፈን ረገድ ያላቸውን ሚና ተዳሷል።

ሐምሌ 3 እና ሐምሌ 4/2017 ዓ.ም ለሁለት ቀናት ያህል እየተካሄደ ያለው ይህ ስብሰባ “የሰላም ማስፈን ሃይማኖታዊ ገጽታዎች” በሚል ርዕስ በጳጳሳዊ የማህበራዊ ሳይንስ አካዳሚ (PASS) በኖትርዳም ዩኒቨርሲቲ እና ከሰላም ምርምር ኢንስቲትዩት ኦስሎ (PRIO) የአለም አቀፍ ጉዳዮች ትምህርት ቤት ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ነው።

ከተናጋሪዎቹ መካከል በኖትር ዴም ዩኒቨርሲቲ የሰላም ስምምነት ድርድር ፕሮጀክት ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ጆሴፊና ኢቻቫሪያ ይገኙበታል። ለቫቲካን ዜና በሰጡት ቃለ መጠይቅ ላይ ሲናገሩ  ዝግጅቱን “በእምነት ላይ የተመሰረቱ እሴቶች እና የሃይማኖት መሪዎች ለሰላም ድርድር እና በጦርነት የተበላሹ ማህበረሰቦችን ለመፈወስ የሚያበረክቱት ሚና እንዴት እንደሆነ ለመዳሰስ አጋጣሚ” እንደሆነ ገልጸዋል።

እምነት እንደ ህጋዊነት እና የእርቅ ምንጭ

ፕሮፌሰር ኢቻቫሪያ እንዳብራሩት የሀይማኖት ተቋማት መሪዎች በተለይ በተቃዋሚዎች መካከል መተማመን ሲጣፋ ወይም መተማመን በሌለበት ሁኔታ ውስጥ ለሰላም ሂደቶች የሞራል ስልጣን እና ህጋዊነት ያመጣሉ ሲሉ ተናግረዋል ።

ኮሎምቢያዊት የሆኑት ኢቻቫርሪያ ግጭት ባለባት ሀገር ውስጥ የመኖር እና የሰላም ሂደት የጀመሩበትን የራሳቸውን ልምድ አካፈለዋል። "ለምሳሌ በኮሎምቢያ፣ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በካሪታስ ኮሎምቢያ እና በሌሎች ድርጅቶች በኩል እ.አ.አ በ2016 ዓ.ም የሰላም ስምምነት ትግበራ ወቅት ቀውሶችን በማስታረቅ ረገድ ወሳኝ ሚና ቤተክርስቲያን ተጫውታለች" ሲሉ ተናግረዋል።

በሰላማዊ ስምምነት ድርድር ፕሮጀክት ላይ የሰሩትን ሥራ በተመለከተ፣ “የሰላም ጥናትን ከሰላም ግንባታ ተግባር፣ ከሰላም ድርድር እና ከሲቪል ማህበረሰብ ጋር በማጣመር ከጦርነት ወደ ሰላም በሚሸጋገርበት ሂደት እና እንዲሁም ለእርቅ አስተዋፅዖ እናደርጋለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን” ሲሉ አብራርተዋል።

በደቡብ አፍሪካ የሚገኘውን የእውነት እና የእርቅ ኮሚሽን፣ በሞዛምቢክ የሚገኘውን የቅዱስ ኤጂዲዮ  ማህበረሰብ ስራን የመሳሰሉ ምሳሌዎችን በመጥቀስ፣ መንፈሳዊ ሰዎች ከአመታት ብጥብጥ በኋላ ውይይት እና ፈውስ ለማመቻቸት በልዩ ሁኔታ እንደሚቀመጡ ጠቁመዋል።

"ከጦርነት በኋላ ሰዎች ደህንነትን ብቻ ሳይሆን ክብርን፣ መካተትን እና ተስፋን ይፈልጋሉ። እናም ብዙውን ጊዜ እነዚያ ፍላጎቶች ለልብ እና ለህሊና በሚናገሩ ተዋናዮች ሲከናወኑ የተሻሉ ናቸው" በማለት ገልጸዋል።

"ግንኙነት መመስረት በጣም ከባድ ነው፣ ነገር ግን መተማመንን መፍጠርም ደግሞ በጣም ከባድ ነው። እናም ብዙ ጊዜ የምናገኘው ነገር ቢኖር የሰላም ግንባታ ሀይማኖታዊ ተቋማት ብዙ የተለያዩ ግጭቶችን በአንድ ላይ የማሰባሰብ እድል እንዳላቸው ነው" ብለዋል።

የውይይት እና የትብብር መድረክ

ጉባኤው የተለያዩ መሪ ሃሳቦችን ይዳስሳል፡ የቅድስት መንበር ዲፕሎማሲ ሚና፣ ከሃይማኖታዊ ልኬቶች ጋር በሚጋጩ ግጭቶች ውስጥ ዓለማዊ ሽምግልና፣ እና የሃይማኖቶች ተነሳሽነቶች አስፈላጊነት። እንደ አዘጋጆቹ ገለጻ፣ የመጨረሻ ሰነድ ለማውጣት ታስቦ ሳይሆን በትምህርት ተቋማት፣ በሃይማኖት ማህበረሰቦች እና የሰላም አስከባሪዎች መካከል ቀጣይነት ያለው ትብብር ለመፍጠር ታስቧል።

"ይህ የረጅም ጊዜ አጋርነት ጅምር ነው ብለን ተስፋ እናደርጋለን" ብለዋል ፕሮፌሰር ኢቻቫሪያ በላቲን አሜሪካ፣ አፍሪካ እና አውሮፓን ጨምሮ ከተለያዩ ሁኔታዎች የተውጣጡ ሸምጋዮችን ተሳትፎ በመጥቀስ።

ትምህርት፣ ሥልጠና መስጠት፣  የረጅም ጊዜ ለውጥ

ፕሮፌሰር ኢቻቫሪያ በትምህርት ቤቶች ውስጥ ብቻ ሳይሆን መደበኛ ባልሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ መግባባት፣ ሽምግልና እና መተሳሰብን ማዳበር በሚቻልበት ጊዜ የሰላም ትምህርትን አስፈላጊነት ጎላ አድርገው ገልጸዋል።

"ሰላም ለመፍጠር ስልታዊ ነገር አለ" ሲሉ ገልጸዋል፣  ይህም "ድርድርን እንዴት ማመቻቸት እንደሚቻል እና ተጎጂዎችን እንዴት ማጀብ እንዳለብን። ነገር ግን የሰው ወገንም አለ፣ ተጋላጭ የሆኑትን ለማየት እይታችንን እንዴት እንደምናሰለጥን፣ እምነትን እንዴት እንደምንገነባ፣ ሰዎች አዳዲስ መንገዶችን እንዲመርጡ እንዴት እንደምናበረታታ" እነዚህን ማወቅ እጅግ በጣም ጠቃሚ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የሲቪል ማሕበረሰቦች በዘመናዊ ግጭቶች ውስጥ እየጨመሩ ባሉበት ዓለም ውስጥ ተጎጂዎችን በሰላም ሂደቶች ውስጥ ማካተት እና ድምፃቸው እንዲሰማ ማድረግ አስፈላጊ ነው ብለዋል።

"የሰላም ስምምነቶች የዛሬ ጦርነቶች ብቻ እንዲያቆሙ ማድረግ ብቻ ሳይሆን፣ የነገን መከላከል መሆኑን ማረጋገጥ አለብን" ሲሉ አክለው ገልጸዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የሰላም ጥሪ አቀረቡ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የሰላም ጥሪ ስላስከተለው ተጽእኖ ተጠይቀው፣ ፕሮፌሰር ኢቻቫሪያ በትጥቅ ግጭት ውስጥ ለተሳተፉ እና ፈውስ ለሚሹም አስፈላጊነታቸውን አረጋግጠዋል።

"[የጳጳሱ] ድምጽ በሚሊዮን የሚቆጠሩ: ተዋጊዎች፣ ተጎጂዎች እና ለሰላም ፈጣሪዎች በተመሳሳይ መልኩ ይደርሳል። ይህ የህሊና እና የድፍረት ጥሪ ነው" ሲሉ አክለው ገልጸዋል።  

"ከችግር ሁኔታ ወደ ፈጠራ ትብብር መሄድ አለብን" ያሉት ኢቻቫሪያ አክለውም "ይህ ኮንፈረንስ በዚያ አቅጣጫ አንድ እርምጃ ነው" በማለት የትብብር አስፈላጊነትን አጉልቶ ያሳያል ያሉ ሲሆን እናም “በችግር ሁኔታ ፣ለዚህ ሁኔታ በህልውና ሁኔታ ውስጥ ምላሽ መስጠትን መቀጠል አንችልም” ሲሉ በድጋሚ ተናግረዋል፣ ደጋግመው እንደተናገሩት ከሆነ  “አንድ እርምጃ ወደፊት መሄድ አለብን ፣ ወደ ፊት ለመራመድ እና ድልድዮችን ለመገንባት በጋራ ለማሰብ" አንድ ላይ መጓዝ አለብን ያሉ ሲሆን "እዚያ ደረጃ ላይ እየደረስን ነው ብዬ አስባለሁ፣ እናም ይህ ጉባኤ የዚያ ምሳሌ ነው ብዬ አምናለሁ" ካሉ በኋላ ንግግራቸውን አጠናቀዋል።

 

11 Jul 2025, 16:04