ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ “በጋዛ ያለው ብጥብጥ መቆም አለበት” ሲሉ አሳሰቡ
የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን፥ በጋዛ እየተካሄደ ያለው ብጥብጥ መቆም እንዳለበት አሳስበው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ እሑድ ሐምሌ 13/2017 ዓ. ም. በካስቴል ጋንዶልፎ የመልዓከ እግዚአብሔር ጸሎት ባቀረቡበት ወቅት፥ በጋዛ በተፈጸመው ጥቃት ሰለባ የሆኑትን በንግግራቸው ማስታወሳቸውን ለቫቲካን የዜና አገልግሎት ገልጸዋል።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ እሑድ ሐምሌ 13/2017 ዓ. ም. ባቀረቡት የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ከቀናት በፊት በጋዛ በሚገኘው የቅዱስ ቤተሰብ ካቴድራል በእስራኤል ጦር በተፈጸመ ጥቃት የተገደሉት ሦስት ሰዎችን በስም ጠቅሰዋቸዋል።
በእነዚያ ስሞች አማካይነት በጋዛ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በሙሉ መወከላቸውን በአሁኑ ወቅት በትሬንቲኖ ግዛት በዕረፍት ላይ የሚገኙት ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን ለቫቲካን ዜና አገልግሎት ተናግረዋል።
ብጹዕነታቸው ለዜና አገልግሎቱ እንደተናገሩት፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በጋዛ ውስጥ በቅርብ ቀናት ውስጥ በተፈጸሙት አሳዛኝ ክስተቶች የተገደሉትን በስም ማስታወሳቸውን ገልጸው፥ “እነዚህ ስሞች በአደጋው የተጎዱን በሙሉ ይወከላሉ” ብለዋል።
“በአንዱ ወይም በሌላው መካከል ምንም ዓይነት ልዩነት የለም” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን፥ “ሁሉም ተቀባይነት የሌለው ጥቃት ዒላማ እና በፍጥነት ማብቃት ያለበት ግጭት ሰለባዎች ናቸው” ብለው፥ “የጥቃቱ ሰለባዎችን በሙሉ ወደ ልባችን በማስገባት፣ በውስጣችን እንዳሉ በማሰብ ለሁሉም የእግዚአብሔርን ሰላም እንለምናለን” ብለው፥ “በደማቸው መስዋዕትነት አደጋው እንዲቆም እንጸልያለን” ብለዋል።
21 Jul 2025, 17:28