ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ ጋዛ ውስጥ ያለው ጥፋት እና ረሃብ ሊቋቋሙት የማይችሉት መሆኑን ገለጹ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ብፁዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን ዓርብ ዕለት በስልክ ባደረጉት ቃለ ምልልስ፥ ቅድስት መንበር ግጭቶችን በማስታረቅ ረገድ ለምትጫወተው ሚና መልካም የፖቲለካ ፈቃደኝነትን ማሳየት እንደሚገባ አሳስበው፥ ይህ ካለሆነ የሚደርሰው ጉዳት ለሁሉም እንደሚተርፍ በማስጠንቀቅ፥ በጋዛ እየሆነ ያለውን ሁኔታ “ማብቂያ የሌለው ጦርነት” በማለት ገልጸውታል።
“ከገደብ ያለፈ እና ከባድ እየሆነ የመጣ” ስላሉት የጋዛ ውስጥ ስቃይን በማስመልከት ሲናገሩ፥ ሐሙስ ሐምሌ 10/2017 ዓ. ም. የእስራኤል ጦር በጋዛ በሚገኘው የቅድስት ቤተሰብ ካቴድራል ላይ ወታደራዊ ጥቃት በማካሄድ የቁምስናውን መሪ ካህን አባ ገብርኤል ሮማኔሊን ጨምሮ የሦስት ሰዎች ሕይወት ስለ መጥፋት ግልጽ ማብራሪያ እንዲሰጥበት ጠይቀዋል።
ብፁዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን፥ በዓለማችን ውስጥ እየካሄዱ ያሉ በርካታ ጦርነቶችን በማስመልከት ሲናገሩ፥ ቅድስት መንበር ለሽምግልና ዘወትር ፈቃደኛ እንደሆነች ገልጸው፥ ነገር ግን “ሽምግልና ውጤታማ የሚሆነው ሁለቱም ወገኖች ሲቀበሉት ብቻ ነው” ሲሉ አጽንዖት ሰጥተው፥ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ እና በእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ መካከል በተደረገው የስልክ ጥሪ ላይም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ጋዛ ውስጥ በሚገኝ የቅድስት ቤተሰብ ካቴድራል ላይ በተፈጸመው ጥቃት ክብደት አንጻር የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በቀጥታ ማስረዳታቸው እጅግ አስፈላጊ እና አዎንታዊ እንደ ነበር የገለጹት ብፁዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን፥ የስልክ ጥሪውን ተከትሎ የሚጠበቁ ሦስት ነገሮች እንዳሉ አስረድተዋል።
የተፈጸመውን ጥቃት በማስመልከት የተሰጠው የመጀመሪያ ማብራሪያ ስህተት ስለ ነበር፥ ከሁሉ በፊት ቃል የተገባለት የምርመራ ውጤት እውነተኛነት መታወቅ እንዳለበት ተናግረው፥ ምርመራው በቁም ነገር መደረጉ እና ግኝቶቹን ይፋ ማድረግ አስፈላጊ እንደ ሆነ አሳስበዋል። በሁለተኛ ደረጃ የተገቡት በርካታ ቃላት በተግባር መገለጻቸውን ማየት እንደሚያስፈልግ ተናግረው፥ በጋዛ እየሆነ ያለው አስከፊ ሁኔታ ሊቋቋሙት የማይችሉት ስለሆነ፥ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ቤንያሚን ኔታንያሁ የተናገሩት በተቻለ ፍጥነት እውን ሊሆን እንደሚችል ተስፋ እንዳላቸው አስረተዋል።
በጋዛ ገደብ የለሽ ጦርነት እየተካሄደ መሆኑን የገለጹት ብፁዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን፥ “እንደ ጋዛ ያለ ሕዝብ እንዴት ሊወድም እና ሊራብ ይችላል?” ሲሉ ጠይቀዋል። እንደ ቅድስት መንበር ዲፕሎማሲያዊ ቡድን ጋዛ ውስጥ በሚገኘው የቅድስት ቤተሰብ ካቴድራል ላይ የተፈጸመው ጥቃት በእርግጥ ስህተት እንደ ነበር ወይም ሆን ተብሎ ቤተ ክርስቲያንን ለመምታት የታሰበ እንደ ነበር በትክክል ለመረዳት ጊዜን እንደሚወስድ ተናግረው፥ በፍልስጥኤማውያን እና በአይሁዶች መካከል ያለውን ግንኙነት ጨምሮ ክርስቲያኖች በመካከለኛው ምሥራቅ እንደ አስታራቂ ኃይል እንደሚያገለግሉ መረዳት እንደሚገባ ተናግረው፥ ይህ እንዳይሆን ከተደረገ ቢያንስ ወደ ተኩስ አቁም እና በመጨረሻም ወደ ሰላም ሊያመራ የሚችል ማንኛውንም ጥረት የማስወገድ ዓላማ አለ ብሎ ማሰብ እንደሚቻል አስረድተዋል።
በዓለማችን ውስጥ ጦርነት የሚካሄድባቸው በርካታ ቦታዎች በመኖራቸው፥ ቅድስት መንበር በዲፕሎማሲው ረገድ ከዚህ በላይ ምን ማድረግ ትችላለች? ተብለው የተጠየቁት ብፁዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን፥ ቅድስት መንበር ግጭቶችን በማስታረቅ ረገድ የምትጫወተውን ሚና ለማበርከት ዘወትር ዝግጁ መሆኗን እና በተለያዩ አጋጣሚዎች በተግባር መገለጹንም አስታውሰው፥ ከዚህ ውጪ ተጨማሪ እርምጃዎችን መውሰዱ እንደሚከብድ እና በተለይ “‘ሽምግልና’ የሚለውን ቃል በቴክኒካዊ ትርጉሙ ከተጠቀምንበት ውጤታማ ሊሆን የሚችለው ሁለቱም ወገኖች ሲቀበሉት ብቻ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።
በግጭቱ ውስጥ ያሉት ሁለት ወገኖች፣ ሁለት አገሮች ወይም ሁለት ሕዝቦች የቅድስት መንበርን ሽምግልና ለመቀበል ፈቃደኛ መሆን እንዳለባቸው ተናግረው፥ በቴክኒካዊ ሁኔታ ስንመለከተው ተግባራዊ ማድረጉ ከባድ ቢሆንም ቅድስት መንበር ተስፋን የማትቆርጥ መሆኗን አስረድተዋል።
ብጹዕነታቸው በማከልም፥ ቫቲካንን ያላካተቱት በርካታ የሽምግልና ጥረቶች እስከ ዛሬ ፍሬን ያላፈሩ መሆናቸውን በመግለጽ፥ የጦርነት ዋጋ በሁሉም መንገድ ለሁሉም ሰው ከባድ እንደሆነ በማወቅ ጦርነትን ለማስቆም የፖለቲካ ፍላጎት እንደሚያስፈልገው ተናግረዋል።
ተቃራኒ መሆን ባይፈልጉም አለመታደል ሆኖ ያለው የፖለቲካ ፍላጎት እጅግ ዝቅተኛ እንደሆነ ገልጸው፥ እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ አገላለጽ ተኩስ የሚቆምበት ጊዜ መቃረቡን ጠቅሰው፥ ነገር ግን ተግባራዊነቱን በተጨባጭ ማየት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።